ከአፍሪካ ቀንድ ጀርባ የሚሸረቡ ሴራዎች

ዜና ትንታኔ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግብፅ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ እያደረገች ያለችው እንቅስቃሴ አዲስ የችግር አረንቋ የሚወልድ ስለመሆኑ ለመገመት አያዳግትም። በተለይ ኢትዮጵያ ከሶማሌ ላንድ ጋር ያደረገችውን የባህር በር ስምምነት ተከትሎ ሶማሊያ በኢትዮጵያ ላይ ተደጋጋሚ ክስ ማቅረቧን ተከትሎ ግብጽ የሶማሊያ ወዳጅ በመምሰል ነገሩን ለማባባስ ሌት ተቀን መሥራት ላይ ትገኛለች።

በነሐሴ ወር 2016 ዓ.ም. ግብፅ ከሶማሊያ ጋር ያደረገችው የጦር ስምምነት ሳያንስ ሁለተኛውን የሶስትዮሽ ስምምነት ከሶማሊያና ኤርትራ ጋር በቅርቡ መስርታለች። ይህ አካሄድ መብት ቢሆንም ከዚህ በስተጀርባ ያለው ፍላጎት ግን ሌላ ስለመሆኑ ጸሃይ የቀሞቀው ሀቅ ነው። በተለይም የግብፅ ድጋፍ ወታደራዊ ትብብር ወይስ ሕገ-ወጥ የመሣሪያ ዝውውር የሚለው ለቀባሪ ማርዳት አይነት መሆኑ ነው።

የራሷ አሮባት የሌላውን ታማስላለች ነውና ነገሩ ሶማሊያም ብትሆን ያለባትን የውስጥ ችግር ከመፍታት ይልቅ ዳር ቆመው እሰይ አበጀሽ በሚሏት ድምጾች ተሸብባ ካፈርኩ አይመልሰኝ ብላለች። ምን ይሄ ብቻ ‹‹ሽሽታቹ በክረምትና በጭቃ አይሁን›› የሚለውን የፈጣሪ ቃል የዘነጋችም ትመስላለች። በዚህም ታዲያ የግብፅን የእውር ድንብር ጉዞ ደግፋ ሀገሯን ይበልጥ ወደ ለየለት ቀውስ ውስጥ እያስገባች ትገኛለች።

ይህ አካሄድም ታዲያ ለአፍሪካ ቀንድ ስጋት መሆኑን የዘርፉ ሙሁራን ያብራራሉ። ከሁሉ የሚገርመው ይላሉ ሙሁራኑ የአፍሪካ ህብረትም ሆነ ኢጋድ በጉዳዩ ዙሪያ ዝምታን መምረጣቸው ጉዳዩን አሳሳቢ ያደርዋል።

በዲላ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስና የሥነ-ሠብ ኮሌጅ መምህርና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና የኤሲያ ጥናት ሶስተኛ ዲግሪ ተማሪ ዳዊት መዝገበ ጸጋዬ ለኢፕድ በሰጡት ቃል፤ የጠላቴ ጠላት በሚል ግብፅ ከሶማሊያ ጋር እያደረገችው ያለው ስምምነት የሶማሊያን መንግሥት ፍላጎት የሚያሟላ ሳይሆን የግብጽን ቀጣናዊ የማተራመስ ፍላጎት ለማሳካት ያለመ ነው ይላሉ።

ግብፅ ለሶማሊያ የምታደርገው ድጋፍ አልሸባብን ከማስታጠቅም በላይ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር ነው የሚሉት መምህር ዳዊት፤ በዓለም ላይ የሚገኙ አሸባሪዎች ካላቸው ትስስር አንጻር ጦሱ ለአፍሪካ ቀንድ ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም የሚተርፍ መሆኑን ይናገራሉ።

የግብፅ ዓላማ በዲፕሎማሲ ከሚያምንና የመንግሥት ቅርፅ ካለው አካል ይልቅ አልሸባብን እንዲሁም መሰል አሸባሪዎችን አስታጥቃ ለራሷ ጥቅም ለማዋል መሆኑን ያክላሉ።

ግብጽ ለሶማሊያ እያስታጠቀችው ያለው መሣሪያ ለአልሸባብ ተጨማሪ አቅም መፍጠር የሚችል ስለመሆኑም ያስረዳሉ። በዓለም ላይ እየተካሄዱ ባሉ ጦርነቶች ኃያላን ሀገራት ድጋፍ የሚያደርጓቸው መሣሪያዎች የት እንደሚገቡ ኦዲት ባለመደረጉ የአሸባሪዎች መበራከት ለዚህ ማሳያ ነው።

እንደ መምህር ዳዊት ገለጻ፤ በ1990ዎቹ ከሲያድባሬ ውድቀት ጀምሮ የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ኢትዮጵያ ትልቁን ሚና ተጫውታለች። የአፍሪካ ቀንድ የጦር መሣሪያ እጥረት የለበትም፤ ለቀጣናው የሚቆረቆር አካል መሠረተ ልማት እንጂ መሣሪያ መስጠት ትክክል እንዳልሆነ ይታወቃል።

ግብጽ ከአረብ ሀገራት የበለጠ ለአፍሪካ ትኩረት ሰጥታ አታውቅም የሚሉት መምህር ዳዊት፤ በአፍሪካም ሆነ በአፍሪካ ቀንድ ሰላም ማስከበር አለመቻሏ ብቻ ሳይሆን ሌሎች በየጊዜው መስዋዕትነት ሲከፍሉ የነበሩ ጎረቤት ሀገራት የት ሄደው ነው ሲሉም ይጠይቃሉ።

መምህር ዳዊት፤ በተለይ አፍሪካ የጸጥታው ምክርት ቤት አባል አለመሆኗ በአህጉሪቱ ባላንጣነት እየተስፋፋ መሆኑን ጠቅሰው፤ቀጣናው በባህል፣ በቋንቋ እንዲሁም በሃይማኖት የሚያገናኛቸው በርካታ ጉዳይ በመኖሩ ከጦርነት ይልቅ ዲፕሎማሲው የበለጠ ዘላቂ ውጤት የሚያመጣ መሆኑን ያብራራሉ።

በግብፅ እንቅስቃሴ ዙሪያ የአፍሪካ ህብረት ድክመት አለ ያሉ ሲሆን ግብጽ አፍንጫዋ ስር ያለውን ሰላም ማስከበር ሳትችል ወደ አፍሪካ ቀንድ መጥታ ሰላም ላስከብር ስትል በዝምታ ሊታለፍ አይገባም ባይ ናቸው።

በተጨማሪም ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ በሚለው መርህ ዲፕሎማሲ ፈጥሮ መፍትሔ መስጠትና ሕጋዊ ርምጃ መውሰድ የሚያስፈልገውን ደግሞ ሕጋዊ ርምጃ መውሰድ እንዳለበት ይናገራሉ።

የግብፅ እንቅስቃሴ ለአየር መንገዶችና የባህር ላይ ንግዶች ላይ ከፍተኛ ሳንካ የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ ለሕገ-ወጥ የሰዎች፣ ንግድ፣ ገንዘብና የመሣሪያ ዝውውር መናኸሪያ ለሆነችው ሶማሊያ ተጨማሪ ስጋት የሚጭር ነው።

የኢንቴራክሽን ፎር ቼንጅ ኢን አፍሪካ ዳይሬክተር ወርቁ ያዕቆብ (ዶ/ር) በበኩላቸው ግብፅ ለሶማሊያ መንግሥት የምታደርገውን የጦር መሣሪያ ድጋፍ ለአልሸባብ ተጨማሪ ጉልበት ይሆናል የሚል ግምት ባይኖራቸውም በሶማሊያና ኢትዮጵያ መካከል ያለው ውጥረት የበለጠ የሚያባብሰው እንደሆነ ይጠቁማሉ።

ግብፅ፣ ሶማሊያና ኤርትሪያ በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ አብረው መሥራታቸው በራሱ ምንም ዓይነት አንደምታ ባይኖረውም በተለይ ከዚህ በፊት ያልተለመዱ የጦር መሣሪያ ስምምነቶችና ኢትዮጵያና ሶማሊያ ውዝግብ ውስጥ በገቡበት ወቅት መሆኑ የፖለቲካ ቁማር እንዳለ እንደሚጠቁም ያብራራሉ።

እንደ ዶክተር ወርቁ ገለጻ፤ ጠብታ የዓባይን ውሃ በብቸኝነት የመቆጣጠር ፍላጎት ያላት ግብፅ ፍላጎቷ ከዚህ ቀደም በነበረው ዲፕሎማሲ መንገድ ማሳካት ሲሳናት ቀጣናውን በማተራመስ የጀመረችው የፖለቲካ ቁማር ነው። የግብፅ ሌላኛው ዓላማ በውክልና ጦርነት የኢትዮጵያ መንግሥት ኃይል ተዳክሞ ህዳሴ ግድብ ላይ ያለውን ትኩረት እንዲቀንስ ለማድረግ ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት ቆም ብሎ ውሳኔዎችን በጥንቃቄ ከወሰደ እንዲሁም ስለጉዳዩ በቂ ግንዛቤ መፍጠር ከቻለ የሦስቱ ሀገራት ስምምነት የሚያሳድረው ጫና የለም።

የግብፅ አጀንዳ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመዝጋት የህዳሴ ግድብ በሁሉም ዘርፎች በሙሉ አቅሙ ወደ ምርት እንዲገባና ኤሌክትሪክ የሚወስዱ ሀገራት በሙሉ አቅም እንዲሰጥ ማድረግ ተገቢ ነው የሚሉት ዶክተር ወርቁ፤ የህዳሴው ግድብ ይጠናቀቃል በተባለው ጊዜ ባለመጠናቀቁ ለግብፅ የፖለቲካ ቁማር በር ከፍቶ መቆየቱን ተናግረዋል።

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You