በኅዳር የዓይን ብሌን ልገሳ ወር ይከበራል

በሩብ ዓመቱ 75 የዓይን ብሌን ተሰብስቧል

አዲስ አበባ፡– የማህበረሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ መጪውን ኅዳር ወር የዓይን ብሌን ልገሳ ወር ሆኖ እንደሚከበር የኢትዮጵያ የደምና ሕብረ ሕዋስ ባንክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡ በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 75 የዓይን ብሌን ብቻ መሰብሰብ መቻሉም ተጠቁሟል፡፡

የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ታዬ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የዓይን ብሌን ልገሳ ላይ የማህበረሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ መጪው ኅዳር ወር በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል፡፡

ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ውስጥ የሚገኝ አንድ የዓይን ባንክ ብቻ መኖሩ የተደራሽነት ችግር ፈጥሯል ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ የዓይን ብሌን የማሰባሰብ ሥራው በአዲስ አበባ በሚገኙ ጥቁር አንበሳ፣ ቅዱስ ጳውሎስና ራስ ደስታ ሆስፒታሎች ብቻ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል። ይህም ለማህበረሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠርና በቂ የዓይን ብሌን ለመሰብሰብ ተግዳሮት ሆኗል ብለዋል፡፡

በተያዘው ዓመት ቢያንስ ከአዲስ አበባ ውጪ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ተጨማሪ የዓይን ባንክ ለመክፈት መታቀዱን አስታውቀው፤ ለዚህም ከአገልግሎቱ የዓይን ብሌን ወስደው ንቅለ ተከላ የሚሠሩ ጅማ፣ ጎንደር፣ መቀሌና ሐዋሳ ያሉ ሆስፒታሎች ላይ የዳሰሳ ጥናት እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 75 የዓይን ብሌን የመሰብሰብ ሥራ መሠራቱን ጠቅሰው፤ እንደ ሀገር ያለው የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ ፍላጎት ግን ከፍተኛ ነው፡፡ የዓይን ብሌን የሚለግሱ ሰዎችን ቁጥር ማሳደግ አስፈላጊ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በመጪውን ኅዳር የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት የዓይን ብሌን ልገሳ ወር በማካሄድ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ለመሥራት ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

የዓይን ባንክ ተደራሽነት እጥረት ተከትሎ ማህረሰቡ የዓይን ብሌን ለመለገስ ያለው እንቅስቃሴ ዝቅተኛ መሆኑን አስታውሰው፤ የህብረተሰቡን ተሳትፎ ለማሳደግ የደም ልገሳ መርሀ ግብር በሚከናወንባቸው ቦታዎች ላይ ዓይን ብሌን ቃል መግባትን አስተሳስሮ እንዲሠራ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከዚህ በፊት ዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ ሕክምና የተሰጣቸው ሰዎች ከመሠረቱት ማህበር ጋር በመተባበርም የግንዛቤ ፈጠራ ሥራውን ለማከናወን ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

በዓይን ብሌን ጠባሳ ምክንያት የዓይን ብርሃናቸውን አጥተው የተለያዩ ችግሮች ውስጥ የሚገኙ በርካታ ዜጎች መኖራቸውን አንስተው፤ የዓይን ብሌን የሚለገሰው ከሕልፈት ሕይወት በኋላ በመሆኑ በሕይወት እያለን ቃል ገብተን ለሌሎች ብርሃን እንስጥ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You