አዲስ አበባ፡– የኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚ በ2021 ዓ.ም ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት አንድ ነጥብ ሦስት ትሪሊዮን ብር በላይ አበርክቶ እንደሚኖረው ጂኤስኤምኤ በተባለ ዓለም አቀፍ ድርጅት ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባባር ያወጣው ሪፖርት አመላከተ።
የተቋሙ ከሰሀራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት የፐብሊክ ፖሊሲና ኮሙኒኬሽን ከፍተኛ ዳይሬክተር ካሮሊን ምብጉዋ ትናንት ሪፖርቱን ሲያቀርቡ እንዳሉት፤ የቴሌኮም ማሻሻያና የሞባይል ቴክኖሎጂ ኢንቨስትመንቶች በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ እና በሕዝብ አገልግሎቶች በመሳሰሉት ቁልፍ ዘርፎች እድገትን ያበረክታሉ።
በዚህም በ2021 ዓ.ም ከአንድ ሚሊዮን በላይ አዳዲስ ሥራዎች እንደሚፈጠሩ እና ለመንግሥት 57 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ የታክስ ገቢ ያስገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።
እ.ኤ.አ. በ2023 ዘርፉ 700 ቢሊዮን ብር ለጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት አበርክቶ 57 ቢሊዮን ብር ከታክስ ገቢ አስገኝቷል ያሉት ከፍተኛ ዳይሬክተሯ፤ የሞባይል ኢንተርኔት ግንኙነቶች በ65 በመቶ ያደገ ሲሆን፤ የ4ጂ ሽፋን በስምንት እጥፍ መጨመሩን ጠቁመዋል።
የሞባይል ኢንተርኔት ተጠቃሚነትና በቴሌኮም ገበያ ላይ ያለው ውድድር እንዲጨምር ኢትዮ ቴሌኮም እና ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ትልቅ ሚና እንደነበራቸው አንስተዋል።
በ2021 ዓ.ም ከ50 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን ከሞባይል ኢንተርኔት ጋር ይገናኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አመላክተው፤ ይህም በ2021 ዓ.ም በግብርና ዘርፉ ላይ 140 ቢሊዮን ብር፣ በማኑፋክቸሪንግ ላይ የ114 ቢሊዮን ብር አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ያለውን የዲጂታላይዜሽን አቅም ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት አቅርቦትን ማመቻቸት፣ ፈጣን የቴሌኮም ማሻሻያ ማድረግ፣ የሞባይል ቀፎዎችን ዋጋ ተመጣጣኝነት ማሻሻል፣ የሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎቶችን ማስፋፋት እንዲሁም የዲጂታል ክህሎትን እና የመንግሥት አገልግሎቶችን ማሳደግ የሚሉ ጉዳዮች በምክረ-ሃሳብነት ቀርበዋል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ሪፖርቱን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት፤ ሪፖርቱ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚውን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማገዝ እያከናወነች ያለው ሥራ ውጤታማነት ያሳየ ነው። በዚህም ዲጂታል ኢኮኖሚው ለአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ስምንት በመቶ አስተዋጽኦ ማድረጉን አመላክቷል።
ባለፉት ስድስት ዓመታት በተወሰዱ ርምጃዎች ሀገራችን ቀደም ሲል ከነበራት የኢንተርኔት ተደራሽነት እያደገ መምጣቱን አሳይቷል ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፤ ይህም ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ላይ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ሀገሪቱን በአፍሪካ ደረጃም ተጠቃሽ የሚያደርጋት መሆኑን አንስተዋል።
ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የ2025 ስትራቴጂ ተቀርጾ በመተግበር ላይ መሆኑን ገልጸው፤ ስትራቴጂውን እውን ለማድረግም መንግሥት፣ የግሉ ዘርፍና ሌሎችም ባለድርሻዎችን ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል።
ጂ.ኤስ.ኤም.ኤ የሞባይል ስነ-ምህዳርን አንድ የሚያደርግ ዓለም አቀፍ ድርጅት ሲሆን፣ አዳዲስ ፈጠራን በመፍጠር፣ ለማዳበር እና ለመልካም የንግድ ስነ-ምህዳሮች እና የህብረተሰብ ለውጦችን ለማምጣት መሰረት አድርጎ እንደሚሠራ ተመላክቷል።
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15 ቀን 2017 ዓ.ም