አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያና ኬንያ በካፒታል ገበያ ስትራቴጂካዊ ግንኙነታቸውን ማሳደግ የሚያስችል ትብብር መፍጠራቸው ተገለጸ።
የኢትዮጵያ የሰነድ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ከናይሮቢ የሰነድ ሙዓለ ንዋዮች ገበያና ከአይ ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት ጋር የመግባቢያ ሰነድ ትናንት ተፈራርሟል።
የኢትዮጵያ የሰነድ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ሥራ አስፈጻሚ ጥላሁን እስማኤል (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፤ ስምምነቱ ኢትዮጵያና ኬንያ በካፒታል ገበያ ልማትና እድገት ስትራቴጂካዊ ትብብር እንዲኖራቸው ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።
መግባቢያ ሰነዱ የገበያውን እድገት ከማፋጠን አኳያ ለኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ወሳኝ ነው ያሉት ጥላሁን (ዶ/ር)፤ በሀገራቱ መካከል የእውቀት ልውውጥን፣ አቅም ግንባታ፣ ድንበር ዘለል የሆኑ ኢንቨስትመንቶችን ለማበረታታት የሚያስችል ነው ብለዋል።
በኬንያና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የካፒታል ገበያ እድገትና ልማት በተለያዩ ስትራቴጂካዊ ትብብር ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይም ሀገራቱ የሰነድ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ልምድ ልውውጥ እንዲኖራቸው የሚያስችል ስምምነት መደረጉን ተናግረዋል።
የካፒታል ገበያን ሥርዓት ለመገንባት የገበያውን ሥነ-ምህዳር መረዳትን እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ ስምምነቱ ከኬንያ ተሞክሮ ለመውሰድና በዘርፉ ያለውን የእውቀት ክፍተት ለመሙላት የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።
የናይሮቢ የሰነድ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍራንክ ሚዊቲ በበኩላቸው፤ የመግባቢያ ስምምነቱ በአፍሪካ ካፒታል ገበያ እድገት ውስጥ ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያበረክትና ኢትዮጵያ በአፍሪካ የፋይናንስ ዘርፍ ወሳኝ ሚና እንድትጫወት ያስችላል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ቁልፍ የፋይናንስ ተዋናይ መሆኗን የገለጹት ሥራ አስፈፃሚው፤ የካፒታል እድገትን የበለጠ ለማሳደግ ከኢትዮጵያ ሰነድ ሙዓለ ንዋዮች ገበያና ከአይ ካፒታል ኢንስቲትዩት ጋር ትብብር መፈጠሩን ገልጸዋል።
ስምምነቱ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ባለሀብቶችን ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንደሚያሳድግ ጠቅሰው፤ ለሀገራቱ ምርት አቅራቢዎችና ባለሀብቶች ጠቃሚ እድሎችን ሊከፍት የሚችል ስምምነት መደረጉን ተናግረዋል።
የሀገራቱን የውስጥ ገበያ ከማጎልበት ባለፈ ቀጣናዊ ንግዶችን ለማጠናከር የሚያግዝ መግባቢያ ሰነድ መሆኑን በመግለጽ፤ በኢትዮጵያና በኬንያ መካከል ያለውን የካፒታል ገበያን ማጎልበት የሚያስችልና የእውቀት ሽግግር፣ አቅም ግንባታና ድንበር ዘለል ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ መሆኑም አስረድተዋል።
የአይ ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ገመቹ ዋቅቶላ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በስምምነቱ መሠረት የካፒታል መፍትሄዎችን በማቅረብ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያና በአካባቢው የካፒታል ገበያ እንዲያድግ እንደሚሠሩ ጠቅሰው፤ በተለይም በፈጠራና በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ በጋራ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
ስምምነቱ የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ በምስራቅ አፍሪካና በሀገሪቱ የፋይናንስ ገበያን ማጎልበት የሚያስችል መሆኑንም ጠቁመዋል።
ተቋማቱ በመግባቢያ ሰነዱ ላይ የተገለጹትን ተግባራት በመጪዎቹ ወራት ተግባራዊ ለማድረግ በቅርበት እንደሚሠሩም ተገልጿል። የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ በማህበረሰብ ውስጥ ያለመግባባት ሲፈጠር ውሎ ከማደሩ በፊት በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት የሚያስችል ባህላዊ እሴቶች ያላት ሀገር ነች ያሉት ሀይቻ ጉሉ፤ ዕሴቶቹ ለአሁናዊ ሀገራዊ ችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሄ ከመሆን አንጻር የላቀ ሚና ያላቸው መሆኑን በመገንዘብ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ባህላዊ ሥርዓቶቻችን ተገቢ ትኩረት በማጣት እየተሸረሸሩ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት አቅማችን ጥያቄ ውስጥ እንዳይገባ ቆም ብሎ ማጤን ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
በሽምግልና ሥርዓት ያጠፋውን ገስፀው ግጭትን አስወግደው ሰላምን የሚያወርዱ ባህላዊ የእርቅ እሴቶችን በማስተዋወቅ ለትውልድ በተግባር ማሸጋገር ይገባል። በየአካባቢው የሚገኙ ሀገር በቀል የሰላም እሴቶችን በጥናት ጭምር አስደግፎ ወደ ተግባር በመለወጥ ለችግሮቻችን ሀገርኛ መፍትሄ ማምጣትን መለማመድ ቢቻል ውጤቱ የላቀ መሆኑንም አመልክተዋል።
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 9/2017 ዓ.ም