የፖለቲካ ፓርቲዎችንና በትጥቅ ትግል ላይ የሚገኙትን በምክክሩ ለማሳተፍ ጥረት እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፡- የፖለቲካ ፓርቲዎችንና በትጥቅ ትግል ላይ የሚገኙትን በሀገራዊ ምክክሩ ለማሳተፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የኮሚሽኑ ቃልአቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ኮሚሽኑ ሀገራዊ ምክክሩ ሁሉን አካታችና አሳታፊ እንዲሆን በትኩረት እየሰራ ይገኛል፡፡

በሀገሪቱ የሚገኙ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችና በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ አካላት ወደ ምክክሩ እንዲመጡ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል።

በሀገራችን ከሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች አብዛኞቹ ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ጋር  ከተሳታፊነት ባለፈ በማማከርም ጭምር እየሰሩ መሆኑን ጠቁመው፤ በጣም ውስን የሆኑ ፓርቲዎች ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች በሂደቱ እየተሳተፉ አለመሆኑን አንስተዋል። ኮሚሽኑ የተቀሩት ፓርቲዎች ወደ ምክክር ሂደቱ እንዲመጡ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

እየተሰሩ ባሉ ስራዎች ጥሩ ውጤት መገኘቱን ያነሱት ቃልአቀባዩ፤ በዚህም በቅርቡ የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምክክር ሂደቱን መቀላቀላቸውን ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ የታጠቁ ኃይሎች ሂደቱን እንዲቀላቀሉ ጥረቶች እየተደረጉ ነው ያሉት አቶ ጥበቡ፤ እነዚህ አካላትም ወደ ምክክሩ እንዲመጡ ለማድረግ ኮሚሽኑ ብቻውን የሚሰራው ስራ ባለመሆኑ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ይገኛል ሲሉ አስረድተዋል።

ኮሚሽኑ ባላው አቅም ነፍጥ ያነገቡ አካላት በሀገራዊ ምክክሩ እንዲሳተፉ በሩን ክፍት አድርጎ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኑን ተናግረው፤ ጥያቄያቸውን ተቀብሎ በሂደት መታየት ያለባቸውን ጉዳዮች ለማየት ያለውን ዝግጁነት በመግለጽ ጥሪ እያቀረበ ይገኛልም ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ትጥቅ ትግል ላይ የሚገኙ ዜጎች ወደ ምክክር ሂደቱ በሚመጡበት ወቅት የሚያነሷቸው የደህንነት ስጋቶች ካሉ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተለይም ከመንግሥት ጋር በመሆን ምቹ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ኮሚሽኑ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ቃል አቀባዩ እንደገለጹት፤ ኮሚሽኑ ተቋቁሞ ስራ ከጀመረ ከሁለት ዓመት በላይ ሆኖታል፤ በእነዚህ ዓመታትም በርካታ የዝግጅትና የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡

ሀገራዊ ምክክሩ ሁሉን አካታችና አሳታፊ ከማድረግ አንጻር በተሰራ ስራም ከወረዳ እስከ ዳያስፖራው ማህበረሰብ ድረስ ተሳታፊዎችን መለየት ተችሏል ብለዋል። በቀጣይም በኦሮሚያ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራውን ለማጠናቀቅ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ በክልሎቹ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ኮሚሽኑ ተንቀሳቅሶ ስራውን መስራት ባለመቻሉ በአማራና ትግራይ ክልሎች ተሳታፊዎችን መለየትም ሆነ አጀንዳ የማሰባበሰብ ስራ አለማከናወኑን ተናግረዋል።

በትግራይ ክልል የምክክር ሒደቱን ለማከናወን የሚያስችሉ ውይይቶች መደረጋቸውን አስታውሰው፤ በቀጣይ ኮሚሽኑ በክልሉ ስራውን የሚጀምር ይሆናል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በአማራ ክልል ባሉ ግጭቶች ምክንያት ሙሉ በሙሉ ስራዎችን ማከናወን ባይቻልም ኮሚሽኑ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ተባባሪ አካላትን የመለየትና ስልጠናዎችን የመስጠት እንቅስቃሴዎችን አድርጓል ብለዋል።

እንቅስቃሴዎቹ ግን በሁሉም ወረዳዎች በተሟላ መልኩ ማካሄድ ባለመቻሉ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አልተቻለም ሲሉ ገልጸዋል።

በሁለት ክልሎች ያሉ ፈታኝ ሁኔታዎች እንዲስተካከሉና አንጻራዊ በሆነ ሁኔታ ስራውን እንዲሰራ ኮሚሽኑ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ በክልሎች ያሉ ሁኔታዎች ሲመቻች በፍጥነት ወደ ስራ መግባት የሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አመላክተዋል።

ዳግማዊት አበበ

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You