“ብሪክስ አብሮ የማደግን ትልቅ እድል ይዞ መጥቷል” – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፡– ብሪክስ በሁለተናዊ መስኮች አብሮ የማደግን ትልቅ እድል ይዞ መጥቷል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡ ኢትዮጵያ በፍትሃዊነት መርህ ላይ የተመሠረተ ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗንም ጠቁመዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሩሲያ ካዛን ከተማ እየተካሄደ ባለው 16ኛው የብሪክስ መሪዎች ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፤ በብሪክስ ውስጥ ትልቅ አብሮ የማደግ እድል አለ፡፡ ይህን ዕድል አባል ሀገራቱ መካከል በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በቱሪዝም ተጠቃሚ የሚያደርግ የኢኮኖሚ እድገት ይዞ መጥቷል፡፡

ብሪክስ ከዓለም ሕዝብ ግማሽ ያህሉን እንደሚወክል ገልጸው፣ ብሪክስ የለውጥ ሃይል የመሆን አቅም እንዳለውና ፍትሃዊ የዓለም ሥርዓት የሚያሰፍን እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡

ብሪክስ አባል ሀገራቱ መካከል ንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ተጠቃሚ የሚያደርግ የኢኮኖሚ እድገት ማስፈን እንደሚችል የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የተለያዩ ኢኮኖሚዎችንና ከፍተኛ የዕድገት አቅሞችን በመጠቀም ሕዝቦቻችን ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን ማስመዝገብ አለብን ብለዋል፡፡

በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እድገት ውስጥ ትብብርን ማጎልበትም አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለአዲሱ ልማት ባንክ የአባልነት ጥያቄም በፍጥነት እንዲጤንና አማራጭ የፋይናንስ ልዩነትን ለማሻሻልና ለመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች እንደሚረዳ ጠቁመዋል።

ብሪክስ ለፍትሃዊና ውክልና ያለው የባለብዙ ወገንነት ድጋፍን እንደሚያበረታታ በመግለጽ፣ የታዳጊ ሀገራትን ስጋት የሚፈታ ማሻሻያና ድምፃቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲሰማ ማድረግ እንደሚቻልም ተናግረዋል፡፡

የብሪክስ አባል ሀገራት መካከል በማኑፋክቸሪንግ፣ ግብርና፣ ኢነርጂ፣ ቱሪዝምና የመሳሰሉ ዘርፎች ላይ ጠንካራ የኢኮኖሚ ትብብር ሊያደርጉ እንደሚገባ ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ የጋራ ራዕይን ለማሳካት በንቃት ለመሳተፍ ያላትን ቁርጠኝነትንም ገልጸዋል፡፡

የቡድኑ መሪዎች መሰባሰብ ሀገራቱ ዛሬ የሚያጋጥሟቸውን አንገብጋቢ ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ውጤታማ የባለብዙ ወገን ትብብር ተስፋ እንዳለው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ ያደጉትንና በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት መካከል በፍትሃዊነት መርህ ላይ በተመሠረተ መልኩ ለመሳተፍ ዝግጁ ናት ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ አዲስ የብሪክስ አባል እንደመሆኗ በፍትሃዊነት መርህ ያደጉ እና በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ያማከለ ባለብዙ ወገን ትብብር እንዲጎለብት ለማድረግ እንደምትሠራም አመልክተዋል፡፡

ዓለም ጥበብና ማስተዋልን በሚጠይቁ በርካታ ቀውሶች በፍጥነት እየተለወጠች መሆኗን ጠቅሰው፣ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን የምጣኔ ሀብት እድገት የሚፈታተነው ፍትሃዊ ያልሆነ የዓለም የፋይናንስ ሥርዓት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ማዕቀፋችን ውስጥ ያለው አለመመጣጠን የዋጋ ንረት፣ ስራ አጥነትን እየጨመረ መምጣቱ ከምንጊዜውም በላይ የጋራ ጥረቶችን እንደሚጠይቅ በመግለጽ፣ ቀውሱ እየጨመረ በሄደ ቁጥር የአየር ንብረት ርምጃና የአየር ንብረት ፋይናንስ የቀረቡ ጥያቄዎች ችላ እየተባሉ መቀጠላቸውንም ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ማሻሻያ ትኩረት ሊሰጠን የሚገባው መሆኑን እንደምታምን የገለጹት ዐቢይ (ዶ/ር)፣ የጉባዔው ተሳታፊ ሀገራትም አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት የአፍሪካን ውክልና የአፍሪካን የጋራ አቋም በማክበር ቅድሚያ እንደሚሰጥ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

ጥያቄው ውክልና ብቻ ሳይሆን ፍትህ፣ ፍትሃዊነትና ሁሉም ሀገራት ለዓለምአቀፍ አስተዳደር የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ማድረግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት በሶስተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሀገሪቱ ወጣት የሰው ሃይል፣ ሰፊ የእርሻ መሬትና በቂ የታዳሽ ሃይል ሀብት እንዳላትና የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውም አዳዲስ ለውጦችን እያስገኘ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በስድስት ዓመታት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ኢኒሼቲቭ ቀርጻ ዜጎችን ማንቀሳቀሷን በመግለጽ፣ ቀጣይነት ያለውና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ሥርዓት ለመገንባት ቁርጠኛ መሆኑዋን ተናግረዋል፡፡

ከጉባዔው ጎን ለጎን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከተለያዩ የብሪክስ አባል ሀገራት መሪዎች ጋር በሁለትዮሽና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You