በአዲስ አበባ ከተማ የዳቦ ስርጭትና አቅርቦትን ለማስፋት በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ ነው

አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከተማ የዳቦ ስርጭትና አቅርቦትን ለማስፋት በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን የከተማው ንግድ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሰውነት አየለ ለኢፕድ እንደተናገሩት፤ በአዲስ አበባ ከተማ የዳቦ ስርጭትና አቅርቦትን ለማስፋት የከተማ አስተዳደሩ ንግድ ቢሮ ከአቅርቦት ጋር በተያያዘ በሶስት መንገዶች እየሠራ ይገኛል።

በዚህም በከተማዋ በሚገኙ የሸገር ዳቦ የማከፋፈያ ሱቆች፣ በከተማ አስተዳደሩና በባለሀብቶች ጥምረት በተገነቡ 20 የዳቦ ፋብሪካዎች፤ እንዲሁም ከ1 ሺህ 300 በላይ በሆኑ በግል ዳቦ ቤቶች አማካኝነት ዳቦ ለህብረተሰቡ እንዲሰራጭ እየተደረገ ነው ብለዋል።

ከዚህ አኳያ ቢሮው ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ በሸገር ዳቦ፣ በግል ባለሀብቶችና በመንግሥት አጋርነት በተገነቡ ዳቦ ቤቶች አማካኝነት ከ86 ሚሊዮን በላይ ዳቦዎችን ለህብረተሰቡ እንዲሰራጭ መደረጉን ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ ከተማ አስተዳደሩ ድጎማ የሚያደርግባቸው የሸገር ዳቦዎች 70 ግራም እንደሆኑና በአምስት ብር እየተሰራጩ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

እንደ አቶ ሰውነት ገለጻ፤ የመንግስትና የግል ባለሀብቶች በተገነቡ የዳቦ ፋብሪካዎችና በግል ዳቦ ቤቶች አማካኝነት ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ዳቦ ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆን ቁጥጥር እየተደረገ ይገኛል። በዚህም የህብረተሰቡን የዳቦ ፍላጎት ለማሟላት በሸገር ዳቦና በሌሎች አማራጮች በመጠቀም ጥረት እየተደረገ ነው።

በተለይም የሸገር ዳቦዎች አነስተኛ ገቢ ባላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ተመራጭ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ሰውነት፤ በአሁኑ ወቅትም በቀን ከ500 ሺህ እስከ 550 ሺህ ዳቦዎች ተጋግረው ከነዋሪዎች በተጨማሪ ለምገባ ማዕከላትና ለበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች እየተሰራጩ መሆኑን ተናግረዋል።

ዳይሬክተሩ አክለውም፤ እነኚህ ዳቦዎችም በሁሉም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ከ430 በላይ የሸገር ዳቦ መሸጫ ሼዶች አማካኝነት ጠዋትና ማታ ለህብረተሰቡ እየቀረቡ ይገኛል ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ የሸገር ዳቦ መሸጫ ሼዶች አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን ከልማት ጋር በተያያዘ እየተነሱ ያሉም ከሆነ እየተጠና አማራጭ ቦታዎችን በማፈላለግ መልሰው የሚደራጁበት ሁኔታ እንደሚኖር ያመላከቱት አቶ ሰውነት፤ የስርጭት መጠኑንና አቅርቦቱን ለማስፋት የሸገር ዳቦን ከሚያመርተው ኩባንያ እና ምርቱን ተቀብለው ከሚያሰራጩ ወጣቶች ጋር የጋራ መድረኮችን በማዘጋጀት ችግሮች እንዲቀረፉ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

በከተማዋ በሶስቱም አማራጮች በሚቀርቡ ዳቦዎች ላይ ከአቅርቦት፣ ከጥራትና ግራም ጋር በተያያዘ ሰፊ ቁጥጥሮች እየተደረጉ ነው። ለዚህም ዜጎች በከተማዋ በተለያዩ አማራጮች በቂ የዳቦ አቅርቦት በመኖሩ ገዝተው መጠቀም እንደሚችሉ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2017 ዓ.ም

Recommended For You