አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ በሀገርና ከሀገር ውጭ የምታካሂዳቸው የቢዝነስና የኢንቨስትመንት ጉባዔዎች የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትን እያሳደጉ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከኦስትሪያ ኤምባሲ ጋር በመተባበር የኢትዮ- ኦስትሪያ ቢዝነስ ጉባዔን ዛሬ በአዲስ አበባ ያካሂዳል። ጉባዔውን አስመልክቶ በትናንትናው ዕለት በኮሚሽኑ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እና ፕሮሞሽን ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) እና በኢትዮጵያ የኦስትሪያ አምባሳደር ሲሞን ኬናፕ (ዶ/ር) በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
በኮሚሽኑ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እና ፕሮሞሽን ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ዘለቀ (ዶ/ር) ተመስገን እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ከሌሎች ሀገራት ጋር በመሆን የቢዝነስና ኢንቨስትመንት ጉባዔዎችን እያዘጋጀች ነው። በ2016 ዓ.ም ከፓኪስታን፣ ሩሲያ፣ ሳዑዲ፣ ቻይናና ከሌሎች የተለያዩ ሀገራት ጋር በአዲስ አበባና ከኢትዮጵያ ውጭ ማካሄድ ተችሏል።
እንደ ዘለቀ (ዶ/ር) ገለጻ፤ የቢዝነስና የኢንቨስትመንት ጉባዔዎች የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰቱን የመጨመር ዕድል አላቸው። ያለፈው የ2017 ሩብ ዓመት ከ2016 ተመሳሳይ ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ12 በመቶ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ጭማሪ አለው።
የኢትዮ- ኦስትሪያ የቢዝነስ ጉባዔ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመው፤ በጉባዔው ለመሳተፍ ከኦስትሪያ የሚመጡ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ እንዲያለሙ በማድረግ ፍሰቱን ለመጨመር ታሳቢ ተደርጎ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በአይነቱ ለየት ያለ የቢዝነስ ጉባዔ ከኦስትሪያ ጋር ይካሄዳል ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ ትላልቅና ረጅም ዓመት ልምድ ያላቸው ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ነው። ይህም ኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ፍሰትን እንዲሰፋ እያስቻለ ነው። ኮሚሽኑ በውጭ ሀገር በተዘጋጁ ጉባዔዎች ላይ በንቃት በመሳተፍ የተወሰኑ አልሚዎችን መሳብ ችሏል። በ2017 በእቅድ ደረጃ የተያዙ በርካታ የንግድና የቢዝነስ ጉባዔዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
በኢትጵያና በኦስትሪያ መካከል ጠንካራ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት አለ ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ አንድ መቶ ዓመት ያስቆጠረ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ነው። በዲፕሎማሲው ረገድ ያለውን ጠንካራ ግንኙነት በኢኮኖሚ ረገድ መድገም ተገቢ በመሆኑ የቢዝነስና የኢንቨስትመንት ጉባዔው መዘጋጀቱ አስፈላጊ ነው። በጉባዔው የሚሳተፉ ድርጅቶች በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሀገሮች ልምድ ያላቸው መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትምንት መጨመር ብዙ ምክንያቶች አሉ ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ በቅርቡ የወጣው የልዩ ኢኮኖሚ አዋጅ ወደ ሥራ ገብቷል። አዲሱ አዋጁ በሀገር ያሉ ኢንዱስትሪያል ፓርኮችን ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የሚያሸጋግር ሲሆን የማዘዋወር ሥራው ተጀምሯል። ይህ ደግሞ ለሀገርና ለውጭ አልሚዎችምች ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑን አብራርተዋል።
ባለፈው ሳምንት አራት ድርጅቶችን ከኢንዱስትሪ ፓርክ ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን እንዲሸጋገሩ ማድረግ መቻሉን በመጥቀስ የተደረገው የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ማሻሻያ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መጨመር ሌላው ምክንያት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የኦስትሪያ አምባሳደር ሲሞን ኬናፕ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የቢዝነስ ጉባዔው ለሁለቱም ሀገራት ትልቅ ጠቀሜታ አለው። ኢትዮጵያና ኦስትሪያ ረጅም ጊዜን ያስቀጠረ የዲፕሎማሲ ግንኙነት አላቸው። በቅርብ ጊዜ ደግሞ በንግድ ዘርፍ ያላቸው ግንኙት መጠናከሩን ጠቅሰዋል።
ግንኙነቱ አንድ መቶ ዓመትን የተሻገረ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ የኦስትሪያ ኤምባሲ የተከፈተበትን 60ኛ ዓመት እንደሚከበርም ጠቅሰዋል።
የኦስትሪያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች መሰማራት ይፈልጋሉ ያሉት አምባሳደሯ፣ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱን አስመልክቶ የኦስትሪያ አልሚዎች በኢትዮጵያ እንዲያለሙ ለማድረግ የቢዝነስ ጉባዔ ተዘጋጅቷል። የኦስትሪያ ባለሀብቶች ኩባንያዎቻቸውን በኢትዮጵያ የማስፋት እቅድ አላቸው፤ ቢዝነስና የንግድ ጉባዔ ለአልሚዎች ትልቅ እድል ይፈጥራሉ። የኢንቨስትመንት ማሻሻያዎችና መንግሥት እየተገበረ ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለአልሚዎች ትልቅ እድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
ሞገስ ጸጋዬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 12 ቀን 2017 ዓ.ም