ዜና ትንታኔ
የፌዴራል መንግሥት ሀገሪቷ የነበረችበትን የኢኮኖሚ ሁኔታ መሠረት በማድረግ የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን አድርጓል። ማሻሻያው ከፋይናንስና ምንዛሬ፣ ከምርታማነትና ከሥራ እድል ፈጠራ አንፃር መሠረታዊ ለውጦችን ይዞ መምጣቱን የገንዘብ ሚነስቴር ማስታወቁ አይዘነጋም።
ማሻሻያዎቹ በኢኮኖሚ ውስጥ የሚታዩትን ዘርፈ-ብዙ ችግሮች ለመቅረፍ አቅም ያላቸው ቢሆንም ጠንካራ ሥራን የሚጠይቁ መሆናቸው አያጠያይቅም። ማሻሻያውን መሠረት አድርገው ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እና የዓለም ባንክ እስከ ነሀሴ ወር 2016 ዓ.ም ብቻ ሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ማቅረባቸውን ብሔራዊ ባንክ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
በገንዘብ ማሻሻያው ኢኮኖሚውን ወደሚፈለገው ደረጃ ለማድረስ የሚረዱ ምን አይነት ሥራዎች ተከናውነዋል፤ ምንስ ውጤት ተገኝቷል? በግብርና፣ በማዕድን፣ በቱሪዝምና በተለያዩ ዘርፎች የተደረጉ ማሻሻያዎች የኢኮኖሚ ስብራቱን ለማሻሻል ምን አይነት አቅም ፈጥረዋል በሚሉ ጉዳዮች ላይ ምሁራንና የዘርፉ ኃላፊዎች ሃሳባቸውን ሰጥተዋል::
የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምሕረቱ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን በተመለከተ በቅርቡ በሰጡት ማብራሪያ እንዳነሱት፤ ከሀገራዊ ለውጡ በፊት የነበረው የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ኢትዮጵያን ለውጭ ምንዛሬ እጥረትና ለከፍተኛ የብድር ጫና የዳረገ እንዲሁም የግል ሴክተሩን ከብድር አቅርቦት ያገለለ ነበር።
በቀድሞ ጊዜ የነበረው ኢኮኖሚ አካሄድ በዋናነት የመንግሥት ኢንቨስትመንትን መሠረት ያደረገ በመሆኑ የፋይናንስ አቅርቦቱ ጤናማ እንዳልነበረ አንስተው፤ መንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም በመተግበር የኢኮኖሚ ስብራትን ለመጠገን የሚያስችሉ ርምጃዎችን መውሰዱን ይገልጻሉ።
ሕዝብን ተጠቃሚ ለማድረግም ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራ የገቢ አስተዳደርና አሰባሰብ፣ የገንዘብ እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ አስተዳደርን ጨምሮ ሁሉንም ዘርፎች በማስተሳሰር የሚተገበር መሆኑን ጠቁመው፤ የውጭ ምንዛሪ ችግርን በዘላቂነት የሚፈታ ቁልፍ ውሳኔ መሆኑንም ነው ያብራሩት።
በዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ትንበያ ብቻ በቀጣይ አራት ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአማካይ ስምንት በመቶ ያድጋል ይላሉ። በዚህም ሪፎርሙ በገቢ ማሰባሰብ አቅም የሚፈጥር፣ የውጭ ምንዛሬ ክምችት የሚጨምር፣ ኤክስፖርትና ኢንቨስትመንትን ትርጉም ባለው መልኩ የሚለውጥ እንዲሁም የኢኮኖሚ ፍትሃዊነትን የሚያሰፍን እንደሆነ ያመላክታሉ።
ብሔራዊ ባንክ ካደረጋቸው ሪፎርሞች መካከል የውጭ ምንዛሬ ተመኑ በገበያ መወሰኑ ሕገ ወጥነትና ብልሹ አሠራርን በመቅረፍ ኤክስፖርትና ኢንቨስትመንት ለማበረታታት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ያስረዳሉ።
በዚህም የምንዛሬ ተመኑ ወደ ገበያ መር መለወጡ በሸቀጦች ዋጋ ላይ ጭማሪ ሊፈጥር እንደማይገባ ገልጸው፤ ሪፎርሙን ተከትሎ ሕገ-ወጥነትና አሉታዊ ጫና የሚፈጥሩ ጉዳዮች ከተከሰቱ ሕጋዊ ምላሽ ለመስጠት ባንኩ ተገቢውን ዝግጅት ማድረጉንም ይጠቁማሉ።
ማሻሻያው ለኢትዮጵያን የተሻለ የፋይናንስ አቅም እንደፈጠረ አንስተው፤ ከአይኤምኤፍ እና ዓለም ባንክ የተገኘው ድጋፍና ብድርም ለሪፎርሙ ትግበራ እንደሚውል ነው ያስረዱት። አበዳሪ ተቋማቱ የሪፎርም ይዘት ጥራትና የኢትዮጵያን ምርታማነት አቅም በማየት ድጋፍና ብድር መስጠታቸውንም ይገልጻሉ።
ኢትዮጵያ ከሁለቱ አበዳሪ ተቋማት ባሻገር ከተለያዩ አጋር አካላት የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ሳይገድባት ሪፎርሙን ለማስቀጠል የሚያስችል ሀብት ማግኘቷንም ነው ያስታወቁት።
አቶ ማሞ እንደሚያመላክቱት፤ መንግሥት የተለያዩ የፋይናንስ ሕግ ማሻሻያዎችንና አሠራሮችን በመተግበር የሪፎርሙን ውጤታማነት ለማስቀጠልም በትኩረት መሥራቱን ይቀጥላል።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያውና የፓን አፍሪካ ንግድ ምክርቤት ዋና ኃላፊ ክቡር ገና በበኩላቸው፤ ገበያ መር የኢኮኖሚ ሥርዓት ማለት እኛ የማንቆጣጠረው ኃይል ገበያውን ይተምነው ማለት ነው። ይህ ደግሞ አቅም ያለው አካል ብቻ ገበያውን እንዲመራው መፍቀድ ነው ይላሉ።
ማሻሻያው በተለይም የውጭ ምንዛሪን በተመለከተ የኢትዮጵያ ብር በዓለም አቀፍ ግብይት ሥርዓት ውስጥ እንዲንሸራሸር የሚያደርግ ነው ያሉት አቶ ክቡር ገና፤ በዚህም የውጭ ምንዛሬውን እኛ እንድንቆጣጠረው የሚያደርግ አይደለም ሲሉ ይገልጻሉ ።
የቀድሞው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለውጭ ምንዛሬው ለእድገት የሚሆኑ አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች የሚሰጡበት እንደነበር የሚያነሱት አቶ ክቡር ገና፤ እድገት ፈላጊ በሆነችና የኑሮ ውድነት ባለበት ሀገር ገበያ መር የኢኮኖሚ ሥርዓት ውጤታማ ላይሆን የሚችልበት ዕድል ስላለ ቁጥጥሩን ማጠናከር እንደሚገባ ነው ሃሳባቸውን የሰጡት።
በመሆኑም የውጭ ምንዛሬ ቁጥጥር ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አመላክተው፤ በኢኮኖሚው ዘርፍ ያሉ አሠራሮችን በማሻሻል ጠንካራ አካሄድን መከተል እንደሚገባ ያስረዳሉ። በተለይም የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ሊያሳድጉ የሚችሉ አሠራሮችንና ምርታማነትን በማሳደግ እንደሀገር ውጤት ለማምጣት መሥራት እንደሚገባ ይገልጻሉ።
ዳግማዊት አበበ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 13 ቀን 2017 ዓ.ም