በወላይታ ዞን የወባ ወረርሽኝ እንዳይከሰት የመከላከል ሥራ እየተሠራ ነው

ወላይታ፡- የወላይታ ዞን የወባ በሽታ መከላከል ግብረ ኃይል ወባን ለመከላል የተለያዩ የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን አስታወቀ፡፡ ጥቅምት 5 ቀን 2017 ዓ.ም. በበሽታው አስከፊነትና መቆጣጠሪያ ስልቶች ዙሪያ በሶዶ ከተማ ምክክር አድርጓል፡፡

በሶዶ ከተማ በተደረገው ምክክር ላይ ንግግር ያደረጉት የግብረ ኃይሉና የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ተወካይ አቶ ታምራት በለጠ በዞኑ እየተባባሰ የመጣውን የወባ ስርጭት በጤና ባለሙያዎች፣ በአመራር አካላት፣ በሕዝብና በባለድርሻዎች ተሳትፎ ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንደሚቻል ጠቁመዋል።

በሽታውን ካልተቆጣጠርን የከፋ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል ያሉት ተወካዩ የሕዝቡን ሕይወት ለመታደግ በቁርጠኝነትና በተጠያቂነት መንፈስ መሥራት የሁላችንም ኃላፊነት ነው ብለዋል።

የዞኑ ወባ መከላከል ግብረ ኃይል ፀሀፊና የጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ፀጋዬ ኤካ በበኩላቸው እየተባባሰ የሚገኘውን የአየር ንብረት ለውጥ ተከትሎ በዞኑ እየጨመረ የመጣውን የወባ ስርጭት የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራዎች ግብረ ኃይሉ በትኩረት እንደሚመራ አንስተዋል።

ከህክምና አንፃር የመከላከሉ ሥራ ወጪው እምብዛም መሆኑን ተናግረው በቅድሚያ የወባ ትንኝ መራቢያ ሥፍራዎችን የማፋሰስ እና የማዳፈን ሥራን ጨምሮ የአጎበር አጠቃቀም ማጎልበት በእጅጉ ይመከራል ብለዋል።

የታመመውን ሰው ሙያዊ ሥነ-ምግባር በተላበሰ መልኩ ማከም ሠብዓዊና ሞራላዊ ግዴታ መሆኑን ገልፀው ታካሚዎች ደግሞ ኃላፊነት ከሚሰማው የጤና ተቋም በባለሙያ የታዘዘውን መድኃኒት በአግባቡ እንዲጠቀሙ አቶ ፀጋዬ አስገንዝበዋል።

በመምሪያው በሽታ የመከላከልና ጤና የማጎልበት ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ አቶ አንበሳው ወልዴ ለውይይት ባቀረቡት ጥናታዊ ሰነድ በዞኑ ባለፉት አምስት ዓመታት የወባ ስርጭት እየጨመረ መምጣቱን አመላክተው በ2016 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ የበሽታው ታካሚዎች ቁጥር ከአንድ መቶ ሺህ በላይ መድረሱን ገልፀዋል።

ስርጭቱን ለመግታት የሚያስችል የተቀናጀና ተመጣጣኝ ጥረት ማድረግ ከጤና ባለሙያዎች፣ ከአመራር አካላት፣ ከህብረተሰቡና አጋር ድርጅቶች እንደሚጠበቅም አመላክተዋል።

የአረካ ከተማና የቦሎሶ ቦምቤ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት የአካባቢ ቁጥጥር ከማሳለጥ በተጓዳኝ በአጎበር አጠቃቀም ላይ የሚስተዋሉ ውስንነቶችን ለማረም አቅደው እየሠሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ፈዋሽነቱ ባልተረጋገጠ ሕገ ወጥ የመድኃኒት ዝውውር በሚያከናውኑትና ሙያዊ ሥነ ምግባርን በሚጥሱ ስግብግቦች ላይ ሕጋዊ እርምት እየተወሰደ እንደሚገኝም አመላክተዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2017 ዓ.ም

Recommended For You