አዲስ አበባ፡- በአርሶ አደሮች የአደጋ ቅነሳ ፕሮጀክት ከ160 ሺህ በላይ አርብቶ አደሮች በእንስሳት መድን ተጠቃሚ መሆናቸውን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በግብርና ሚኒስቴር የአርብቶ አደሮች አደጋ ቅነሳ ፕሮጀክት አስተባባሪ ጀማል አሊዬ ለኢትጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በሀገሪቱ በአርብቶ አደር አካባቢዎች በተደጋጋሚ በሚከሰተው ድርቅ ምክንያት በእንስሳት ሀብት ላይ የሚደርሰው ጉዳት ከፍተኛ ነው፡፡
ጉዳቱን ለመቀነስ ግብርና ሚኒስቴር ከሁለት ዓመት በፊት የጀመረው የአደጋ ስጋት ቅነሳና አካታች የኢኮኖሚ እሴት ማሻሻያ ፕሮጀክት ስር የእንስሳት መድን አገልግሎትን በማካተት አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል።
የ2017 የአንድ ወቅት ምዝገባን ጨምሮ ከ160 ሺ በላይ አርብቶ አደሮች የእንስሳት መድን አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል ብለዋል፡፡
የአርሶ አደር አካታች የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮጀክት በአሁኑ ሰአት በአፋር ፣በሶማሌ ፣በኦሮሚያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያና በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ስር በሚገኙ 187 ወረዳዎች ላይ እየተተገበረ መሆኑን ተናግረዋል።
አካባቢዎቹ የሀገሪቱን 60 በመቶ የሚሆን የእንስሳት ሀብት መያዛቸውን ጠቁመው፤ ከእንስሳት ሽያጭ የሚገኘው አብዛኛው ገቢው ከእነዚሁ አካባቢዎች ጋር የተያያዘ መሆኑን አንስተዋል።
አቶ ጀማል የመድን አገልግሎቱ ከተጀመረ እስካሁን ባለው ጊዜም አርብቶ አደሮችን ለማበረታት መንግሥት ከ140 ሚሊዮን ብር በላይ ፕሪሚየም መክፈሉን ገልጸዋል።
የእንስሳት መድን አገልግሎቱ ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው አካባቢዎች በድርቅ የሚጠቁና የእንስሳት ሀብት ያለባቸው አካባቢዎች መሆናቸውን ጠቁመው፤ ወረዳዎቹ የ20 ዓመት የሳተላይት መረጃን መሰረት በማድረግ የተለዩ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ የሚገኙ በእንስሳት ኢንሹራንስ ተጠቃሚ ሊሆኑ ይገባቸዋል ተብለው የሚታሰቡ ሁሉም ወረዳዎች ተካተዋል ማለት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡
የእንስሳት መድን አገልግሎቱ የክረምት ዝናብ በአግባቡ ካልተገኘ በበጋ ሶስት ወራት ማለትም ጥቅምት፣ህዳርና ታህሳስ ወራት ላይ ድርቅ ሊከሰት ይችላል ተብሎ ስለሚታሰብ በመስከረም ወር ምዝገባ የሚካሄድበት አሰራርን የሚከተል መሆኑን አንስተዋል።
ሌላኛው አሰራር ደግሞ የበልግ ዝናብ በአግባቡ ካልዘነበ በክረምት ወራት ድርቅ ሊያጋጥም ስለሚችል በየካቲት ወር ምዝገባው እንደሚካሄድ አስረድተው፤ ችግር ሲያጋጥምም በመድን አገልግሎቱ መሰረት አርሶ አደሩ በሚያገኘው ድጋፍ እንስሳቱን በመተካት ሕይወቱን እንዲመራ የሚረዳ አሰራር መሆኑን አመላክተዋል።
መስከረም ሰይፉ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም