የዓባይ ፖለቲካ በተፋሰሱ ሀገራት መነፅር

ዜና ትንታኔ

የታችኞቹ የዓባይ ወንዝ ተፋሰስ ሀገራት ውሃውን በብቸኝነት ለመጠቀም ካላቸው ፍላጎት የተነሳ በቅኝ ግዛት ውል ስምምነት ላይ ተመርኩዘው መቆየታቸው የሚታወስ ነው።

ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባች በምትገኘው ግድብ አማካኝነት የሚለቀቀው የውሃ መጠን ይቀንስብናል የሚል ስጋት ቢያድርባቸውም ኢትዮጵያ ግን የሚፈሰውን የውሃ መጠን ጭምር ይፋ በማድረግ ስጋታቸው ትክክል እንዳልሆነ በተደጋጋሚ አሳይታለች።

ውሃውም አሁንም ድረስ እየፈሰሰ በበቂ ሁኔታ እየደረሳቸው ይገኛል። አንዳንዴም ከባድ ዝናብ በሚዘንብበት ወቅት የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት በጎርፍ ጭምር ሲጠቁ ላስተዋለ ስጋታቸው ልክ እንዳልነበረ መገንዘብ ይቻላል።

በአፍሪካ ቀንድ አለመረጋጋት ለማስፈን የሚሰሩ ኃይሎች የውሃውን ጥያቄ በመመርኮዝ ለተለየ ደባና ሕጋዊ ላልሆኑ አካሄዶች እጃቸውን ሲዘረጉም ይስተዋላል። ታዲያ በዓባይ ግድብ ዙሪያ በተለይም ከግብጽ በኩል እየተደረገ ያሉ እንቅስቃሴዎች መነሻቸው ምንድን ነው አላማቸውና የመጨረሻ ግባቸው ምን ያሳያል በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል።

የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ኅብረት /ኢዴኅ/ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ገብሩ በርሔ፤ ግብጽ የዓባይ ወንዝ የውሃ ድርሻዬ ይጎልብኛል ከሚል መሰረት ከሌለው ስጋት በመነሳት በኢትዮጵያ ላይ ተደጋጋሚ ሴራዎችን እንደምትሸርብ ያነሳሉ።

የኢትዮጵያን ሕዝብ ሆን ተብሎ በመከፋፈል የውስጥ አለመረጋጋት ለመፍጠርና የውስጥ ችግሮቻችንን ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዳንፈታ እያደረገች ያለችው ጥረት ለኢትዮጵያውያን አዲስ አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡

ኢትዮጵያ በመልክዓ ምድሯ የተገኘውን የውሃ ሃብት እንዳትጠቀም የሚከለክላት ዓለም አቀፍ ሕግ አለመኖሩን ጠቁመው፤ የዓባይ ወንዝ ሀብትን እንዳንጠቀም ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች፤እያደረገችም ነው ይላሉ፡፡

በዚህም እንደእብድ ውሻ በየአቅጣጫው ተጽእኖ ለመፍጠር በሱዳን፣ በኤርትራ ፣ በደቡብ ሱዳን አሁን ደግሞ በሱማሊያ በኩል የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግና ችግር ለመፍጠር ጥረት እያደረገች ቢሆንም የሱማሊያ ሕዝብ ከፍተኛ ጥላቻውን ሲያሳይ መቆየቱን አንስተዋል።

በአንድ አህጉር እንደመኖራችን እንደ ጉርብትናችን ተከባብረንና ተሳስበን፤ ችግሮች ቢኖሩም ተወያይቶ መፍታት ሲቻል ወደማስፈራራትና ደባ ውስጥ የመግባት አዝማሚያ መኖሩ የዓባይ ወንዝ ተጠቃሚነት ላይ ያለባቸውን ስጋት ያሳያል ይላሉ። ይህ አካሄድ ትክክለኛው መንገድ ባለመሆኑ መተባበር ላይ የተመሰረተ አካሄድን መከተል እንደሚገባ ይጠቁማሉ።

ህዳሴ ግድብን ሱዳን እና ግብጽን በማይጎዳ መልኩ በጋራ እንጠቀማለን ተብሎ እንደሚታሰበው ሁሉ ዲፕሎማሲ ጥረትና ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ስራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው ያመላከቱት፡፡

መንግሥት እውቀትን መሰረት ያደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችና መግባባቶች ለመፍጠር የሚያከናውናቸው ስራዎች የሚደገፉ መሆኑን ጠቅሰው፤ የውሃ ዲፕሎማሲው በናይል የትብብር ማሕቀፍ የታገዘበት መንገድም አስፈላጊ መሆኑን ነው ያነሱት።

አቶ ገብሩ እንደሚገልጹት፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወታደራዊ አቅም እና በሀገር ፍቅር ምንም ያህል ችግሮች ቢኖሩበትም ቀፎው እንደተነካበት የንብ መንጋ በጋራ ለሀገር ሉአላዊነትና አንድነት የሚቆም ቆራጥ ሕዝብ መሆኑ ከዓድዋ ጀምሮ ያሳየ በመሆኑ ችግሮች ቢመጡ እንኳን ተባብሮ የማለፍ ልምድም አለው።

በተለይም ግብጽ ኢትዮጵያን በዓባይ ግድብና የባህር በር እንዳታገኝ የምታደርገው ጥረት ብሎም ሱማሊ ላንድን በማስፈራራትና የጋራ ጠላትን ለመፍጠር የሚያደርጉት ጥረት የማይሳካ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

አቶ ገብሩ እንደሚሉት፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሀገርን ህልውና መሰረት አድርገው የተቋቋሙ በመሆኑ ከመነጣጠል ይልቅ በጋራ ከመንግሥት ጎን በመቆም የዓባይ ዲፕሎማሲያዊ ስራን ማገናዘብ ለሀገር ዘብ የመቆም ልምድን ሊያዳብሩ ይገባል፤

የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ /ኢሶዴፓ/ አባል አቶ ሉምባ ደምሴ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ እና ግብጽ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ረዥም ዓመታትን የፈጀ ቢሆንም በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረት አይደለም ይላሉ፡፡

በተለይም ግብጽ የዓባይን ውሃ ጥቅም የጋራ ለማድረግ ከተፋሰሱ ሀገራት አዲስ ስምምነት የማፈንገጥ ባህሪ እያሣየች መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ለጋራ ጥቅምና ሰላም እጇን ዘርግታ ጥያቄ ብታቀርብም ግብጽ ብዙውን ጊዜ ከራሷ ጥቅም ጋር እንጂ የጋራ ጥቅም እሳቤ እንደማታይ ያስረዳሉ።

መንግሥት የሰላም እጁን እየዘረጋ ጥረት ቢያደርግም በምላሹ ግን እንደግብጽ ያሉ ሀገራት የኢትዮጵያን ሉአላዊነትን ለመጋፋትና የተፈጥሮ ሀብታችንን እንዳንጠቀም የሚሰሩትን ስራ እግር በእግር ተከታትሎ ማምከን እንደሚገባም ይጠቁማሉ።

ከመንግሥት በተጨማሪም ፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገር ጉዳይ የሚወጡት ሚና ከፍተኛ ነው ያሉት አቶ ሉምባ ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካ አላማ ልዩነት ቢኖራቸውም ውድድርንና ሰላምን መሰረት ያደረጉ በመሆናቸው ከሀገር አቀፍ እንቅስቃሴና ከሀገር ጥቅም ጋር የተያያዘ ስራ ማከናወን አለባቸው ይላሉ።

በመሆኑም ፓርቲዎች በዲፕሎማሲው፣ የውስጥ አንድነትን በማጠናከር እንዲሁም ከሴረኞች ጋር ባለመተባበር ለሀገራቸው ያላቸውን አበርክቶ ከፍ ማድረግ እንዳለባቸው ይገልጻሉ። ከየትኛውም ተላላኪ አካላት ነጻ በመሆን በሀገር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ያለማዳላት በጋራ የሚሰሩ መሆናቸውን በተግባር ማሳየት እንደሚገባቸው ይጠቁማሉ።

ሁሉም ሊኖር የሚችለው ሀገር ስትኖር ነውና በዓባይ የውሃ ፖለቲካ ላይ ተንተርሶ የሚመጣን እኩይ ተግባር ለመመከት ቴክኖሎጂን፣ አንድነትን፣ ዕውቀትና ሙሉ አቅም ተጠቅሞ መስራት እንደሚገባም የፖለቲካ ፓርቲ ኃላፊዎቹ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል።

ማህሌት ብዙነህ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You