በአክሱም ከአምስት ሺህ በላይ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ለመሳብ ታቅዷል

አዲስ አበባ፡- በከተማዋ ያለውን ሰላም አስተማማኝ በማድረግ በተያዘው በጀት ዓመት ከአምስት ሺህ በላይ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ለመሳብ ማቀዱን በትግራይ ክልል የአክሱም ከተማ ባህልና ቱሪዝም ፅ/ቤት ገለፀ።

የፅ/ቤቱ ኃላፊ አቶ ገብረመድህን ፍፁምብርሃን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳሉት፤ በክልሉ ያለውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዲያንሰራራ ለማድረግ አስተማማኝ የሆነ ሰላም ያስፈልጋል።

ከተማዋ ቀደም ሲል በርካታ ቱሪስቶች ስታስተናግድ ነበር፤ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ጎብኚዎች በእጅጉ መቀነሳቸውን አንስተዋል።

በመሆኑም በተያዘው በጀት ዓመት የከተማዋን ሰላምና መረጋጋት በማረጋገጥ ከአምስት ሺህ በላይ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ለመሳብ እቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል።

በአክሱም ከተማ ቀድሞ እንደነበረው ከፍተኛ የቱሪስት ቁጥር ወደ ከተማዋ እንዲመጣ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በክልሉ ውስጥ እየታየ ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋት በቱሪዝም ሥራ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እያሳደረ መሆኑን ተናግረዋል።

የተለያዩ ክብረ በዓላት ማለትም መስቀል እና አሸንዳ ሲከበሩ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ወደ ከተማዋ መምጣታቸውን አስታውሰው፤ በርካታ ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያንም ከተማዋንና ቅርሶችን መጎብኘታቸውን ጠቁመዋል።

በቀጣይ ወር የሚከበረው ዓመታዊው የአክሱም ፅዮን ማርያም በዓል ላይ በርካታ እንግዳ ይመጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ የተናገሩት ኃላፊው፤ በተለይ ቀደም ብሎ በነበረው ጦርነት ምክንያት የመምጣት ዕድል ያላገኙ ሰዎች እንደሚመጡ ያላቸውን እምነት አመላክተዋል።

አሁን ላይ ሰላም እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል የተሟላ ባይሆንም፤ በአንፃራዊነት ሲታይ ግን በጥሩ ሁኔታ እና ተስፋ የሚሰጥ የቱሪዝም እንቅስቃሴ መኖሩን አስረድተዋል።

የውጭ ጎብኚዎች በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚራገቡ ወሬዎች ሳይሆን በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ላይ ያለውን ሰላምና መረጋጋት በመመልከት ሊጎበኙ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

በመሆኑም የውጭ ሀገር ጎብኚዎች በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ላይ 340 የውጭ ጎብኚዎች እንዲሁም ከአንድ ሺህ በላይ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች መምጣታቸውን ገልጸው፤ የሰላም ሁኔታ አስተማማኝ እየሆነ ሲሄድ የጎብኚዎች ቁጥርም እየጨመረ እንደሚሄድ አብራርተዋል።

የባለፈውን ጊዜያት ድክመቶች በማረም በተያዘው በጀት ዓመት የተሻለ ሥራ ለመሥራት መታሰቡን ጠቁመው፤ በተለይ ሰላም ለቱሪዝም ዋነኛ ጉዳይ በመሆኑ ጎን ለጎን ሰላም እንዲረጋገጥ እና ቱሪዝም የተሻለ ውጤት እንዲያመጣ እንቅስቃሴ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

ሄርሞን ፍቃዱ

 አዲስ ዘመን ጥቅምት 9/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You