በኢንዱስትሪ ፓርኩ ሰባት ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገበ ኩባንያ ወደ ሥራ ሊገባ ነው

አዲስ አበባ፡- በሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሰባት ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገበ የሶላር ፓኔል ማምረቻ ኩባንያ ወደሥራ ሊገባ መሆኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

የኮርፖሬሽኑ የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽንና ማርኬቲንግ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዘመን ጁነዲን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ቶዮ ሶላር ኢነርጂ የተባለ የጃፓን ኩባንያ ሰባት ቢሊዮን ብር ካፒታል ኢንቨስትመንት በማስመዝገብ በሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ገብቶ ሊያለማ ነው።

ኩባያው ሥራውን ለመጀመር ከሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሼዶችን ወስዷል ያሉት አቶ ዘመን፤ አንድ ነጥብ ሁለት ሄክታር መሬትም ተረክቧል።

ኩባንያው ዘመናዊ ሶላር ፓኔሎችን እንደሚያመርት ጠቅሰው፤ ምርቱንም ወደ መካከለኛው ምስራቅ፣ ሕንድና አሜሪካ ገበያዎች የሚልክ ይሆናል ብለዋል።

በተጨማሪም ኩባንያው በፓርኩ ውስጥ ከ200 በላይ የመኖሪያ አፓርትመንቶችን በኪራይ እንደሚይዝ አቶ ዘመን ጠቁመዋል።

አምራች ድርጅቱ ማሽነሪዎቹን ተክሎ እንዳጠናቀቀ በቅርቡ ወደ ሥራ ሲገባም ከ400 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር አስታውቀዋል።

እንደ ምክትል ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ፤ ኩባንያው ትልቅ አቅምና ልምድ ያለው በመሆኑ ኢንቨስትመንቱ ለሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር ነው።

እንደሀገር ከታየ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በሰው ኃይል ልማት እንዲሁም በውጭ ምንዛሪ ግኝት ከፍተኛ አበርክቶ የሚኖረው ማምረቻ መሆኑን አስረድተዋል።

የመንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን ተከትሎ በተከናወኑ የውጭ ምንዛሪና የኢንቨስትመንት ዘርፍ ማበረታቻዎች እንዲሁም የፖሊሲ ማሻሻያ ሥራዎች ጋር በተያያዘ በርካታ ባለሀብቶች ወደኢንዱስትሪ ፓርኮችና ወደ ድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ገብተው ለማልማት ቅድመ ሁኔታዎችን በማጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን አመላክተዋል።

በተለይ የቻይናውያን ባለሀብቶች ፍሰት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው ያሉት አቶ ጁነዲን፤ በቦሌ ለሚ፣ ቂሊንጦና ኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ ገብተው ለማልማት ያላቸው ፍላጎት እየጨመረ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከጃፓንና ቻይና እንዲሁም ከአሜሪካ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰት እየተስተዋለ መሆኑን አንስተው፤ በተጨማሪም የሩስያ ባለሀብቶች በድሬዳዋ የነጻ ንግድ ቀጣና ገብተው ለማልት ፍላጎት ማሳየታቸውን አስረድተዋል።

ኮርፖሬሽኑም ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ ከባለድርሻ አካላት በተለይም ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በትብብር እየሠራ መሆኑን አስታውሰው፤ በዚህም በመላው ዓለም ከሚገኙ የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች ኢንቨስትመንት ዳይሬክተሮች ጋር በቅርበት እየሠራ ነው ብለዋል።

አገልግሎት አሰጣጡን ከምንጊዜውም በላይ ፈጣንና ቀልጣፋ በማድረግም ባለሀብቶች በፍጥነት አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። ለኢንቨስትመንት ፍሰቱን ለመጨመር የምናደርገውን ጥረት አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 9/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You