ኮሚሽኑ በበጀት ዓመቱ 8 ቢሊዮን ብር ካፒታል ለማስመዝገብ አቅዷል

አዲስ አበባ፡- በበጀት ዓመቱ 8 ቢሊዮን ብር ካፒታል ለማስመዝገብ ማቀዱን የአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ኢቨስትመንት ኮሚሽን ዕቅድና በጀት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ እናትነሽ ታመነ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጀት እንደገለጹት፤ ኮሚሽኑ በ2017 የሥራ ዘመን በአገልግሎት እና በማምረቻ ዘርፍ ስምንት ቢሊዮን ብር ካፒታል ለማስመዝገብ አቅዷል።

ከተማዋ ላይ ያለው የኢንቨስትመንት ሥራ በአራት ሥራ መስኮች ላይ ያተኮረ ነው ያሉት ወ/ሮ እናትነሽ እነሱም ማኑፋክቸሪንግ ፣ አገልግሎት ፣ የከተማ ግብርና እና ኮንስትራክሽን ናቸው ብለዋል።

የሚሰበሰበውን የገቢ ዕቅድ ለማሳካት በዋናነት ለባለሀብቱ ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት፣ ባለሀብቱ ባለበት ሆኖ ስለ ኢንቨስትመንት መረጃ እንዲኖረው በማድረግ ፣ የኦንላይን አገልግሎት እንዲሰጥ በማድረጉ እንዲሁም ለአገልግሎት ክፍያዎችን በካሽ እና ከፖስት ማሽን በተጨማሪ በቴሌ ብር እና በሲቢኢ ብር እንዲጠቀሙ የማድረግ ሥራ በትኩረት ይሠራል ሲሉ ገልጸዋል።

የሥራ እድል ፈጠራን በተመለከተ ፕሮጀክቶችን ወርዶ በመደገፍ እና በመከታተል ወደ ሥራ እንዲገቡ በማድረግ የተሻለ የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ ለማድረግ እየተሠራ ሲሆን በቴክኖሎጂው ረገድ ደግሞ ተቋሙ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች አብዛኛው በቴክኖሎጂ በመደገፍ የሚሰጡ ናቸው ብለዋል።

በዚህ በጀት ዓመት የኢንቨስትመነት ፈቃድና ፈቃድ ነክ አገልግሎቶችን ኦን ላይን ለማድረግ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸው የመዝገብ ቤትን ዲጂታላይዝ የማድረግ ሥራውም ትኩረት ተሰቶት ወደ ሥራ ተገብቷል ብለዋል።

ኮሚሽኑ ባለሀብቶች የሚያነሱትን ጥያቄ ለመመለስ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ሲሆን ለአብነትም የምንዛሬ እጥረት ያለባቸውን ፍራንኮ ቫሉታ ወይም ቀረጥና ታክስ ከፍለው እንዲያስገቡ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል።

ሌላው የመሥሪያ ቦታ እና ብድርን በተመለከተ ተቋሙ በራሱ የማይፈታቸውን ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ለመሥራት ከተቋማት ጋራ ሰነድ ተፈራርሞ ወደ ሥራ ገብቷል ብለዋል።

በተጨማሪም ባለሀብቶች የሚጠይቁትን የድጋፍ አገልግሎቶት ፈጣን እና ቀልጣፋ በሆነ መንገድ ለመስጠት እና በተደጋጋሚ የሚያነሷቸውን የመሬት እና የብድር ጥያቄዎችን ለመመለስ ትክለኛነቱን ለማረጋገጥ አመራሩ በትክክል መሥሪያ ቦታው ላይ በመሄድ ችግሩን የማጣራት ሥራ እየሠራና እነዚህን ችግሮችን በቀጣይነት ለመፍታት እንዲያመች ከተቋማት ጋር በቅንጅት ለመሥራት ሰነዶች አዘጋጅቶ በመፈራረም ላይ ይገኛል ብለዋል።

ዳግማዊት አበበ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2017 ዓ.ም

Recommended For You