ዘላቂ ኢኮኖሚ ዕድገትን ለማረጋገጥ የሰው ሀብት ልማት ላይ በትኩረት መሥራት ይገባል

አዲስ አበባ፡ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማረጋገጥ የሰው ሀብት ልማት ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩትና የአፍሪካ የኢኮኖሚ ምርምር ኮንሰርቲየም “የሰው ሀብት ልማት በኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሃሳብ ትናንት የፖሊሲ ውይይት አካሂደዋል። በተጨማሪ ተቋማቱ በጋራ ለመሥራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ጸጋ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማረጋገጥ የሰው ሀብት ልማት ላይ በትኩረት ሊሠራ ይገባል፡፡

ኢንስቲትዩቱ ፖሊሲ ለሚያወጡ የመንግሥት አካላት ምርምርና ሳይንሳዊ ማስረጃ ላይ መሰረት ያደረገ ጥናት በማድረግ ግብዓት እንደሚሰጥ ጠቁመው፤ ለፖሊሲ የሚጠቅሙ ሰነዶችን እንደሚያዘጋጅ አስረድተዋል። ተቋሙ የፖሊሲ ሰነዶችን በማዘጋጀት ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እንደሚያቀርብ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ያለው የሰው ሀብት ልማት ለኢኮኖሚ እድገት ጠቃሚ ነው ያሉት አቶ ፍቃዱ፤ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማረጋገጥ የሰው ኃይል ልማት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

ምርምሮችን ሴክተር መስሪያ ቤቶች እንዲጠቀሙበት እንደሚደረግም ጠቁመው፤ በውይይቱ ላይም የትምህርት ጥራት ችግር ያልተሻገረችው ችግር እንደመሆኑ ከለውጡ ወዲህ በርካታ ሥራዎች የተሰሩ ቢሆንም የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እንደሚጠይቅ አመላክተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ያለው የሰው ሀብት ልማት ለዘመናት የቆዩ ችግሮች እንዳሉበት በመግለጽ፤ የትምህርት ተቋማትን ተደራሽ በማድረግ በኩል የተሠራ ቢሆንም ጥራት ላይ ግን በሚፈለገው ልክ አለመሠራቱን አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ያለው ትልቁ ሀብት የሰው ኃይል ቢሆንም ያለው እውቀት ደግሞ በቂ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ በትምህርት ተደራሽነትና ጥራት ላይ የተጀመሩ ሥራዎች አጠናክሮ በማስቀጠል የሚፈለገውን የሰው ኃይል ልማት ማሳካት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

የአፍሪካ ኢኮኖሚ ምርምር ኮንሰርቲየም የምርምር ዳይሬክተር አቢ ከድር (ፕ/ር) በበኩላቸው፤ በትምህርት ላይ ኢንቨስት ማድረግ ከተቻለ ውጤታማ የሰው ኃይል ልማትን ማምጣት ይቻላል ብለዋል፡፡

የትምህርት ጥራት ለአንድ ሀገር የሰው ኃይል ልማት ወሳኝ ነው ያሉት ፕሮፌሰር አቢ፤ በውይይቱም በትምህርት ጥራትና በተማሪዎች ምገባ መርሀ ግብር ላይ ሰፊ ውይይት መደረጉን አንስተዋል።

ጥናቱን ተከትሎ የቀረቡት የፖሊሲ ምክረ ሃሳቦች የተማሪዎች ምገባ መርሀ ግብሩ በሁሉም የክልልና የከተማ አስተዳደር አካባቢዎች ላይ ተግባራዊ ሊደረግ እንደሚገባ ማመላከቱን ጠቅሰው፤ በቀጣይ በትምህርት ጥራትና በሰው አቅም ግንባታ ላይ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ የሚያመላክት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የመግባቢያ ስምምነቱ ተቋማቱ ቀደም ሲል ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚያስችል ገልጸው፤ የሰው ኃይል ልማት ፕሮጀክትን ጨምሮ ሌሎች ተግባራትንም በጋራ ለመሥራት የሚያስችል መሆኑን አስታውቀዋል።

ማርቆስ በላይ

 አዲስ ዘመን ጥቅምት 15/2017 ዓ.ም

Recommended For You