አማኑኤል የአዕምሮ ሆስፒታል በቀን 600 ሕሙማንን እያስተናገደ ነው

  • የአዕምሮ ሕክምና በሁሉም የጤና ተቋማት ሊቀርብ ይገባል

አዲስ አበባ፡- በቀን 600 ሕሙማንን እያስተናገደ መሆኑን አማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አስታወቀ። የአዕምሮ ሕክምና አገልግሎት በሁሉም የጤና ተቋማት ማቅረብ እንደሚገባ ተመላክቷል።

የአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሜዲካል ዳይሬክተር ረዳት የሆኑት አቶ አያሌው አባተ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በሀገር አቀፍ ደረጃ የአዕምሮ ሕክምናን ለረዥም ዓመታት በብቸኝነት የተመላላሽ፣ አስተኝቶ ሕክምናና በድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። በቀን ከ500 እስከ 600 ሕሙማንን እያስተናገደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሀገሪቱ በሚገኙ የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና መስጫ ተቋማትን ጨምሮ በሁሉም የጤና ተቋማት የአእምሮ ሕክምና መሰጠት ይኖርበታል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ሁሉም ክልሎች እራሳቸውን የቻሉ ትላልቅ የአዕምሮ ሕክምና መስጫ ማዕከላት ሊኖሩ እንደሚገባም አቶ አያሌው ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከሌሎች የጤና አገልግሎቶች ጋር ሳያካትት የሥነ-አዕምሮ ሕክምናን በብቸኝነትት የሚሰጥ የጤና ማዕከል መሆኑ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑን አንስተዋል። ከ120 ሚሊዮን በላይ ለሆነ ሕዝብ የሚያገለግል ብቸኛ የመንግሥት ተቋም መሆኑ ጫናውን እንደሚያሳይ ጠቁመዋል።

ሆስፒታሉ ረዥም ዓመታትን ያስቆጠረ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አገልግሎቱ በሚፈለገው መጠን እንዳልዘመነ አስታውቀው ፤ በግቢው ውስጥ የመሰረተ ልማት፣ በቂ የታካሚዎች አልጋ እጥረት እና የሥነ-አዕምሮ ባለሙያዎችና የግብዓት እጥረት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ሶስት ዓመታት ከተለያዩ አቅጣጫዎች ሕክምናውን ፈልገው የሚመጡ ታካሚዎች በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ አለመረጋጋቶች ሳቢያ መምጣት ባለመቻላቸው የተገልጋይ ቁጥሩ ቀንሶ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ በቂ የሕክምና መስጫ ቦታ ባለመኖሩ በአገልግሎቱ ላይ ከፍተኛ መጨናነቅ አለ ብለዋል፡፡

በሆስፒታሉ ሕክምና የጀመሩትን በቅብብሎሽ ወደሚቀርባቸው ጤና ተቋማት በመላክ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ጥራት ያለውን አዕምሮ ሕክምና ተደራሽ በማድረግ ብሎም በሆስፒታሉ ያለውን ጫና በመጠኑ የሚቀንስ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የአዕምሮ ሕክምና አገልግሎቱን ለማስፋት በሁሉም የጤና ተቋማት የአዕምሮ ሕክምና መሰጠት አለበት የሚል ስትራቴጂ መቀመጡን አስታውቀዋል።

የተቀመጠውን ስትራቴጂ ሁሉም የጤና ተቋማት በመተግበር የሥነ-አዕምሮ ባለሙያዎች እንዲቀጥሩ እና ቀላል የአእምሮ ህክምና አገልግሎቶችን እንዲያቀርቡ መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የህብረተሰቡን የአዕምሮ ጤና የመጠበቅ አገልግሎት በአንድ ሆስፒታል ብቻ የሚሰራ ባለመሆኑ በቂ በጀትና ባለሙያዎችን በማሰማራትና ተቋሙን ማበረታታት በተለይም አምራች ዜጋውን እያጠቃ ለሚገኘው የአዕምሮ ህመም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡

አማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በቀጣይ በሥነ-አዕምሮ የልህቀት ማዕከል የመሆን እቅድን በመያዝ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ከአዕምሮ ሕክምና በተጨማሪ ለታካሚዎች የውስጥ ደዌ፣ የማዋለድና ሌሎች ተጨማሪ የጤና አገልግሎቶችን በማካተት ሕክምና ለመስጠት ማቀዱን አስታውቀዋል፡፡

በአዕምሮ ህመም ዙሪያ ማህበረሰቡ ብቻ ሳይሆን የጤና ባለሙያውም ጭምር የተሳሳተ እሳቤ እንዳላቸው ጠቅሰው፤ የአዕምሮ ህመም ታክሞ መዳን የሚችል በመሆኑ ህብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ ሊኖረውና ወደሕምክና ተቋማት መሄድ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ማህሌት ብዙነህ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 15/2017 ዓ.ም

Recommended For You