የኮሪደር ልማቱ የዜጎችን ክብር በሚመጥን መልኩ የተከናወነ ነው

አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወነው የኮሪደር ልማት የዜግጎችን ክብር በሚመጥንና የነዋሪውን የኑሮ ሁኔታ ያሻሻለ መሆኑ ተገለጸ።

በአዲስ አበባ እየተከናወነ ባለው የኮሪደር ልማት ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ የሚሰጥ መድረክ ትናንት በተካሄደበት ወቅት፤ ልማቱ የዜጎችን ክብር በሚመጥን መልኩ ለሰው ቅድሚያ የሰጠና ዜጎች በተሻለ፣ ንጹህና ዘመናዊ በሆነ ሁኔታ መኖር እንዲችሉ ያደረገ መሆኑ ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመድረኩ ላይ ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች መልስ ሲሰጡ፤ ለልማት የተነሱ አካባቢዎች ላይ የነበሩ ቤቶች ያረጁ ፣ጊዜያቸው ያለፈባቸውና የወደቁ ከመሆናቸው ባሻገር የዜጎችን ክብር የሚመጥኑ እንዳልነበሩ ገልጸው፤ ቤቶቹን በማንሳት ነዋሪዎች ለኑሮ ምቹ በሆነ ቤት ውስጥ እንዲገቡ መደረጉ መንግሥት ምን ያህል ለዜጎች ቅድሚያ ሰጥቶ እየሠራ እንዳለ ማሳያ ነው ብለዋል።

የኮሪደር ልማቱ ዋነኛ ዓላማ አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ አበባ የሆነች ከተማ ለማድረግ ነው ያሉት ከንቲባዋ፤ ከተማዋ ውብ መሆን የምትችለው ደግሞ መሠረተ ልማቷን በተሟላ ሁኔታ ስታገኝ እንደሆነ ተናግረዋል። መሠረተ ልማቶች ሲታደሱ፣ ከተማዋ ስትታደስ፣ እንዲሁም ነዋሪዎቿ ምቹ መኖሪያ ቤትና አካባቢን ሲያገኙ እንደሆነ ተናግረዋል።

ከንቲባዋ፤ ከተማዋ የዛሬ ብቻ ሳትሆን የወደፊትም ከተማ ናት በማለት፤ የኮሪደር ልማቱ የሚሠራው አሁን ላለው ትውልድ ብቻ ሳይሆን የነገውንም ትውልድ ታሳቢ አድርጎ እንደሆነ አብራርተዋል።

“ዛሬ ለነዋሪዎቿ ምቹ እናድርግ ብለን ስንሠራ ወደፊት ህጻናት ደስ ተሰኝተው፣ በአካባቢያቸው ንጹህ አየር አግኝተው ማደግ ይገባቸዋል ለማለት ነው” ያሉት። ይህም ከትውልድ ግንባታ ሥራዎች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የተሳተፉት ልማቱ በማንኛውም ወገን ዘንድ ቅቡልነት ያለው፤ የዜጎችን ኑሮ ያሻሻለ፤ የከተማዋን ውበትና ደረጃ ያስጠበቀ መሆኑን በመጥቀስ፤ ግንዛቤ መስጠትን ጨምሮ በአሠራሩ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ማረም እንደሚገባ አንስተዋል።

የኮሪደር ልማት ሥራው የከተማዋን ገጽታ የሚቀይርና የዲፕሎማቲክ መቀመጫነቷን የሚያረጋግጥ መሆኑን እንዲሁም ነዋሪዎች ከነበሩበት አስከፊ የኑሮ ሁኔታ የሚያላቀቅ መሆኑን ጠቅሰው፤ ልማቱ በሁሉም የከተማዋ አካባቢዎች ተደራሽ እንዲሆንም ጠይቀዋል።

ከተማ አስተዳደሩ በቀጣይ ዙር በሚያከናውነው የኮሪደር ልማት ችግሮች እንዳይከሰቱ መረጃ ላይ የተመሰረቱ ቅሬታዎችንና ጥያቄዎችን ተቀብሎ እንደሚያስተናግድና ስህተት በሚፈጽሙ አካላት ላይም ርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑን ከንቲባዋ አንስተዋል። በሂደት ልማቱን በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሠራም ጠቁመዋል።

ውይይቱ ከተማዋን ለማዘመን፣ ጽዱ፣ ውብና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ እየተሠሩ ባሉ የኮሪደር ልማት ላይ ለመግባባት ተሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ ሲሆን፤ በውይይቱም የሃይማኖት አባቶች፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎች፣ የማህበረሰብ ተወካዮችና ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

አዲሱ ገረመው

 አዲስ ዘመን ጥቅምት 9/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You