ዘንድሮ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና እንደሚቀላቀሉ ይጠበቃል

አዲስ አበባ፡- በዘንድሮ የትምህርት ዘመን ከ 526 ሺ በላይ ተማሪዎች የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ይቀላቀላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የ2017 የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና የመግቢያ መቁረጫ ነጥብን በትናንትናው እለት አሳውቋል።

በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ(ዶ/ር) እንደገለጹት ፤ የመቁረጫ ነጥቡ በ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎችን ታሳቢ ተደርጎ የተሰላ ሲሆን የሚያገለግለውም ለ2017 የሥልጠና ዘመን ብቻ ነው፡፡

በዚህም መሠረት በደረጃ አንድና ሁለት የሚመዘገቡ ሰልጣኞች በአስራ ሁለተኛ ብሄራዊ ፈተና ወንዶች 141 እና ከዚያ በታች፣ ሴቶች 138 እና ከዚያ በታች ያመጡ ናቸው።

ለታዳጊ ክልሎችና አርብቶ አደር አካባቢዎች ለወንዶች 137ና ከዚያ በታች፣ ለሴቶች 134ና ከዚያ በታች፣ ለሁሉም ክልል አካል ጉዳተኞች 124ና ከዚያ በታች ያመጡ መሆኑንም ገልጸዋል።

በደረጃ ሶስትና አራት የሚመዘገቡ በ12ኛ መልቀቂያ ፈተና ወንዶች 142ና ከዚያ በላይ፣ ሴቶች 139ና ከዚያ በላይ ያመጡ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ለታዳጊ ክልሎችና ከአርብቶ አደር አካባቢዎች ለወንዶች 138 እናና ከዚያ በላይ፣ ለሴቶች 135ና ከዚያ በላይ፣ ለሁሉም ክልል አካል ጉዳተኞች 125ና ከዚያ በላይ ያስመዘገቡ ናቸው።

በደረጃ አምስት የሚሰለጥኑ ወንዶች 179ና ከዚያ በላይ፣ ሴቶች 170ና ከዚያ በላይ ያስመዘገቡ ተማሪዎች ሥልጠናውን ለመውሰድ መስፈርቱን የሚያሟሉ ሲሆን ከታዳጊ ክልሎችና ከአርብቶ አደር አካባቢዎች ወንዶች 167ና ከዚያ በላይ፣ ሴቶች 162ና ከዚያ በላይ እንዲሁም ከሁሉም ከልል አካል ጉዳተኞች 154ና ከዚያ በላይ ያስመዘገቡት በደረጃ አምስት ገበተው መሠልጠን እንደሚችሉ ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው በተለያዩ የሥልጠና አይነት ወደ ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ሊገቡ የሚችሉት ሠልጣኞች ብዛት 526 ሺ683 ይሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጹ ሲሆን ከባለፉት ዓመታት ልምዶች በመነሳት በመደበኛ ሥልጠና ተመዝግበው ይሰለጥናሉ ተብለው ከሚጠበቁት ሠልጣኞች መካከልም 30 በመቶ የሚሆኑት በአጫጭር የሥልጠና ፕሮግራም ሊስለጥኑ እንደሚችሉ ታሳቢ መደረጉን አብራርተዋል፡፡

ዶ/ር ተሻለ ከ2016 የትምህርት ዘመን በፊት የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች በዚህ የሥልጠና ዘመን ወደ ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ገብተው መሰልጠን ቢፈልጉ በየሥልጠና ዘመኑ በነበረው የመቁረጫ ነጥብ መስፈርት መሠረት የሚስተናገዱ መሆኑ ገልጸዋል፡፡

መስከረም ሰይፉ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2017 ዓ.ም

Recommended For You