ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የግብርና ዘርፉን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ትገኛለች። በተለይም የዜጎቿን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ፤ ዘርፉ የሚያስገኘውን የውጭ ምንዛሬ ገቢ ለማሳደግ ትኩረት ሰጥታ ስትሰራ ቆይታለች። በዚህም ምርትና ምርታማነት እያሳደገች መጥታለች።
ለእዚህ ምርትና ምርታማነት እድገት አስተዋጽኦ ካደረጉት መካከል የኩታ ገጠም እርሻ መስፋፋት አንዱ መሆኑ ይጠቀሳል። የዚህ የኩታ ገጠም እርሻ አስፈላጊነት የእርሻ ሥራውን በሜካናይዜሽን የታገዘ ማድረግ እንደመሆኑ እርሻው በሜካናይዜሽን እንዲታገዝ ማድረግ ከተጀመረ ወዲህ በግብርናው ዘርፍ ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ ችላለች።
በግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ እምርታ ካሳዩ ክልሎች መካከል ደግሞ የኦሮሚያ ክልል አንዱ ነው። የክልሉ መንግሥት ለግብርና ዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት በየዓመቱ የሚታረሰው መሬትም ሆነ የሚለማው የሰብል ዓይነት በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል። በዋናነትም ኩታ ገጠም እርሻ እንዲስፋፋ በመደረጉ የአርሶ አደሩ ምርታማነት እየጎለበተ መጥቷል።
የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ በቅርቡ የ2016/17 የምርት ዘመን የክልሉን የግብርናው ዘርፍ እቅድ አፈፃፀም ያለበትን ሁኔታ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ እንደገለፁት፤ በክልሉ በምርት ዘመኑ ከየትኛውም ጊዜ በላቀ ምርታማነትን ለማሳደግ ሰፊ እንቅስቃሴ ተደርጓል። ‘’ከተረጂነት ወደ ምርታማነት’’ የሚለውን ሀገራዊ አቅጣጫ በመከተል በዘንድሮው የመኸር እርሻ በመሬት ሽፋንም ሆነ በምርት ከፍተኛ ለውጥ ለማምጣት እየተሰራ ነው። በተለይም በመኸር እርሻ በክልሉ 10 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ ሰፊ እንቅስቃሴ የተደረገ ሲሆን፣ 11 ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በተለያዩ አዝዕርት ዓይነቶች ዘር በመሸፈን ከእቅድ በላይ መፈፀም ተችሏል። ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ16 ነጥብ ሰባት በመቶ ብልጫ አለው።
‹‹ለእቅዳችን መሳካትም በተለይም ደግሞ ኢኒሼቲቮች ላይ ከፍተኛ የሆነ ትኩረት ሰጥተን መሥራታችን የላቀ አስተዋፅኦ አበርክቷል›› የሚሉት ኃላፊው፤ በእርሻውም ሆነ በእንስሳት እርባታ ዘርፍ በክላስተር በመሥራቱ ከፍተኛ ውጤት እየተገኘ ስለመሆኑ ያስረዳሉ። ‹‹ከዚህ አኳያ ዘንድሮ በምርት እንሸፍናለን ብለን ካቀድነው ውስጥ ስምንት ሚሊዮን 651 ሺ ሄክታር የሚሆነውን መሬት በክላስተር በመሸፈን ከእቅድ በላይ አሳክተናል›› በማለትም ተናግረዋል። ይህም አጠቃላይ በምርት ከተሸፈነው መሬት 78 በመቶ የሚሆነውን በክላስተር መሸፈን እንዳስቻለ ያስገነዝባሉ።
የኩታ ገጠም እርሻ መስፋፋቱ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር እንደሚያደርግ ያለፉት ዓመታት የክልሉ ተሞክሮ እንደሚያሳይ ተናግረው፤ ‹‹ምክንያቱም ደግሞ በክላስተር የተሰሩ እርሻዎች የቴክኖሎጂ፣ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ አጠቃቀማቸው የተሻለ በመሆኑ ምርታማነትም በዚያው ልክ የሚጨምር በመሆኑ ነው›› ሲሉ ያስረዳሉ።
ዘንድሮም 78 በመቶ የሚሆነው መሬት በክላስተር በመታረሱ ምርታማነቱ የተሻለ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ ያመለክታሉ። በምርት ዘመኑ በክልሉ 337 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ በሁሉም ዞኖች ላይ ከፍተኛ ዝናብ በመጣሉና አርሶ አደሩም ከፍተኛ ርብርብ በማድረጉ እቅዱ ሊሳካ እንደሚችል ነባራዊ ሁኔታው እንደሚያሳይ አቶ ጌቱ ይጠቁማሉ። ተባይና አረምን የመከላከሉ ሥራም በባለሙያ እየተመራ በመሰራት ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
‹‹እነዚህን ሥራዎች ስናከናውንም በዋናነት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ሰፊ እንቅስቃሴ አድርገናል›› ያሉት ኃላፊው፤ ለዚህም ቅድሚያ ሊያገኙ የሚገባቸው የእህል ዓይነቶች ላይ ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱን ያስረዳሉ። በተጨማሪም ከውጭ የሚገቡትን ምርቶች በሀገር ውስጥ ለመተካት እንደ ክልል እየተሰራ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል። ወደ ውጭ የሚላከውንም ምርት ለመጨመርና በዘርፉ የሥራ እድል ለመፍጠር ርብርብ እየተደረገ መሆኑም ያስገነዝባሉ።
የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡ ተብለው በኢኒሼቲቭ ከተለዩ ሰብሎች አንዱ በቆሎ መሆኑን አቶ ጌቱ ጠቅሰው፤ ‹‹በክልላችን የበቆሎን ምርት በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ ሰፊ እንቅስቃሴ አድርገናል፤ በዚህም አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በበቆሎ እንሸፍናለን ብለን አቅደን ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት መሸፈን ችለናል›› ሲሉ አብራርተዋል። በተመሳሳይም በኢኒሼቲቩ የክልሉን የዘንጋዳ ምርት ለመጨመር ትኩረት መደረጉን ይጠቁማሉ። በተለይም ቆላማና ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች ላይ የውሃ እጥረትን ሊቋቋሙና ቶሎ ሊደርሱ የሚችሉ የዘንጋዳ ዝርያዎችን በመለየት አንድ ሚሊዮን ሄክታር በእነዚህ ዝርያዎች ለመሸፈን ታቀዶ አንድ ነጥብ 40 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘንጋዳ ዘርፍ የሸፈንበት ሁኔታ መኖሩን ያስረዳሉ።
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ ከውጭ የሚገቡትን የግብርና ምርቶች በሀገር ውስጥ ለመተካት ከተለዩ ሰብሎች መካከል ስንዴ ዋነኛው ነው። በዚህ መሰረት ባለፈው የምርት ዘመን በክልሉ በተለይም በበጋ መስኖ ሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን የሚሆነውን ሄክታር መሬት በስንዴ ዘር እንዲሸፈን ተደርጓል። ይህንን እምርታ በማየትም በ2016/17 መኸር ወቅት 3 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በስንዴ ለመሸፈን ታቅዶ ሦስት ሚሊዮን 165 ሺ ሄክታር መሬት ማልማት ተችሏል።
በሌላ በኩልም ኢትዮጵያ የቢራ ገብስ ከውጭ ሀገራት ታስገባ እንደነበር አስታውሰው፤ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ግን በሀገር ውስጥ አቅም ለማምረት ታቅዶ የተጀመረው ሥራ ውጤት እያመጣ መሆኑን ይናገራሉ። በተለይም የኦሮሚያ ክልል ሥነ-ምህዳር የቢራ ገብስን በስፋት ለማምረት የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህንን ማዕከል ያደረገ ሥራ መሰራቱንም ገልጸዋል። ‹‹ዘንድሮ 500 ሺ ሄክታር መሬት ላይ የቢራ ገብስ እንዘራለን ብለን አቅደን 528 ሺ ሄክታር መሬት ላይ የቢራ ገብስ መዝራት ችለናል። በአሁኑ ወቅትም ሰብሉ በጥሩ አቋም ላይ ይገኛል›› ብለዋል።
በተመሳሳይ ከውጭ የሚገባውንም ሩዝ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የክልሉ መንግሥት ትኩረት ከሰጠባቸው ሥራዎች አንዱ መሆኑን ያስረዳሉ። ለዚህም ይረዳ ዘንድ በአማራ ክልል ፎገራ እየለማ ካለው የሩዝ እርሻ ተሞክሮ መወሰዱን ያስገነዝባሉ። ‹‹በዚህ መነሻም ዘንድሮ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን የሚሆነውን መሬት በሩዝ ለመሸፈን አቅደን ስንሰራ ቆይተን አንድ ሚሊዮን 918 ሺ ሄክታር መሬት ማልማት ችለናል›› በማለት ይገልፃሉ።
እንደ አቶ ጌቱ ማብራሪያ፤ የክልሉ መንግሥት ከውጭ የሚገቡትን ሰብሎች በሀገር ውስጥ ለመተካት ከያዛቸው የዘይት እህሎች መካከል አኩሪ አተር አንዱና ዋነኛው ነው። ዘንድሮም 600 ሺ ሄክታር መሬት በአኩሪ አተር ለመሸፈን ታቅዶ 603 ሺ ሄክታር ለምቷል። በተጨማሪም ከዚህ ቀደም እምብዛም ትኩረት ተሰጥቶ ያልነበረውን የለውዝ ሰብል ለማስፋፋት ርብርብ ተደርጓል። በዚህም 500 ሺ ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ 518 ሺ ሄክታር የሚሆነውን መሬት በለውዝ ዘር በመሸፈን ከእቅድ በላይ ማሳካት ተችሏል። በተመሳሳይ 200 ሺ ሄክታር መሬት ላይ ሱፍ ለማልማት ታቅዶ 180 ሺ ሄክታር መሬት ተሸፍኗል።
‹‹ከዚህ ባሻገር ወደ ውጭ በሚላኩ ሰብሎች ላይ በዚሁ መጠን ሰፋፊ ሥራዎች ስንሰራ ነበር›› የሚሉት አቶ ጌቱ፤ ከዚህም ውስጥ ቦሎቄ ትልቁን ስፍራ እንደሚይዝ፤ ይህም የሆነው በውጭ ሀገራት ገበያ በስፋት ተፈላጊ በመሆኑ እንደሆነ ያስረዳሉ። በዚህ መሰረትም የክልሉ መንግሥት ዘንድሮ አንድ ሚሊዮን በሚሆን ሄክታር መሬት ላይ ቦሎቄ ለመዝራት አቅዶ፣ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች እንቅስቃሴ ማድረጉንና አንድ ሚሊዮን 81 ሺ ሄክታር መሬት ማልማት መቻሉን ያመለክታሉ። ‹‹በዚሁ ልክ በተለይም ወደ ቆላማው አካባቢ 500 ሺ ሄክታር መሬት በሰሊጥ እንሸፍናለን፤ 300 ሺ 112 ሄክታር መሬት በማሾ ለመሸፈን እየሰራን ነው›› ሲሉም ያብራራሉ።
እንደ ኃላፊው ገለፃ፤ የክልሉ መንግሥት በምርት ዘመኑ በኢኒሼቲቭ የያዛቸውን የልማት ግቦች ለማሳካት ያስችለው ዘንድ የግብዓት አቅርቦት ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ ተንቀሳቅሷል። ከፌዴራል መንግሥትና ግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለግብርና ልማቱ ወሳኝ የተባሉ ግብዓቶች በወቅቱ ተደራሽ እንዲሆኑ የተቀናጀ ጥረት አድርጓል። በዋናነትም የኬሚካል ማዳበሪያ በአፋጣኝ ከውጭ ሀገር ተገዝቶ ለአርሶ አደሮቻችን በመቅረቡ የልማት ሥራውን በወቅቱ ለመጀመር ተችሏል። እንደ ክልልም የኬሚካል ማዳበሪያም ሆነ የተፈጥሮ ማዳበሪያ /ኮምፖስት/ በማምረት ለአርሶ አደሮቹ ለማቅረብ ሰፊ እንቅስቃሴ ተደርጓል።
በዚህ መሠረትም ስምንት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ኩንታል የሚሆን ኬሚካል ማዳበሪያ ለስምንት ነጥብ 64 ሚሊዮን አርሶ አደሮች ማድረስ መቻሉን ያመለክታሉ። ይህም ካለፉት ዓመታት አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ እምርታ የታየበት መሆኑንም ያስረዳሉ። ‹‹የቀረበውን ማዳበሪያ ደግሞ በትክክልም አርሶ አደሮቻችንን የማዳበሪያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ተሰርቷል፤ በኤሌክትሮኒክ ሲስተም ለአርሶ አደሮቻችን ሥርጭቱ እንዲካሄድ ያደረግንባቸው ሁኔታዎችም አሉ። በእዚህም ከዚህም በፊት ሥርጭት ላይ የነበሩት ጉድለቶች በዚህ የምርት ዘመን እንዲፈቱ ተደርጓል›› ይላሉ።
በሌላ በኩል በእንስሳቱ ዘርፍ ላይም ምርታማነት እንዲጨምር ሰፊ እንቅስቃሴ መደረጉን አቶ ጌቱ አመልክተዋል። ‹‹በተለይም በሰው ሠራሽ ዘዴ የማዳቀል ሥራዎች ከጀመርን ወዲህ ትልልቅ ውጤቶችን ማገኘት ተችሏል፤ በዘንድሮ የምርት ዘመን ደግሞ አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን የሚሆኑ ጊደሮችና ላሞችን በሰው ሠራሽ የማዳቀል ዘዴ ማዳቀል ችለናል›› ሲሉም ይጠቅሳሉ።
በዶሮ እርባታ ረገድም የአንድ ቀን ጫጩቶችን በማቅረብ ሥራ ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራቱን ይጠቅሳሉ። በዚህም መሠረት በምርት ዘመኑ 53 ሚሊዮን የሚሆኑት የአንድ ቀን ጫጩቶች ለአርሶ አደሮች ለማድረስ መቻሉን ያስረዳሉ። በተጨማሪም ዘመናዊ ቀፎ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ በማድረግ የክልሉን የማር ምርት በመጠንም ሆነ በጥራት ለማሳደግ ርብርብ መደረጉን ያመለክታሉ። ‹‹በምርት ዘመኑ አንድ ሚሊዮን 31 ሺ ዘመናዊ ቀፎዎችን በማሰራጨት አርሶ አደሮቻችን ተጠቃሚ ማድረግ ችለናል›› ይላሉ።
በምርት ዘመኑ ትልቅ ትኩረት ከተሰጣቸው ሥራዎች አንዱ የቡና ልማቱን በከፍተኛ ደረጃ ማስፋፋት እንደሆነም ይናገራሉ። ‹‹በተለይም በቡና ችግኝ ዝግጅት ላይ በ2016 ክረምት በከፍተኛ ደረጃ ተረባርበናል፤ በዚህም ሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን የቡና ችግኞችን በማዘጋጀት ለአርሶ አደሩ እንዲሰራጩና እንዲተክሉ ተደርጓል›› በማለት ያስረዳሉ። የተተከሉት የቡና ችግኞች ፍሬያማ እንዲሆኑ አስፈላጊውን የባለሙያና የቴክኖሎጂ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ያመለክታሉ።
በተመሳሳይ እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር የሻይ ቅጠል ልማት እምብዛም ትኩረት ሳይሰጠው መቆየቱን አስታውሰው፤ ‹‹ዘንድሮ በተለየ መልኩ 413 ሚሊዮን የሻይ ቅጠል ችግኞች አዘጋጅተን በ30 ሺ ሄክታር መሬት ላይ ለመትከል አቅደን እየሰራን ነው›› ሲሉም ይገልፃሉ። ከዚህ እቅድ በመነሳትም ባለፈው ክረምት 58 ሚሊዮን ችግኞች በአራት ሺ ሄክታር መሬት ላይ ለመትከል መቻሉን ያስገነዝባሉ። ይህም የክልሉን ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገርም ያለውን የሻይ ቅጠል ማሳ መጠን በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳድገው መሆኑን ይጠቁማሉ። በቀጣይም የክልሉ ግብርና ቢሮ በበጀት ዓመቱ በሻይ ልማት የተያዘውን ግብ ለማሳካት ርብርብ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
እንደ አቶ ጌቱ ማብራሪያ፤ በምርት ዘመኑ ለተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራም ትልቅ ትኩረት ከተሰጠባቸው የልማት ሥራዎች ዋነኛው ነው። እንደ ሀገርም እየተተገበረ ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከግቡ እንዲደርስ የተቀናጀ ጥረት ተደርጓል። በተለይም ደግሞ የአንድ ቀን የችግኝ ተከላ ከፍተኛ ስኬት የተገኘበት ሲሆን፣ ከዚህ አንፃር ባለፈው ክረምት አምስት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ችግኞችን በአንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ በመትከል ውጤታማ ሥራ ተሰርቷል። የችግኞች የጽደቀት ሁኔታን በተመለከተም ሲያብራሩ፣ እስከ አሁን ባለው ሁኔታ የጽድቀት መጠኑ ወደ 92 በመቶ ደረጃ ላይ መድረሱን መረጃችን ዋቢ አድርገው ገልጸዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ እንደ አጠቃላይ በምርት ዘመኑ በክልሉ የተከናወኑ ሥራዎች ከፍተኛ እምርታ የታየባቸው ሲሆኑ፣ ምርቱ ተሰብስቦ ወደ ጎተራ እስከሚገባ ድረስ አስፈላጊው ክትትልና ድጋፍ የሚደረግ ይሆናል።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም