“ታሪካዊው የኢትዮጵያና ሩሲያ የሁለትዮሽ ግንኙነት ተጠናክሮ ቀጥሏል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፦ ታሪካዊ ቁርኝት ላይ የተመሰረተው የኢትዮጵያና ሩሲያ የሁለትዮሽ ግንኙነት ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሩሲያው አቻቸው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ትናንት ውይይት አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ትናንት ባሰፈሩት መልዕክት፤ በሁለቱ ሀገራት ታሪካዊ ቁርኝት ላይ የተመሠረተው የሁለትዮሽ ግንኙነት እያደገ መቀጠሉንም ጠቅሰዋል።

የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጠናከር እና አዳዲስ የትብብር መንገዶችን ለመፈተሽ በሚደረገው ጥረት ላይ እንደሚሠሩም ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ መድረኩ የጋራችን በሆነው የብሪክስ መድረክ ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ ትብብር እንድናደርግ በር ከፍቶልናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሩሲያ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሟትም ኢኮኖሚያዊ መረጋጋትን ለማስጠበቅ መቻሏን አድንቀዋል። ይህም ለኛ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ጠንክረን ከሠራን እና ቀጣይነት ባለው መልኩ ከተሳተፍን ኢኮኖሚያዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ሌሎች ግንኙነታችንን ማሳደግ እንችላለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በበኩላቸው፤ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታችንን ያከበርንበት 125ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የበለፀገ ታሪክና የብዙ ዓመታት የወዳጅነት፣ የመከባበር፣ የሕዝባችን ባህላዊ ቅርበት የታየበት እንደሆነ ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እና በኤጀንሲዎች መካከል ጥሩ ግንኙነት በመመሥረት ተወያይተናል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ሩሲያ ለምታደርጋቸው አብዛኛዎቹ ውጥኖች ኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ እናደንቃለን ብለዋል።

ሩሲያ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሳደግ ልዩ ትኩረት ሰጥታለች። በሁለተኛው የሩሲያ አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይ የተደረሱትን

ስምምነቶችንም ተግባራዊ እናደርጋለን ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ እ.ኤ.አ. በ2023 ከኢትዮጵያ ጋር የተደረገው የንግድ ልውውጥ መጠን በ65 በመቶ መጨመሩን አይተናል ነው ያሉት።

ግንኙነታችን በጤና አጠባበቅና በሳይንሳዊ ምርምር ዘርፎች እንዲሰፋ እንፈልጋለን። የሩሲያ ሸማቾች ኤጀንሲም ከኢትዮጵያ አቻዎቹ ጋር በተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ ተባብረው መሥራት እንዲችሉ ይደረጋል። በዚህም የቴክኖሎጂ ሽግግር እና ሙያዊ ስልጠና እንደሚኖር ይጠበቃል ሲሉ ተናግረዋል።

የሩሲያ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ሊቀመንበር በሚቀጥሉት ወራት አዲስ አበባን ለመጎብኘት ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ጥቅምት 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You