አገልግሎቱ የገበያ ድርሻውን 50 በመቶ ከሀገር ውስጥ አምራቾች የመሸፈን ፍላጎት አለው

አዲስ አበባ፦ በሶስት ዓመታት ውስጥ 50 በመቶ የመድኃኒት አቅርቦት የገበያ ድርሻውን ከሀገር ውስጥ አምራቾች ለመሸፈን ፍላጎት እንዳለው የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት አስታወቀ።

የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታሪኩ በላቸው ለኢፕድ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ጥራታቸው የተረጋገጡ መድኃኒቶችና የህክምና መገልገያዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ቀጣይነት ባለው መልኩ ለጤና ተቋማት ያቀርባል።

በአገልግሎቱ ስትራቴጂክ እቅድ መሰረት ለሀገር ውስጥ መድኃኒት አምራቾች 60 በመቶ የገበያ ድርሻ ለመስጠት ታቅዷል ያሉት አቶ ታሪኩ፤ የተያዘው ዓመትን ጨምሮ በሶስት ዓመት ውስጥ የሀገር ውስጥ መድኃኒት አምራቾች የአገልግሎቱን 50 በመቶ የገበያ ድርሻ እንዲሸፍኑ ፍላጎት መኖሩን ተናግረዋል።

አሁን ላይ አገልግሎቱ ለጤና ተቋማት ከሚያቀርበው መድኃኒቶች ውስጥ 30 በመቶ የሚሆነው የገበያ ድርሻ በሀገር ውስጥ መድኃኒት አምራቾች እየተሸፈነ መሆኑን የገለጹት አቶ ታሪኩ፤ ይህን ወደ 50 በመቶ ለማሳደግ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከመድኃኒት አምራቾችና አስመጪዎች ማህበር እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሆነ አንስተዋል።

የዕቅዱ ዋና ዓላማ ከውጭ በሚገቡ መድኃኒቶች ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ እና የሀገር ውስጥ ምርትን ለማሳደግ እንዲሁም አምራቾችን ለማበረታታት ነው ብለዋል።

አቶ ታሪኩ እንደተናገሩት፤ውጥኑ የሀገር ውስጥ የመድኃኒት አምራቾች በገቢ ደረጃ እንዲሻሻሉና ከዓለም አቀፍ የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች ጋር በብቃት እንዲወዳደሩ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።

ለሀገር ውስጥ የመድኃኒት አምራቾች 50 በመቶ የገበያ ድርሻ ማግኘት ለሀገሪቱ በርካታ ጥቅሞችን ያስገኛል ያሉት አቶ ታሪኩ፤ ከእነዚህም መካከል ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ፣ ለስራ እድል ፈጠራ፣ በተመጣጣኝ ዋጋ መድኃኒቶችን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚረዳ አስረድተዋል።

ባለፉት ዓመታት ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የአገልግሎቱ የመድኃኒት ግዢ የሚፈጸመው ከውጭ ሀገራት ነው ያሉት አቶ ታሪኩ በላቸው፤ ይህም የሀገር ውስጥ መድኃኒት አምራቾች በሀገሪቱ የመድኃኒት አቅርቦት ገበያ ላይ ያላቸው ድርሻ ዝቅተኛ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።

መድኃኒቶችን ከውጭ ሀገራት ገዝቶ ለማምጣት የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንደሚያጋጥም ጠቁመው፤ አምራቾቹ ከቻይና፣ ከህንድና ከተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት በመሆናቸው ትራንስፖርት ላይ ተግዳሮቶች ያጋጥማሉ ሲሉ አንስተዋል። በተለይ መድኃኒቶች በድንገተኛና በወረርሽኝ ጊዜ በሚፈለገው ፍጥነት ለማድረስ አስቸጋሪ መሆኑን ገልጸዋል።

አገልግሎቱ በጤና ሚኒስቴር አስተባባሪነት እነዚህን ችግሮች ለመፍታትና የሀገር ውስጥ አምራቾችን ለማበረታታት በርካታ ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመዋል። በተለይም መመሪያዎችን የማሻሻል ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውም ለሀገር ውስጥ መድኃኒት አምራቾች የውጭ ምንዛሪ ግኝት ጠቀሜታ እንዳለው አመላክተዋል። አገልግሎቱ በየዓመቱ በቢሊዮን ብሮች የሚገመቱ የመድኃኒት ግዢ እና ስርጭት ስራዎችን ያከናውናል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You