ማን እንደሀገር!

ከጊዜ ወደ ጊዜ ስር እየሰደደና ዜጎችን ለአስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና እንግልት እየዳረገ ይገኛል። በሕገወጥ መንገድ ድንበርን በመሻገር የተሻለ ሕይወትን በመሻት በሚደረገው ጉዞ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ዜጎች ለስቃይ፣ ለእንግልት፣ ለጉልበት ብዝበዛ፣ ለአካል ጉዳትና ለሞት እየተዳረጉ ይገኛል።

አንዳንዶች በመንግሥት ጥረት ወደሀገራቸው ሲመለሱ ሌሎች ደግሞ በማረሚያ ቤት ስቃይና በተለያዩ እንግልት ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ሥራዎቹ በርካታ ዜጎችን በተለያዩ ሀገራት ከሚያጋጥማቸው ችግሮች ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲመጡ እያደረገ ይገኛል። ከሰሞኑ በመካከለኛው ምሥራቅ የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ ዜጎችን ከሊባኖስ ወደሀገራቸው ለመመለስ በተደረገው እንቅስቃሴ 51 ዜጎችን መመለስ ተችሏል፡፡

ከተመላሾች መካከል አንዷ የሆነችው ባይሴ ኢንኪ፤ በቤሩት ለሰባት ዓመታት ያህል ቆይታለች፡፡ ታዲያ በእነኝህ ሁሉ የስደት ዓመታት ህይወት እንዳሰበችውና እንዳለመችው አልሆነላትም፡፡ ቤተሰቦቿንና ዘወትር የምትናፍቃቸውን የአብራኳ ክፋይ የሆኑ ልጆቿን አንዴም እንኳን ወደ ኢትዮጵያ ጎራ ብላ እንዳልጠየቀቻቸው ትገልጻለች፡፡

“የቤተሰቦቼን ናፍቆት ለመግለጽ ቃላት ያጥረኛል። በተለይም የልጆቼ ከባድ ነበር” የምትለው ባይሴ፤ እዚህ የሚወራው ወደውጭ ከተወጣ በቀላሉ ህይወት እንደሚቀየር ነው፡፡ ቋንቋ፣ የዜጎች የአኗኗር ዘይቤ፣ የሥራ ብዛትና ሌላም ህይወትን ከባድ ያደርገዋል፡፡ የሰው ቤት መስራቱ አንድ ችግር ሆኖ ሳለ በስደት ወቅት ደግሞ ሴትነት ሌላ ችግር ነው ትላለች።

ስሄድ በሕገወጥ ደላላ ነው የሄድኩት፡፡ ሄጄ በገባውበት ቤት የሚከፈለኝ ክፍያ ልጆቼን እንኳን ለመደጎም ያላስቻለኝ በመሆኑ በተደጋጋሚ አማራጮችን ስፈልግ ነበር ስትል ታስረዳለች።

በአሁኑ ወቅት ህይወታቸውን ለመቀየር በርካታ ዜጎች በስደት ምክንያት ከሀገራቸው እየወጡ ነው፡፡ ነገር ግን የስደት ላይ ህይወት እዚህ ሁነን እንደምናስበው ቀላል አይደለም፡፡ በእኔ ይብቃ ማን እንደሀገር! በሀገር መኖርን የሚመስል ነገር የለም። ምንም ቢሆን በሀገራችን ላይ ያገኙትን ሥራ ሰርቶ መኖር ይሻላል ስትል ባይሴ ትመክራለች፡፡

የናፈቅኳትን የሀገሬን ምድር ስረግጥ ልዩ የሆነ ስሜት ተሰምቶኛል፡፡ ይህ እንዲሆን ሁሌም ለፈጣሪዬ ጸሎት እያደረግሁ ነበር የምትለዋ ባይሴ ኢንኪ፤ ብዙ አደጋና ችግር አልፌ እዚህ ሀገሬ ስደረስ ሞቼ እንደተነሳሁ ነው የምቆጥረው በማለት ደስታዋን ትገልጻለች፡፡

እንደ ባይሴ ኢንኪ ሁሉ ከባድና አስከፊ ጊዜያትን እንዳሳለፈች በቁጭት የምትናገረው ሌላኛዋ ከሊባኖስ ተመላሺዋ ዝናሽ ገተሌ ናት፡፡

ከነበረው የከፋ ችግር በሰላም ወደሀገራቸው እንዲመለሱ በቆንጽላ ጽህፈት ቤቱ አማካኝነት ተመዝግበው እስከ ኤርፖርት ድረስ ተገቢው ሽኝት እንደተደረገላቸው በማንሳት፤ የተደረገላቸውን ትብብር በአዎንታ በመመልከት አመስግናለች፡፡

እንደ ዝናሽ ገተሌ ንግግር፤ ያሰቡትን አለማሳካት፤ እንደሄዱ አለመመለስ የሕገ ወጥ ስደት ትርፉ ነው። ዜጎች በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች የሀሰት ማማለያ ተታለው ያላቸውን ጥሪት ሸጠው እና ተበድረው ህይወታቸውንም ለአደጋ አጋልጠው ወደ ሳዑዲ አረቢያና ሌሎች ሀገራት በተለያዩ መንገዶች የተሻለ ኑሮና ሥራ ፍለጋ ይሄዳሉ፤ ዛሬም በዚህ መንገድ ጉዞው ቀጥሏል፡፡

ሊባኖስ በነበርንበት ወቅት የነበረው ችግር መድረሻ እስኪታጣ ድረስ የሚያስጨንቅ ነበር በማለት ያሳለፈችውን ከባድ ጊዜ የምታስታውሰው ዝናሽ፤ ከዛ ሁሉ ችግር አልፎ ለሀገር መብቃትን ማሰብም እንደሰማይ የራቀ መሆኑን በመከፋት ታወሳለች፡፡

ዝናሽ ገተሌ፤ በተጨባጭ እየተከናወነ ያለውን ሁኔታ ለመግለጽ ከባድ ነው፡፡ ብዙዎቹ ለሀገራቸው ምድር ሳይደርሱ አፈር ውስጥ የገቡ እህቶቻችን አሉ፡፡ ከዛ ውስጥ ተርፌ ሀገሬ እገባለሁ የሚል እሳቤ በፍጹም አልነበረኝም፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ቸርነት የሀገሬን ምድር ረግጫለሁ ትላለች፡፡

አሁንም በሊባኖስ የሚኖሩና በጭንቅ ያሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን የምታነሳዋ ዝናሽ ገተሌ፤ ወገን ለወገን ደራሽ ነውና መንግሥት ለእነሱ የሰጣቸውን አይነት ትኩረት ለሌሎቹም በመስጠት እንዲታደጋቸው ትጠይቃለች፡፡

በመጀመሪያው ዙር 51 ዜጎች ወደሀገራቸው በገቡበት ወቅት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው እንደተናገሩት፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሚያካሂደው የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎችን ደህንነት እየተከታተለ ችግሮች ሲያጋጥሙ መፍትሄዎችን እያስቀመጠ ሲሠራ ቆይቷል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም በሊባኖስ የተፈጠረውን ቀውስ ተከትሎ በርካታ ዜጎች ለችግር ተጋላጭ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ይህ ችግር እንደተሰማ በሚኒስቴሩ የሚመራ ብሄራዊ ኮሚቴና አፋጣኝ የቴክኒክ ኮሚቴ በማቋቋም ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች በማከናወን ላይ ይገኛል ይላሉ።

በዚህም በአካልና በዲጂታል የምዝገባ ሥርዓት ተዘርግቶ ዜጎች እየተመዘገቡ ይገኛሉ ያሉት አምባሳደር ነቢያት፤ ዜጎች ሊባኖስ በሚገኘው ቆንስላ ጽህፈት ቤት አማካኝነት በፈለጉት አማራጭ ተመዝግበው ወደሀገራቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል።

እስካሁን ከሶስት ሺህ በላይ ዜጎች በተለያዩ መንገዶች በቆንስላ ጽህፈት ቤቱ እንዲመዘገቡ የተደረገ ሲሆን፤ ወደ ሀገራቸው የመመለስ ሥራ የሚቀጥል ይሆናል ሲሉ ያስረዳሉ።

ከዚህም ባለፈ የአደጋ ተጋላጭነት ስጋት ያለባቸው አንፃራዊ ደህንነት ወደሚገኝበት ቦታ እንዲንቀሳቀሱ እየተደረገ መሆኑንም አምባሳደር ነብያት ይጠቁማሉ።

እንደ አምባሳደር ነቢያት ከሆነ፤ ዜጎቹን ለመመለስ እየተደረገ ባለው ጥረት የሚያስተባብር አመራር ወደ ሊባኖስ ተልኮ ሥራውን ጀምሯል። የመጡትንም ሆነ ገና የሚመጡ ዜጎችን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለማገናኘት የሚያስችል አሠራር ተዘርግቷል፡፡

ዛሬም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ሀገራት በስቃይ ላይ ይገኛሉ፡፡ ዜጎች የሕገወጥ ዝውውር ሰለባ እንዳይሆኑ የመንግሥት ተቋማት ከሚሠሩት ሥራ ያለፈ ሕዝባዊ ምላሽ ይሻል። እንደ መንግሥትና ሕዝብ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር በዜጎች፣ በህብረተሰብ እና በሀገር ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ከግንዛቤ ያስገባ የመከላከል ሥራ ለነገ የማይባል ነው፡፡

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You