ዜና ትንታኔ
በርካታ ሰዎች አሁን ላይ ታመው ወደ ሕክምና ተቋማት ከሄዱ በኋላ ‘ይሄን ምግብ አትውሰዱ፤ ይሄ ምግብ ለጤናችሁ አደጋ ነው’ ተባልን ሲሉ መስማት የተለመደ ሆኗል። የሕክምና ባለሙያዎችም ለስኳር፣ ለደም ግፊት፣ ለጨጓራና ለመሳሰሉት በሽታዎች መባባስ ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ምግቦችን ለይተው ጥንቃቄ አድርጉ የሚል ምክራቸውን ይለግሳሉ።
በርካታ ኢትዮጵያዊ ስለጤናማ አመጋገብ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑ ስለምግብ ሲነሳ ወደ አእምሮው የሚመጣው ስጋው ፣ ዶሮው፣ ቅቤውና የመሳሰሉት ቅባት አዘል መብሎች ናቸው። አትክልትና ፍራፍሬዎች ደግሞ የኢኮኖሚ አቅም ያነሰው ብቻ የሚመገባቸው አድርጎ የመውሰድ ችግር ይስተዋላል።
“ሆድን በጎመን ቢደልሉት ጉልበት በዳገት ይለግማል” የሚሉ ብሂሎች አትክልት አላስፈላጊ አድርጎ የመውሰድ ለጥንካሬና ለጉልበታማነት ደግሞ ስጋና ሌሎቹን ምግቦች ተመራጭ አድርጎ የመውሰድ የተዛባ አመለካከትን የሚያሰርፁ ናቸው።
አትክልትና ፍራፍሬን የችግር ጊዜ መውጫ ብቻ አድርጎ የመመልከት ችግሩ ለጤናማ አመጋገብ ተመራጭ አለመሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትም ለመሆኑ ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓት ምንድነው? ጤናማ የሚባለው የአመጋገብ ስርአት የትኛው ነው ?ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓትንስ አለመከተል ምን ያስከትላል? ሲል የጤና ባለሙያዎችን አነጋግሯል፡፡
በጤና ሚኒስቴር የሥርዓተ-ምግብ ማስተባበሪያ ክፍል የመከላከል ተኮር ሥርዓተ ምግብ ዴስክ ኃላፊ ቅድስት ወልደሰንበት እንደሚሉት፤ በሀገሪቱ ስለ ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓት ያለው ግንዛቤ አነስተኛና እንደቅንጦት የሚወሰድ ነው።
ነገር ግን ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓትን ባለመከተል የተነሳ ህጻናት በመቀንጨር አዋቂዎች ደግሞ በተለያዩ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች እየተጠቁ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
በቅርቡ ጤና ሚኒስቴርና ዩኒሴፍ ያደረጉት ጥናት እንደሚያሳየው፤ በኢትዮጵያ ከአምስት ዓመት በታች ህጻናት መካከል 39 በመቶ የሚሆኑት የመቀንጨር ችግር አለባቸው። ከነዚህም ውስጥ 11 በመቶው በመቀጨጭ የተጠቁ ናቸው ይላሉ።
የመቀንጨር ችግር የሚፈጠረውም ህጻናት ከተወለዱ በኋላ ተመጣጣኝ ምግብ ባለማግኘታቸውና እናት እርጉዝ በነበረችበት ወቅት ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓት ባለመከተሏ የሚከሰት መሆኑን ያስረዳሉ። በጥናቱ መሰረት 75 በመቶ የሚሆኑ የሀገሪቱ ህጻናት እስከ ሁለት ዓመት አትክልትና ፍራፍሬ የማያውቁ ሲሆን የተመጣጠነ ምግብ የሚያገኙት ደግሞ ስምንት በመቶዎቹ ብቻ መሆናቸውን እንደሚያትት ያነሳሉ፡፡
ለዚህ ችግር መነሻ ምክንያቱ ማህበረሰቡ ስለ ሥርዓተ ምግብ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ መሆኑን አንስተው፤ ተቋማቸው በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚያደርገው ቅኝት ሰዎች በአካባቢያቸው በርካታ ሊበሉ የሚችሉ አትክልትና ፍራፍሬዎች ቢኖሩም እሱን እንደማይመገቡና ከዛ ይልቅም አንድ አይነት የምግብ ይዘት ያላቸው ምግቦችን በተለያየ መልኩ እንደሚመገቡ ነው የጠቆሙት።
በዚህም በበርካታ የሀገሪቱ አካባቢ ያሉ ዜጎች ሊኖራቸው ከሚገባው ክብደት አንሰው ወይም እጅግ በልጠው ፣ ከነበራቸው ተፈጥሯዊ ውበትም ጎድለው እንደሚታዩ ይገልጻሉ፡፡
ይህ ችግር ከገጠራማው አካባቢ ባልተናነሰ በከተማዎችም ላይ የሚስተዋል ሲሆን፤ ለዚህም ምክንያቱ የአትክልትና ፍራፍሬ ምግቦቹን ጠቀሜታ ባለመረዳትና ጣፋጭ ነገር ከመፈለግ የመጣ መሆኑን ያስረዳሉ።
ነገር ግን ሰዎች ምግብን ሲመገቡ ከጣእም ባለፈ ወደ ሰውነታቸው የሚያስገቡት ምግብ ምን አይነት የጤና ጠቀሜታዎችን ያስገኛል የሚለውን ማሰብ እንደሚኖርባቸው ገልጸው፤ ይህንን ችግር ለመቅረፍም ጤና ሚኒስቴር ያዘጋጀውን የሥርዓተ ምግብ ፖሊሲ መከተል እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡
ፖሊሲው አንድ ሰው በቀን ከ100 እስከ 200 ግራም አትክልትና ፍራፍሬ ፣ 80 ግራም ጥራጥሬ፣ 60 ግራም የእንስሳት ተዋጽኦ መመገብ እንደሚያስፈልግ የሚገልጽ መሆኑን ነው የጠቆሙት።
የስነ-ምግብ አማካሪ የሆኑት አብነት ተክሌ እንደሚሉት ደግሞ፤ ምግብ ከመጥገብና ከመራብ ባለፈ በአካላዊና በአእምሮዊ ጤንነት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡
ለአብነትም በቀን ውስጥ አትክልትና ፍራፍሬዎችን፣ የቅባት እህሎች እና ጥራጥሬን አዘውትረው እና በከፍተኛ መጠን የሚመገቡ እንዲሁም ዶሮ፣ እንቁላል፣ የወተት ተዋፅኦንና ቀይ ስጋን ደግሞ አልፎ አልፎ የሚመገቡ ሰዎች በድባቴና በአእምሮ ጭንቀት የመጠቃታቸው መጠን አነስተኛ ነው ይላሉ፡፡
በአንጻሩ ደግሞ ዝቅተኛ የአሰር መጠን፣ ከፍተኛ የሆነና ጤናማ ያልሆነ የቅባት መጠን ያላቸውን ምግቦች ፣ ስኳር እና ተፈጥሮአዊ ያልሆኑ ማጣፈጫዎችን የሚመገቡ ሰዎች ደግሞ የስሜት መረበሽ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ይጠቁማሉ።
በአብዛኛው ማህበረሰብም ጤናማ ያልሆኑ ምግቦች ጠቃሚ ተደርገው የሚሳሉ መሆናቸውን ገልጸው፤ ነገር ግን የተለያዩ የምግብ አማራጮች በመጠቀም የተመጣጠነ የአመጋገብ ዘይቤን በመከተል አካላዊም ሆነ አእምሯዊ ጤና መጠበቅ እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡
ጤናን መጠበቅ የሚቻለው አንድም በቂ አካላዊ እንቅስቃሴ በማድረግ እንዲሁም ጤናማ አመጋገብን በመከተል መሆኑን አንስተው፤ በርካቶች በአካባቢያቸው ያለውን የተመጣጠነ ምግብ በመመገብ ከአላስፈላጊ የጤና ጉዳት እራሳቸውንም ሆነ ቤተሰባቸውን መከላከል እንደሚገባቸው ይገልጻሉ።
መስከረም ሰይፉ
አዲስ ዘመን ዓርብ ጥቅምት 15 ቀን 2017 ዓ.ም