አዲስ አበባ፡– በአዲስ አበባ ከተማ የትምህርት ግብዓት አቅርቦቱና የትምህርት ቤት ምገባው በጀት ከዘጠኝ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን የምገባ ኤጀንሲው አስታወቀ፡፡ የመርሀ ግብሩ መጀመር በተማሪዎች ውጤት ላይ ለውጥ አምጥቷል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምገባ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ምነወር ኑረዲን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በትምህርት ቤት ምገባ በአሁኑ ወቅት ከ801ሺህ በላይ ተማሪዎች ተጠቃሚ ሆነዋል።
አጠቃላይ የግብዓት አቅርቦቱና የትምህርት ቤት ምገባው በጀት ከዘጠኝ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን ጠቁመው፤ ይንን ተሞክሮ ለማየት ከተለያዩ ሀገራት ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ አካላት ቁጥራቸው እየጨመረ ነው ብለዋል፡፡
የምገባ መርሀ ግብሩ ከሙአለ ህጻናት እስከ ስምንተኛ ክፍል መሆኑን የጠቀሱት አቶ ምነወር፤ የግብዓት አቅርቦት እስከ 12ኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች የሚሰጥ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የተማሪ ቁጥር በየጊዜው በፍጥነት እየጨመረ በመሆኑ በጀቱም እየጨመረ እንዳለ አመላክተዋል፡፡
የትምህርት ቤት ምገባ መርሀ ግብሩ ሲጀመር የተጠቃሚ ተማሪዎች ቁጥር 300 ሺህ እንደነበር አስታውሰው፤ ዛሬ ላይ ከ801 ሺህ በላይ መድረሱን አቶ ምነወር ገልጸዋል፡፡
ከአንድ ሚሊዮን 34ሺህ በላይ ተማሪዎች የደንብ ልብስ (ዩኒፎርም)ና ሌሎች የትምህርት ግብዓቶች ማቅረብ እንደተቻልም ተናግረዋል፡፡ ይህ በመሆኑ ከዋጋ ማሻሻያና ጭማሪው ጋር ተያይዞ በአሁኑ ወቅት የግብዓት አቅርቦቱና የምገባው በጀት ከዘጠኝ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን አስታውቀዋል፡፡
በትምህርት ቤት ምገባ መርሀ ግብሩ፤ ለ16ሺህ እናቶች የስራ እድል ተፈጥሮላቸዋል ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ በዚህ ስራም አዲስ አበባ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ እውቅናዎች ማግኘቷን ተናግረዋል፡፡ የምገባ ማእከላቱ የበርካታ ዜጎችን ህይወት ከመደጎም አልፎ ለተለያዩ ሀገራት ተሞክሮን የሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እንደገለጹት፤ የምገባ አገልግሎቱ በትምህርት ቤት ውስጥ መጀመር መቻሉ ዘርፈ ብዙ ውጤቶችን አስገኝቷል፡፡
በኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚታወቅ አብሮ የመኖርና የመደጋገፍ ባህል እንዲጠናከርና በተመሳሳይ ተማሪዎች ስለ ምግብና ስለ ትምህርት ቁሳቁስ እንዳይጨነቁ አድርጓል ብለዋል፡፡
አንድ አይነት ምግብ፣ ተመሳሳይ የደንብ ልብስና ሌሎች የመማሪያ ግብዓቶችም በተመሳሳይ ሁኔታ ስለሚቀርቡ በተማሪዎች መካከል ይታይ የነበረውንም ልዩነት አስቀርቷል ሲሉ ተናግረዋል።
ተማሪዎች ትምህርታቸው ላይ ብቻ ትኩረት በማድረጋቸው በውጤት ደረጃም መሻሻሎች እየመጡ ነው፡፡ ይህ ወደፊትም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ነው ያሉት፡፡
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15 ቀን 2017 ዓ.ም