ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ የህብረተሰቡ ሚና

የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ የሀገርን ሠላም ለማስጠበቅና የሕዝቦችን ደህንነት ለማስጠበቅ ቁልፉ ጉዳይ ነው። የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሂደትን ስኬታማ ለማድረግ የሕዝቦች ቀና ተሳትፎ ወሳኝ ነው። ይህንን የተረዱ የሰለጠኑ ሀገራት የሕግ የበላይነትን ባህል አድርገው፤ ዜጎቻቸውን በሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ሂደት ተሳታፊ በማድረጋቸው የዜጎቻቸውንና የሀገራቸው ደህንነት ማረጋገጣቸውን የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

በእነዚህ ሀገራት የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ጉዳይ ዜጎች አጥፊን ተቆጣጣሪ እና ህብረተሰብን ጠባቂ ሲሆኑ፣ ከጸጥታ ኃይሎች ድርሻ የማይተናነስ ድርሻ አላቸው። የፀጥታ ኃይሎች በሕግ ማስከበር ሂደት ተሳታፊ ለሆኑ ዜጎች ህጋዊ ከለላና ጥበቃ እንደሚያደርጉም የሕግ ምሁራን ይናገራሉ።

ለመሆኑ ዜጎችን የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ሂደት ተሳታፊ ከማድረግ አኳያ የሀገራችን ልምድ ምን ይመስላል? ዜጎችን የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ሂደት ተሳታፊ ማድረግ ምን ፋይዳ ይኖረዋል? በምን መልኩስ ተሳታፊ ማድረግ ይቻላል? የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ሂደት ዜጎችን አሳታፊ ያደረጉ ሀገራት ተሞክሮስ ምን ይመስላል?በሚሉት ጉዳዮች ላይ የሕግ እና የሥነ ምግባርና ሥነ ዜጋ ባለሙያዎች አስተያየታቸው ሰጥተውናል።

በኢትዮጵያ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ሂደት በስፋትም ባይሆን ዜጎችን ተሳታፊ የማድረግ ጅምር ሂደቶች እንዳሉ የሕግ ባለሙያው ኢዘዲን ፈድሉ ይናገራሉ። ለማሳያነትም በፍትሐብሔር ሕጉ አንቀጽ 277 እና ተከታዮቹ መሠረት ተከራካሪ ወገኖች ክርክራቸውን በስምምነት ከጨረሱ ፍርድ ቤት ለሕግና ለሞራል ተቃራኒ አለመሆኑን ተመልክቶ ሊያጸድቅላቸው እንደሚችል ያነሳል።

ይህ ውሳኔ ተፈጻሚነት ያለው በመሆኑ ዜጎች በውሳኔ ሂደት ተሳተፈዋል ለማለት የሚያስችል ነው ይላሉ። በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጋችንም ግለሰብ ዐቃቤ ሕግን ተክቶ ክስ መመስረት እንደሚችል በጠባቡም ቢሆን የተመላከተ መሆኑን አንስተው በኢትዮጵያ በወንጀል ጉዳይ ግን እምብዛም የዳበረ አሠራር አለመኖሩን ይገልጻሉ።

የሥነ ዜጋ እና ሥነ ምግባር መምህሩ አቶ ዘላለም ረጋሳም የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ ከመደበኛው የሕግ ሥርዓት ውጪ ያሉና ህብረተሰቡ የሚያምንባቸውን ዜጎች ማሳተፍ ለሕግ መከበር ሂደት በጎ ሚና እንደሚኖረው ይናገራሉ። የሀገር ሽማግሌዎች፣ እናቶች፣ የእድሜ ባለጸጋዎችና ምሁራን በሕግ ማስከበር ሂደት ውስጥ ተሳታፊ ቢሆኑ ለሕግ የበላይነት መከበር ፋይዳ እንደሚኖረው ያስረዳሉ።

በሀገራችን ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓቶች መኖራቸውን የጠቀሱት መምህሩ፤ ይህ ሥርዓት አሁን ተግባራዊ ከሚሆንበት አግባብ በተሻለ መልኩ ከዘመናዊው የሕግ የበላይነት በማረጋገጥ ሥርዓት ጋር ተሰናስኖ ተግባር ላይ ቢውል የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ተግባርን ውጤታማ ለማድረግ መልካም ይሆናል የሚል አስተያየት ይሰጣሉ።

አቶ ኢዘዲን በመደበኛው የሕግ አስከባሪ ተቋማትና የሕግ የበላይነትን በማስከበር ሥርዓት ውስጥ በኖርዌይ፣ ጀርመን፣ እንግሊዝ አሜሪካና ሌሎችም ሀገራት በወንጀል ጉዳዮች ጭምር ዜጎችን የማሳተፍ ልምድ በስፋት እንደሚተገበር የጠቀሱት የሕግ ባለሙያው፤ በአሜሪካውያን ዘንድ የሚተገበረውን “ጁሪ” የተሰኘውን ሥርዓት በማሳያነት ያነሳሉ።

አቶ ኢዘዲን እንዳስረዱት፣ ጁሪ የአሜሪካ ዜጎች በፍትህ ሂደት ውስጥ የሚሳተፉበት መንገድ ነው። በዚህ ሂደት እያንዳንዱ ፍርድ ቤት ለዳኝነት አገልግሎት በዲስትሪክቱ ውስጥ ካሉ አውራጃዎች ብቁ ናቸው ብሎ ያመነባቸውን ዜጎች ይመርጣል።

ዳኞች እና ጠበቆቹ በችሎት ውስጥ ለማገልገል ብቁ መሆናቸውን ለመወሰን ለተመረጡ ጁሪዎች ጥያቄዎችን ያቀርባሉ። በመልሳቸው መሠረት በችሎት ውስጥ እንዲያገለግሉ ሊወሰን አሊያም እንዳያገለግሉ ሊገለሉ ይችላሉ ነው ያሉት።

በዚህ የሕግ የበላይነት ለማስከበር ሂደትም የህበረተሰቡ ተሳትፎም መታከል በወንጀሎችና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ በሚወሰኑ ውሳኔዎች ላይ የህብረተሰብ ቅሬታን ለማስቀረት፣ አንዳንድ ጉዳዮችን ከመደበኛው የዳኝነት ሥርዓትና የፍትሕ አካላት ባለፈ ከህብረተሰቡ ዘንድ የሚኖረውን ዕይታ ለመረዳት የሚያስችል ነው ያሉት የሕግ ባለሙያው፣ ዜጎች ለሕግ መከበር በራሳቸው ዘብ እንዲቆሙ ለማድረግና ወንጀልንና ሕግን የጣሱ አሠራሮችን ለመከላከል ፋይዳ እንደሚኖረው የሕግ ባለሙያው አስረድተዋል።

መምህር ዘላለም በበኩላቸው፣ የሕግ የበላይነት መከበር ለዜጎች ወሳኝ የመኖር ዋስትና መሆኑን አጽንዖት ሰጥተው ይናገራሉ። ለዚህም በሕግ የበላይነት ማስከበር ተግባራት ላይ ዜጋውን ማሳተፍ ለሕግ አስከባሪ አካላት ትልቅ አቅም ለሀገርም ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ያስረዳሉ። ዜጎች በሕግ የበላይነት ማስከበር ሥርዓት ውስጥ በተጨባጭ ተሳታፊ የሚሆኑበት አሠራር ቢዘረጋ በሀገራችን አብዛኛውን ጊዜ ተፈጸሙ ብለን የምንሰማቸው አሰቃቂና በርካታ ወንጀሎች ላይ የሚወሰኑ ውሳኔዎች በሕዝብ ዘንድ ቅሬታን የሚፈጥሩ አይሆኑም ይላሉ።

ዮርዳኖስ ፍቅሩ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 9/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You