አዲስ አበባ፡- ጠቅላይ ሚኒስት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የብሪክስ አባል ሀገራት ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቀረቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሞስኮ በተካሄደው የብሪክስ ቢዝነስ ፎርም ላይ ትናንት በቪዲዮ ባደረጉት ንግግር እንዳሉት፤ በፍጥነት በማደግ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለብሪክስ ሀገራት ለኢንቨስትመንት፣ ኢኮኖሚያዊ ትብብርና ንግድ ትልቅ እድል ይዞ መጥቷል።
ኢትዮጵያ ያላት እምቅ የተፈጥሮና የግብርና ሀብት ሰፊውን የአፍሪካን ገበያና ከዚያም በላይ የሚፈልግ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የካርጎ ጭነትና መንገደኞችን በማጓጓዝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ግንባር ቀደም የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድም ተጨማሪ እድል ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።
በተጨማሪ የኢትዮጵያ ተመጣጣኝ የታዳሽ ኃይል መሠረተ ልማትና የሠለጠነ ወጣት የሰው ኃይል ሀገሪቱን ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ አድርጓል ሲሉ ተናግረዋል።
በቅርቡ ወደትግበራ የገባው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ሀገሪቱን የበለጠ ለቢዝነስ ተመራጭ የሚያደርጋት መሆኑን አስታውሰው፤ ይህም ኢትዮ ቴሌኮምን ጨምሮ ትልልቅ ተቋማትን ፕራይቬታይዝ ማድረግን የሚያካትት መሆኑን ጠቁመዋል።
እየተተገበረ ያለው ገበያ መር የውጭ ምንዛሪ ግብይትም ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን አስረድተው፤ እነዚህ ለውጦች ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንድትሆን ኢንቨስተሮችም ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኙ የሚረዱ መሆናቸውን አንስተዋል።
ብሪክስም በአባል ሀገራት መካከል የጋራ ተጠቃሚነትን በማስፋፋት ለሌሎች ምሳሌ መሆን መቻል እንዳለበት ጠቁመው፤ በትብብር መሥራቱ አባላቱን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ለሌሎች ዓለም አቀፋዊ የፋይናንስ ተቋማት ምሳሌ መሆን ያስችላል ብለዋል።
የብሪክስ አባል ሀገራት የዓለም አስተዳደራዊ መዋቅር ለታዳጊ ኢኮኖሚ ምላሽ ሰጪ እንዲሆን በንቃት መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሞስኮ በተካሄደው የብሪክስ ቢዝነስ ፎረም ላይ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት ፤ የብሪክስ አባል ሀገራት የዓለምን 50 በመቶ ሕዝብ እንደሚወክሉ ገልጸዋል።
በመሆኑም ይህ ትልቅ አቅም በዓለም የኢኮኖሚ ዕድገትና ዘላቂ ልማት ላይ ተጨባጭ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ አንስተዋል። ይህንን አቅም ወደ ተግባር ለመለወጥም በንቃት መሥራት ይገባናል ብለዋል።
በዚህም የዓለም አስተዳደራዊ መዋቅር ወካይ፣ አካታችና ለታዳጊ ኢኮኖሚ ምላሽ ሰጪ እንዲሆን ለማስቻል በንቃት መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የብሪክስ አባል ሀገራት ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበው፤ በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በማዕድን፣ በታዳሽ ኃይል በቴክኖሎጂና ቱሪዝም ዘርፎች ትልቅ እድል መኖሩን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ የ2025 የብሪክስ ኢኮኖሚያዊ ትብብር ስትራቴጂ እንዲሳካ የበኩሏን ኃላፊነት እንደምትወጣም ቃል ገብተዋል።
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 9/2017 ዓ.ም