በሩብ ዓመቱ 93 ሺህ ዩኒት ደም ተሰብስቧል

አዲስ አበባ፡- በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 93 ሺህ ዩኒት የሚደርስ ደም መሰብሰብ መቻሉን የኢትዮጵያ የደምና ሕብረ ሕዋስ ባንክ አገልግሎት አስታወቀ።

የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ታዬ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 100 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ 93 ሺህ ዩኒት የሚደርስ ደም መሰብሰብ ተችሏል። አፈጻጸሙም ከ90 በመቶ በላይ ይሆናል።

አፈጻጸሙ ከደም ባንክ ደም ባንክ እንዲሁም ከክልል ክልል ይለያያል ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከዚህ ውስጥ 28 ሺህ ዩኒት ደም አዲስ አበባ ውስጥ የተሰበሰበ ነው። አዲስ አበባ፣ ጅግጅጋ፣ ኦሮሚያ አብዛኛው አካባቢ ያሉ ደም ባንኮች ጥሩ ውጤት ያስመዘገቡ ናቸው።

ጥሩ እቅስቃሴ ያሳዩ ደም ባንኮች የበለጠ እዲሠሩ በተወሰነ ምል ዝቅ ያለ አፈጻጸም ያስመዘገቡትንም ወደተሻለ ደረጃ ለማምጣ ሥራዎች እንደሚሠሩ ጠቅሰዋል።

ትምህርት ቤቶች መከፈታቸው ተከትሎ በትምህርት ቤቶች የደም መሰብስብ ሥራ እየተሠራ ነው። በዚህም የተሻለ ውጤት መገኘት መጀመሩን አስታውቀዋል።

ከዓመት ዓመት የማህበረሰቡ ደም የመለገስ ግንዛቤ እየተሻሻለ ነው ያሉት አቶ ሀብታሙ፤ ያለው ሀገራዊ የደም ፍላጎትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። በዓለም ጤና ድርጅት መስፈርት መሠረት የአንድ ሀገር የደም ፍላጎት ተሟላ ተብሎ የሚወሰደው ቢያንስ አንድ በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ደም ሲለግስ ነው።

ከዚህ አንጻር ስናየው ባለፈው ዓመት እንደሀገር የተሰበሰበው 350 ሺህ ዩኒት ደም ነው። ይህም የአጠቃላይ ሕዝቡን ዜሮ ነጥብ 3 በመቶ ብቻ ነው። አጠቃላይ ባህል ሆኖ ሰዎች መጥተው ደም እየለገሱ የሕክምና ተቋማት ፍላጎት የማሟላት ሁኔታ ገና ብዙ መሥራት እንዳለብን የሚያመላክት ነው ብለዋል።

የማህረሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግም መገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ ሌሎችም ባለድርሻ አካላትን ትብብር የሚፈልግ በመሆኑ ሁሉም የየድርሻቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም ጠቀይቀዋል።

አብዛኛው ደም በትምህርት ቤቶች እንደሚሰበሰብ ጠቅሰው፤ ይህን ሥራ ለማጠናከር በቅርቡ 450 ከሚሆኑ የትምህርት ቤት ዳይሬክተሮች ጋር ምክክር ተደርጓል። ለተማሪዎች ግንዛቤ ለመፍጠርም ሥራዎች ይሠራሉ። ከእምነት ተቋማት፣ ከደም ልገሳ ማህበራትና ከሌሎችም ባለድርሻዎች ጋርም በትብብር ይሠራል ብለዋል።

ደም በማጣት ሕይወታቸውን እስከ ማጣት የሚደርሱ ሰዎች አሉ ያሉት አቶ ሀብታሙ፤ ከ18 እስከ 65 እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ፣ በደም ከሚተላለፉ በሽታዎች ነጻ የሆነና ክብደቱ ከ45 ኪሎ በላይ የሆነ ማንኛውም ሰው ደም በመለገስ የሕይወት አድን ሥራ ላይ እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2017 ዓ.ም

Recommended For You