አዲስ አበባ፦ በተያዘው በጀት ዓመት ዜጎች ስለጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ስርጭት በራሳቸው ቋንቋ ጥቆማና ቅሬታ እንዲያቀርቡ የሚያስችል አሰራር በክልሎች መዘርጋቱን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
በባለስልጣኑ የዋና ዳይሬክተር ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሺወርቅ ግርማ በተለይ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ ባለስልጣኑ በተያዘው በጀት ዓመት በክልሎች ቢሮ በመክፈትና ባለሙያዎችን በመመደብ ዜጎች ስለጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ስርጭት በራሳቸው ቋንቋ ጥቆማና ቅሬታ እንዲያቀርቡ፤ እንዲሁም በጉዳዩ ዙሪያ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የሚያደርግ አደረጃጀት ዘርግቷል፡፡
በጅግጅጋ፣ ድሬዳዋ፣ ጅማ፣ ሰመራ፣ ሀረር፣ አሶሳና በሌሎችም አካባቢዎች ቢሮዎች ተከፍተው በሥራ ላይ እንደሚገኙ ያነሱት ወይዘሮ የሺወርቅ፤ ተቋሙ ለሚያወጣው ሀገራዊ የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ጥናት ሪፖርትም ከከፈታቸው ቢሮዎች ግብዓት ይወስዳል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የተለያዩ ቋንቋዎች የሚነገሩባትና በርካታ የሕዝብ ቁጥር ያላት ሀገር መሆኗን ጠቁመው፤ የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ህብረተሰቡ ጥቆማዎችንና ቅሬታዎችን ሊያቀርብ እንደሚገባ አመላክተዋል።
ዜጎች የዳበረ የመረጃ አጠቃቀም ልምድ እንዲኖራቸው በተያዘው በጀት ዓመት ከፍተኛ የግንዛቤ ማስጨበጫና ህብረተሰቡን ተሳታፊ የሚያደርጉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ባለስልጣኑ በአዋጅ በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት በተለያዩ አማራጮች ህብረተሰቡ ምን አይነት መረጃዎችን ማሰራጨትና መጠቀም እንዳለበት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እየሠራ ነው ብለዋል፡፡
ጥፋቶች ተፈጽመው ሲገኙም ከተቋማትና ግለሰቦች የሚመጡ ቅሬታዎችና ጥቆማዎችን በማጣራት ሙያዊ አስተያየት በማከል ለሚመለከተው የሕግ አካል ተደራሽ እንደሚደረግ አመላክተዋል።
ዜጎችና ተቋማት ይሄንን በመረዳት በባለስልጣኑ ነጻ የስልክ መስመር እና በተለያዩ የተቋሙ የግንኙነት ዘይቤዎች በመጠቀም ቅሬታና ጥቆማ በማቅረብ ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በበይነ መረብ የሚሰራጩ የጥላቻና ሀሰተኛ መረጃዎች ያላቸውን የጉዳት ደረጃ በመከታተል ባለስልጣኑ ሪፖርት እንደሚያወጣ የገለጹት ወይዘሮ የሺወርቅ፤ በዚህም በፖለቲካ፣ በብሄር፣ በማንነት፣ በአመለካከትና በሌሎችም ላይ በማተኮር ርዕሰ ጉዳያቸው በየጊዜው የተለያዩ የስድብ፣ የዛቻ፣ ክብረ ነክና ሌሎችም ይዘት ያላቸው መረጃዎች እየተሰራጩ እንደሆነ መገንዘብ ተችሏል ብለዋል፡፡
እንደኤክስ (ትዊተር)፣ ዩቲዩብ፣ ፌስቡክ፣ ቲክቶክና በመሳሰሉት ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ቁጥጥር እንዳለ አንስተው፤ በአዲስ አበባ፣ በሐዋሳ፣ በድሬዳዋና በሌሎችም የክልል ከተሞች ለዜጎች የበይነ መረብ ሚዲያዎችን ለመጠቀም የሚያስችል ነጻ የግንዛቤ ማስጨበጫ መሰጠቱን አስታውቀዋል።
በአዲስ አበባ ለሚገኙ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚኒ ሚዲያ አባላትና መምህራን፣ በተጨማሪም ለፓርላማ አባላትና ለፍትህ አካላትም ስለጉዳዩ ግንዛቤ እንዲይዙ መደረጉን አንስተዋል። የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
በቀጣይም ከሬዲዮ አድማጮችና በጋዜጠኝነት ላይ ከሚሰሩ የሙያ ማህበራት ጋር በመተባበር ዜጎች በቂ ግንዛቤ ኖሯቸው ጥሰቶች ሲገኙ እንዲጠቁሙና ቅሬታ እንዲያቀርቡ ይሠራል ብለዋል፡፡
ቃልኪዳን አሳዬ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም