የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በሚቀጥለው ወር ሥራውን ይጀምራል

– 400 ሺህ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን አክሲዮን አላቸው

አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በሚቀጥለው ወር ሥራውን ለመጀመር እየሠራ መሆኑን ገለጸ። 400 ሺህ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን አክሲዮን እንዳላቸውም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ሥራ አስፈጻሚ ጥላሁን እስማኤል (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ወደ ሥራ ለመግባት የሚያስችሉት አብዛኞቹን የዝግጅት ሥራዎች በመጠናቀቃቸው ሌሎች ነገሮች ካላስቆዩ በቀር በሚቀጥለው ወር በይፋ ይጀመራል።

የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያው አስፈላጊ ግብዓቶች ግዢ መፈጸሙንና ቴክኖሎጂው ሙከራ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ሥራ አስፈጻሚው፣ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮችን ለማገበያየት አገናኝ አባላት /ደላሎች/ ያስፈልጋሉ ብለዋል።

አገናኝ አባላት በካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ፍቃድ አግኝተው ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ አባል መሆን እንዳለባቸው በመግለጽ፣ ስለዚህ አንድም ሁለትም አገናኝ አባላት እንደተገኘ ገበያውን በይፋ ማስጀመር እንደሚቻል  ተናግረዋል።

ገበያው አክሲዮናቸው መሸጫ መለወጫ መድረክ መሆኑን ጠቅሰው፣ የአክሲዮን ዋጋን በማቅረብ በሰከንዶች ውስጥ ከየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል፣ ውጪውንም ጨምሮ መግዛትና መሸጥ እንዲችሉ መድረክ ሆኖ እንደሚያገለግል አስረድተዋል።

የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያው ግብ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከየትም ቦታ ሆኖ ባለው አቅም እንዲቆጥብበት ማድረግ ነው ያሉት ጥላሁን (ዶ/ር)፣ አክሲዮን ወደ ፊት ለልጆች ማስተማሪያ አድርጎ ለመሸጥ፣ ውርስ ለማድረግ መቆጠቢያ መንገድ ነው ብለዋል።

ጥላሁን (ዶ/ር) አክለውም፣ ወደ ፊት አክሲዮኖች ኤሌክትሮኒክ እንደሚሆኑ ጠቅሰው፣ ዜጎች መገበያየት ሲፈልጉ በአገናኝ አባል በኩል፣ ከሞባይል አፕሊኬሽን ላይ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ መግዛትና መሸጥ እንደሚችሉ ገልጸዋል።

በሰነድ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ አባል ለመሆን የአባልነት ምዝገባና ሰርተፍኬት እንደሚያስፈልግ በመግለጽ፣ ለኢንቨስተሮች የውስጥ ደንቦችን በማስተማርና በመፈተን ሥልጠናዎችንም በመስጠት አስፈላጊውን መስፈርት ሲያሟሉ የአገበያይነት ፈቃድ እንደሚሰጥም ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት 400 ሺህ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን የባንኮችንና ኢንሹራንስ ኩባንያዎችን አክሲዮን መግዛታቸውን ጠቅሰው፣ ከአሁን ቀደም አክስዮን መሸጥ ለሚፈልግ ሰው የሚያገለግል ማዕከላዊ ገበያ እንዳልነበር ተናግረዋል።

ይህንንም ተከትሎ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ፈቃድ መስጠት የሚያስችል መመሪያ በካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ወደ ትግበራ እንዲገባ መደረጉን ጠቁመዋል።

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2017 ዓ.ም

Recommended For You