ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት ሶሪያ ውስጥ የውኃ ሽታ ሆኖ የቀረውን አሜሪካዊ ጋዜጠኛ ኦስቲን ታይስን በማፈላለግ እርዱን ሲሉ የጋዜጠኛው ወላጆች የትራምፕን አስተዳደር እና የሶሪያን ባለስልጣናት እየተማጸኑ መሆኑን አልጀዚራ በዘገባው አመልክቷል፡፡
ኦስቲን ታይስ በሶሪያ የተፈጠረውን የእርስ በእርስ ጦርነት ለመዘገብ ነበር ወደ ሥፍራው ያቀናው፡፡ ጋዜጠኛው የሄደበትን ጉዳይ ጨርሶ ወደ ጎረቤት አገር ሊባኖስ በመጓዝ ላይ ሳለ እ.አ.አ ነሐሴ 14 ቀን 2012 አንድ የፍተሻ ጣቢያ ከደረሰ በኋላ ግን ዱካው ጠፍቷል፡፡
ወላጅ አባቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለልጃቸው መጥፋት የሰሙት አስደንጋጩ የሥልክ መልዕክት ዛሬም ድረስ በጆሯቸው እያቃጨለ እንደሚረብሻቸው ይናገራሉ፡፡ ሁኔታውንም እንዲህ አስረድተዋል ‹‹ቀኑ አርብ ነበር፡፡ የደወለልኝም አንድ የአሜሪካን ስቴት ዲፓርትመንት የሥራ ባልደረባ ነው፡፡ ልጄ ከደማስቆ ወጣ ብሎ በሚገኝ አንድ የፍተሻ ጣቢያ ከደረሰ በኋላ የገባበት መጥፋቱን ነገረኝ፡፡ ይህ ከሆነ ስድስት ዓመት ከሦስት ወራትን አስቆጥሯል፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ እኔም ሆንኩኝ ባለቤቴ የአዕምሮም ሆነ የአካል ዕረፍት አላገኘንም፡፡ ስለልጃችን እያሰብን እንብሰከሰካለን፤ ፍንጭ ብናገኝ ብለንም በማናውቀው ሀገር እንማስናለን ፤ በቃ እንዲህ ሆኗል ኑሯችን›› በማለት ያስረዳሉ፡፡
እነዚህ ወላጆች አሁንም የልጃቸውን ወሬ ለመስማት ለስምንተኛ ጊዜ በቤሩት ይገኛሉ፡፡ በሊባኖስና በሶሪያ አዋሳኝ ከተሞችም ቤት ለቤት እየተዟዟሩ ስለልጃቸው ጉዳይ ጆሮ መስጠት የዕለት ተዕለት ሥራቸው ሆኗል፡፡ ከሊባኖስ ዋና ከተማ ቤሩት ወደ ደማስቆ በመኪና የሁለት ሰዓት ጉዞ ይፈጃል፡፡ ኦስቲን ለመጨረሻ ጊዜ ታይቶ የጠፋውም በዚሁ አቅጣጫ በመሆኑ ወላጆቹ ይህን አካባቢ የሙጥኝ ብለዋል፡፡ በተለይም ወላጅ እናቱ በአካባቢው እንደልቧ ተዘዋውሯ ልጇን ማፈላለግ እንድትችል የሶሪያ ባለሥልጣናት ቪዛ በመስጠት እንዲተባበሯት የተማጽኖ ድምጿን እያሰማች ትገኛለች፡፡
የትራምፕ አስተዳደር የታጋቾች ጉዳይ ክትትል ኃላፊ የሆኑት አንድ ቀን በንግግራቸው ‹‹ኦስቲን አሁንም በህይወት ያለ ይመስለኛል›› ማለታቸውን ተከትሎ የኦስቲን ወላጆች በአሁኑ ጉዟቸው የሁለቱን ሀገሮች አዋሳኝ አካባቢዎች የሚያካልሉት ትልቅ ተስፋ ሰንቀው ነው፡፡ ምንም እንኳን የልጃቸውን አጋቾች በውል ባያውቋቸውም ተማጽኖ እያቀረቡላቸው ይገኛሉ፡፡ ወላጆቹ እንደሚሉት ‹‹ከአንደበታችን የሚወጣው ቃል የተመረጠና ሰዎችን የማያስቀይም ስለመሆኑ እርግጠኞች አይደለንም፡፡ ለማንኛውም ግን ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡ እኛ ጉዳያችን አንድ ብቻ ነው፡፡ ማነው ልጃችንን ያገተው የሚል ጥያቄም አናነሳም፡፡ የኛ ትልቁ ተማጽኗችን ማነው ልጃችንን የሚመልስልን የሚልነው፡፡››
የአልጀዚራው ጋዜጠኛ አንክል ቦሀራ የኦስቲንን ወላጆች እንዲህ ይገልጻቸዋል፡፡ ‹‹ እያንዳንዱ ወላጅ ስለልጆቹ መልካም ነገር ቢያወራ ደስ ይለዋል፡፡ የኦስቲን ወላጆች ግን የተለዩ ናቸው፡፡ ቤሩት እግራቸው ከረገጠ ጀምሮ በምግብ ቤትም ይሁን በተለያዩ ሥፍራዎች ለሚያገኟቸው ሰዎች ስለጋዜጠኛው ልጃቸው አውርተው አይጠግቡም፡፡ እናት ስትጨርስ አባት ይቀጥላል፤ አባት ሲጨርስ እናት ትቀጥላለች፡፡ ከልጃቸው ጉዳይ በስተቀር ስለሌላ ነገር ማውራት አይፈልጉም ›› እነዚህ ወላጆች ልጃቸውን ለማግኘት ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም፡፡ የአሜሪካና የሶሪያ መንግሥታት እንዲረዷቸው ተደጋጋሚ ጥሪ አቅርበዋል፤ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ሊባኖሳዊያንና ሶሪያዊያን ጋር በልጃቸው ጉዳይ መረጃዎችን ተለዋውጠዋል፤ በጣም አስከፊና አደገኛ በሆኑ ምሽት ክበቦች በመገኘትም መረጃዎችን ለማግኘት ሞክረዋል፤ ቀደም ሲል በኢራን ታግተው ከተለቀቁ አሜሪካዊያን ቤተሰቦችም ጋር ተገናኝተው ልምድ ተለዋውጠዋል፡፡ ግን ጠብ ያለ ነገር አላገኙም፡፡
ልጃቸውን ለማፈላለግ ከአካባቢያቸው እርቀው በመሄዳቸው ለተለያዩ ማህበራዊ ቀውሶች እንደተዳረጉም ይናገራሉ፡፡ ጓደኞቻቸውና ዘመድ አዝማድ በደረሰባቸው ሁኔታ ግራ እንደተጋቡም ይገልጻሉ፡፡ ውስብስብና አስቸጋሪ የህይወት ውጣ ውረድ ቢገጥማቸውም ሁሉም ነገር ከልጃቸው ጉዳይ እንደማይበልጥና ስለ እሱ ሲሉም ችግሮችን መቋቋም እንደማያቅታቸው ያስረዳሉ፡፡
‹‹ኦስቲን ከታገተ ከአስራ አምስት ቀን በኋላ በሕይወት መኖሩን የሚያሳይ የቪዲዮ ምሥል በኦን ላይን ተለቆ አይቻለሁ፡፡ ምስሉ በእርግጥም የልጄ የኦስቲን ስለመሆኑ አልጠራጠርም፡፡ ልጄ በሕይወት እንዳለ ስላረጋገጡልኝ ምስሉን ፖስት ያደረጉ ሰዎችን ላመሰግናቸው እወዳለሁ፡፡ ግን አንድም ሰው ለመደራደር ዝግጁ እንደሆነ አላሳወቀም፤ ይህ ነው አሳዛኙ ጉዳይ›› በማለት እናቱ ደብራ ተናግራለች፡፡
በቴክሳስ ግዛት የሂዩስተን ከተማ ነዋሪ የሆኑት የኦስቲን ወላጆች አሁን ተስፋቸውን በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ላይ አድርገዋል፡፡ ምክንያቱም ፕሬዚዳንቱ የተናገሩትን የሚፈጽሙና ለአሜሪካ ዜጎችና ለሀገሪቱ ክብር ትኩረት የሚሰጡ ናቸው በማለት፡፡ ትራምፕ ከዚህ ቀደም የታገቱ አሜሪካዊያንን ማስለቀቅ የቻሉ ናቸው፡፡ ከነዚህም በሰሜን ኮሪያ ታግቶ የነበረውና የቨርጂኒያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የነበረው ኦቶ ዋርምቢየር ተጠቃሽ ነው፡፡ ኦቶ ዋርምቢየር ምንም እንኳን ታማሚ ሆኖ መጥቶ ለህልፈት ቢዳረግም ለሀገሩ የበቃው በትራምፕ ጫና ነው፡፡ ትራምፕ ከኦቶ ዋርምየር ህልፈት በኋላ ያደረጉት ንግግር ለኦስቲን ወላጆች ተስፋ ሆኗቸዋል፡፡ በዚህም ኦስቲንን ወደ ሀገሩ ለማስመለስ የተቻላቸውን ሁሉ ሊያደርጉ ይችላሉ በሚል በትራምፕ ላይ አመኔታ አሳድረዋል፡፡
የጋዜጠኛው ወላጆች በተለያዩ መድረኮች በሚያደርጉት ቃለ መጠይቅና ፕሬስ ኮንፍረንስ የአሜሪካና የሶሪያ መንግሥታት ስለ ሶሪያም ይሁን ስለሌላ ሀገር ንጹኋን ዜጎች ደህንነት ሲሉ መስማማት እንዳለባቸው መልዕክታቸውን እያደረሱ ይገኛሉ፡፡
ደብራ በ2014 እና በ2015 ሶሪያ- ደማስቆ በመሄድ የልጇን ፎቶ ግራፍ ለሰዎች በማሳየት ለማፈላለግ ሞክራለች። ግን ምንም ፍንጭ አላገኘችም፡፡ ወቅቱ የአሜሪካን መንግሥት ለሶሪያ ተቃዋሚዎች የሚያደርገውን ድጋፍ እየቀነሰ የመጣበት በመሆኑ ሶሪያ በአሜሪካን ላይ ያላትን አቋም ታለዝባለች የሚል ግምት ነበራት፡፡ ይህንን ክስተት እንደጥሩ አጋጣሚ ብትመለከተውም ሁኔታው ግን እንዳሰበችው አልሆነም፡፡
የፕሬዚዳንት በሽር አል-አሳድ መንግሥት የኦስቲን ቤተሰቦች ልጃቸውን ለማፈላለግ የፈለጉትን ሁሉ ማድረግ እንዲችሉ እንተባበራለን ቢልም፤ ደብራ ግን አታምንም፡፡ እንደ እርሷ አባባል ልጇ የታገተውና ይህን ሁሉ ሥቃይ ያየችው በአሜሪካንና በሶሪያ መንግሥት መካከል አለመግባባት በመፈጠሩ ነው፡፡ የልጇ እጣ ፈንታም በሁለቱ አገሮች እጅ ላይ እንደወደቀ ታምናለች፡፡
‹‹በእርግጠኝነት ልጃችን አንድ ቀን ወደ ቤቱ ይመለሳል፡፡ ሁልጊዜ በህልም ዓለም ከልጄ ጋር አድራለሁ፡፡ አንድ ቀን እንደውም ‹እናቴ ከዚህ በኋላ በእኔ ጉዳይ ከማንም ጋር አትነጋገረም፤ ይሄው መጣሁልሽ፤ ወደ ቤታችን መግባት እንችላለን› አለኝ ይህ ህልሜ ደግሞ እውን እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ›› ትላለች ደብራ፡፡
በመጨረሻም የጋዜጠኛው ቤተሰቦች ስለልጃቸው ፍቅርና ስለእምነታቸው ሲሉ የተጋረጡባቸውን ችግሮች ሁሉ እየተጋፈጡ እስከ መጨረሻ ድረስ በመታገል ኦስቲንን ወደቤቱ ለመመለስ ቆርጠው መነሳታቸውን አስረድተዋል፡፡ ለዚህም የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕንና የፕሬዚዳንት በሽር አል-አሳድን ትብብር ጠይቀዋል፡፡
‹‹ሪፖርተርስ ዊዝ አውት ቦርደርስ›› የሚባለው ተቋም መረጃ እንደሚያመለክተው በአሁኑ ወቅት በመላው አለም 44 ጋዜጠኞች በተለያዩ አገራት ታግተው ይገኛሉ፡፡ የሶሪያ የእርስ በእርስ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ሀገሪቱ ለጋዜጠኞች አስቸጋሪ ሀገር ተብላ የተፈረጀች ሲሆን፤ ስድስት ጋዜጠኞች ታግተው ከአለም ሀገራት ከፍተኛውን ቁጥር ይዛለች።
እያሱ መሰለ