“የትብብር ማሕቀፍ ስምምነቱ ለኢትዮጵያ  ትልቅ ስኬት ነው” ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር

ትዮጵያን ጨምሮ የላይኞቹ የዓባይ ወንዝ ተፋሰስ ሀገራት በኢ-ፍትሃዊ የውሃ ክፍፍል ሕግ ተጠፍንገው አንድ ምዕተ ዓመት ለተቃረበ ጊዜ ቆይተዋል። በተለይ ኢትዮጵያ ከምድሯ የሚነሳውን የዓባይ ወንዝ እንዳትነካ በታችኞቹ ሀገራት በተለይም በግብጽ ሲፎከርባትና ሲዛትባት ከርሟል።

ይሁንና ኢትዮጵያ ይህን የቅኝ ገዥዎችን ሕግ “ይሁና” ብላ ዝም ማለትን ምርጫዋ አላደረገችም። ለሕዝቧ ይበጃል ያለችውን የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይልን መስጠት የሚያስችል ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን እውን አድርጋለች፤ በዚህ ብቻ ሳያበቃ ተቀባይነት በሌለውና ሁለት ሀገራትን ብቻ ተጠቃሚ የሚያደርገውን ሕግ ውድቅ ሊያደርግ የሚችልና በፍትሃዊነት ላይ የተመሰረተ አጠቃቀምን መሰረት ያደረገ የናይል ወንዝ ተፋሰስ የትብብር ማሕቀፍ ስምምነትን የተፋሰሱ ሀገራት እንዲፈርሙና እንዲያጸድቁ በማድረግ ከሰሞኑን ወደ ሕጋዊ ሰነድ አሳድጋዋለች።

ይህንኑ የናይል ወንዝ ተፋሰስ የትብብር ማሕቀፍ ስምምነት ሕጋዊ መሆንን በተመለከተ የኢፌዴሪ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ከትናንት በስቲያ ለጋዜጠኞች መግለጫና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ ይህንኑ እንደሚከተለው አጠናቅረን አቅርበነዋል። መልካም ንባብ።

የትብብር ስምምነት ማሕቀፉ እንደምታ

የናይል ወንዝ ተፋሰስ የትብብር ማሕቀፍ ስምምነት ከ17 ዓመት በላይ ሲታሰብበት የነበረና ሲሰራበትም የቆየ ሲሆን፣ ከጥቅምት 3 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ሕጋዊ ሰነድ፣ ሕጋዊ ማሕቀፍ ሆኖ ይቀጥላል። በስምምነቱ ላይ በተለይ ሀገራችንን የሚጠቅም ልማት በተለያየ ጊዜ በዓባይ ላይ ማልማት እያሰብንና እየፈለግን በተለያየ ምክንያት ሳይሆንልን ቀርቷል፤ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በዋናነት የኢትዮጵያን ስም በማጠልሸትና እንዳንጠቀምም አሳሪ ሕጎችን በማስቀመጥ ይደረግ በነበረው አካሔድ ነው። በአሁኑ ወቅት ግን ስምምነቱ፣ የነበረውን አሳሪ ሕግ ሽሮ ለኢትዮጵያውያንም ለሌሎች ሀገሮችም ጭምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው፡፡ በመሆኑም ለእኛ ደግሞ ተጠቃሚነቱ ላይ የአንበሳው ድርሻ እንድንወስድ የሚያደርግ ነው።

በዚህ ስምምነት ላይ አስራ አምስት ዋና ዋና መርሆዎች አሉ። እነዚህ ዋና ዋና መርሆዎች በሶስት ቦታ ብንከፍላቸው አንደኛው በተለይ ወደ አራት የሚሆኑት ዋና ዋና መርሆዎች የመጠቀም መብት ጉዳይ ጋር የተገናኙ ሃሳቦች ያለቡት ነው። ሁለተኛው ጉዳይ ይህን የውሃ ሀብት መጠበቅ፣ መንከባከብና ተፋሰሱ ላይ ልማቶችን በማካሔድ ዘላቂ አገልግሎት የሚሰጥ በማድረግ ላይ ኃላፊነትን የሚሰጥ፣ ሁሉንም የተፋሰሱ ሀገራት ኃላፊነት የሚሰጥ፣ የሚያስገድድ ሥርዓት በውስጡ ይዟል።

ሶስተኛው ጉዳይ መረጃዎችን በመከፋፈል የልማት እቅድ፣ የውሃ ፍሰት መጠን የተለያዩ በተፋሰሱ ላይ ያሉትን ማንኛውንም መረጃ እያንዳንዱ የተፋሰሱ አባል ሀገራት እርስ በእርሳቸው መረጃ እየተለዋወጡ እንዲሄዱ የሚያግዝ መርሆዎችን ይዟል። እነዚህ መርሆዎች በ45 አንቀጾች የተደገፉ ናቸው። 45ቱን አንቀጾች ብናይ የመጀመሪያዎቹ 15ቱ፤ 15ቱን መርሆዎች የሚመልሱ ሲሆን፣ የቀሩት 30 የሚሆኑቱ ደግሞ ከሕግ እና ከተቋም አሰራር ጋር የተገናኘ በቀጣይ ምን እንደሚሆን የሚገልጹ ናቸው።

ስለዚህ የዚህኛውን የናይል ወንዝ ተፋሰስ ትብብር ማሕቀፍ ስናወራ ከትርጉሙ ጀምረን ምን ምን እንዳለው አይተን፤ በተለይ ለኢትዮጵያ ጠቀሜታው ምንድን ነው? ብለን ብናይ ብዙ ነው። በታችኛው የዓባይ ወንዝ ተፋሰስ ያሉ ወንድሞቻችን ግብጽና ሱዳን እነርሱን ብቻ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነባር ሕጎችን ይዘው የመጡ ናቸው። ይህ ሲሆን በተለይ ኢትዮጵያ ከ85 በመቶ በላይ ለዓባይ (ለናይል ወንዝ) እያወጣች ምንም ሳትጠቀም ወይም ደግሞ ኢትዮጵያ እንዳትጠቀም ሲደረግ ቆይቷል፤ ይህ ስምምነት ግን የነበረውን ሥርዓት በትልቁ ቀይሮ እኛም የመጠቀም መብት እንዲኖረንና ሌሎቹም መጠቀም እንዲችሉ የሚያደርግ ነው።

እንዲያ ስንል እኩል ውሃ መጠቀም ሳይሆን የመብቱን እኩልነት ነው የማናየው። ከዚያ በኋላ ባዋጣነው ልክ ደግሞ መጠቀም ያስፈልገናል። ስለዚህ በጣም ትልቅ የውሃ መጠን ወደ ናይል ወንዝ ይፈስሳል። በዚያው ልክ ለመብራት (ሃይድሮፓወር )፣ ለመስኖ፣ ለመጠጥ ውሃ ለማንኛውም ሥራዎች ለመጠቀም ከፍተኛ እድል ሰጥቶናል። በዚህም ኢትዮጵያውያን ልንኮራበት ይገባናል።

በዚሁ አጋጣሚ የዛሬ 15 እና 16 ዓመት ይህ ሃሳብ ሲጠነሰስ የነበሩ ከፍተኛ ባለሙያዎች፣ ሚኒስትሮች፣ መሪዎች ሊመሰገኑ ይገባል። እኛ ኢትዮጵያውያን አንዱ የጀመረውን ማስቀጠል ልማዳችን ነው። እኛ ዛሬ ስኬቱን ስናጭድ ትናንት በጣም ብዙዎች ዋጋ ከፍለውበት ነው። ከባለሙያ፣ ከሚዲያና ከመንግሥት አመራር ጀምሮ ይህ ማኅቀፍ እንዲሳካ ከፍተኛ ድርሻ ያበረከቱ ወገኖቻችን አሉና ይመሰገናሉ።

እነርሱ ብቻ ሳይሆኑ አጎራባች ሀገሮች በተለይ ደቡብ ሱዳን እውነት ለመናገር በቅርብ ጊዜ በሚያስገርም ሁኔታ ስምምነቱን ተመልክተው በፍጥነት እንዲጸድቅና ሕግ እንዲሆን በማድረጋቸው በትልቁ ይመሰገናሉ። በዚሁ አጋጣሚ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር በጉዳዩ ላይ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ነው። በተለየ ሁኔታ ደግሞ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመሪዎች ደረጃ በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ ድርሻቸው የጎላ ነበር። ሌሎች ኢትዮጵያውንም በየደረጃው ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ነው።

ይህ ማሕቀፍ ለእኛ ትልቅ ስኬት ነው። ባሳካነው ልክ ቅሬታ ያላቸው የሚመስሉ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ወገኖቻችን ደግሞ አሉ። የዚህ ማሕቀፍ ዋና ዓላማ ማንንም ለመጉዳት አይደለም። እኛም መጠቀም፤ እነሱም መጠቀም መብታቸው ነው። ትልቁ ነገር በትብብርና በጋራ ማልማት በጋራ ማደግና በመተጋገዝ መሥራት ሲሆን፣ የተፋሰሱን ሀገራት ዜጎች እኩል ተጠቃሚ ማድረግ ማስቻል መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ ማስገንዘብ እወዳለሁ።

ማሕቀፉን በተመለከተ ቀጣይ ሥራ

በቀጣይ የምንሰራቸው አንደኛውና ትልቁ ሥራችን የዚህ ማሕቀፍ ከጥቅምት 3 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ሕግ መሆን የሚያግዘን የዓባይ ወንዝ ኮሚሽን ወይም ደግሞ ናይል ሪቨር ቤዚን ኮሚሽን ምስረታን ነው። እንሰራ የነበረው እስካሁን ባለን ኢኒሼቲቭ ነው፤ ኢኒሼቲቭ የተባለው ናይል ቤዚን ሲሆን፣ በአስሩ ሀገሮች ውስጥ ያለን ተሰባስበን (አስር ያልኩት ኤርትራ ስለማትመጣ ነው) በየዓመቱ የውሃ ሚኒስትሮች ስብሰባ እናደርጋለን፤ ምን ላይ እንደምንወያይም እንነጋገራለን። ሃሳቦችንም እንቀያየራለን። ስብስቡ በኮሚቴ ደረጃ ነው።

አሁን የዚህ ማሕቀፍ መጠናቀቅ ትልቁ ድርሻ በቀጣይ ለሚኖረን ኮሚሽን የራሱን መሰረት መጣሉ ላይ ነው።

በቀጣይ በሁሉም ሀገሮች የሚሰሩ የልማት ሥራዎችን የሚያስተባብር ያ ኮሚሽን ይሆናል። ኮሚሽኑ የሚያግዝ፣ የሚመራም ይሆናል። ለእሱ ደግሞ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ድርሻ እየበረከተች ትገኛለች። በተለይ ኢኒሼቲቩ እዚህ እንዲደርስ ጭምር በየዓመቱ የምናወጣው ወጪ ከማንም በላይ ነው፤ ከየትኛውም ሀገር በላይ ትልቁን ወጪ የምታወጣው ኢትዮጵያ ናት። ከዚህም የተነሳ የትብብር ማሕቀፉን በዚህ ደረጃ ማሳካት ችለናል።

በአጭር ጊዜ ደግሞ የኮሚሽኑ መቋቋም ትልቁ የምንጠብቀው ጉዳይ ሆኖ ከዚያ በተረፈ ደግሞ በሌሎችም ዓለም ላይ ያለው ኮሚሽን ተመሳሳይ ልምድ ያላቸውንም ልምድ የምንቀስም ይሆናል።

ማሕቀፉን ከነበሩ ስምምነቶች የሚለየው

የናይል ተፋሰስ የትብብር ማሕቀፍ ከሌሎቹ የሚለው በፊት የነበረው ሕግ አቃፊ ባለመሆኑ ነው። ውሃውን ሁለት ሀገራት ብቻ የተካፋፈሉበት ሁኔታ ብቻ ነበር። በዚህ መልኩ የቀደመው ስምምነት የላይኞቹ ተፋሰስ ሀገራትን የረሳ ሕግ ነበር። ይህ ሕግ ተቀባይነትም የለውም። ተቀባይነት የሌለው ምክንያት ሁለቱም የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ለናይል ወንዝ ምንም አስተዋጽኦ አያደርጉም።

ኢትዮጵያ 86 በመቶ አስተዋጽኦ ስታደርግ የምትጠቀመው የውሃ ሀብት ምንም አልነበረም። ሁለተኛው በሌሎቹ ነጭ ዓባይ በምንላቸው ላይም በዚያ ደረጃ ላይ ችላ ተብሏል። ስለዚህ የበፊቱ ስምምነት አቃፊ ያልሆነና የተወሰኑ አካላትን ብቻ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። እናም የታችኛው አካባቢ ያሉ ሀገሮች ዓባይን በባለቤትነት እንዲያስተዳድሩ መብት የሰጣቸው ነው። የትብብር ማሕቀፉ በተለየ ሁኔታ በዓባይ ወንዝ ላይ አስተዋጽኦ ያላቸው ሀገሮች በዚያ ልክ እንዲጠቀሙ የሕግ ማሕቀፍ እንዲሆን ያስፈለገበትና ወደሥራም የተገባበት ምክንያት ለዚህ ነው።

ስለዚህ በፊት የነበረው ሕግ የቅኝ ገዥ ሕግ ነው። የቅኝ ገዥ ሕግ ደግሞ ከዚህ በኋላ የሚያስኬድ አይሆንም፤ ምክንያቱም አፍሪካ ከቅኝ ግዛት ነፃ ወጥታለች። ከአሁን በኋላ መሥሪያ ቤትም አይኖረውም። በዚያ ደረጃ ሲታሰብም በጣም አግላይ ሕግ ነበር። ይህ የአሁኑ ግን አቃፊ ሕግ ነው።

በሌላ በኩል ግብጾች ከሰሞኑን መግለጫ አውጥተዋል። ባወጡት መግለጫ ጉዳዩን አሳዩ እንጂ በተለያየ ጊዜ በምናደርጋቸው ስብሰባዎች ሁለቱም ሀገሮች ማለትም ግብጾችም ሆኑ ሱዳኖች አቋማቸውን ያንጸባርቁ ነበር።

እኛ እያልን ያለነው ውሃን የታችኞቹ ሀገራት በብቸኝነት አይቆጣጠሩ ነው። የታችኞቹ ሀገራት ጽንሰ ሐሳብ ውሃውን በብቸኝነት እንጠቀም ነው፤ በላይኞቹ ሀገሮች አካባቢ ያለን ሀገራት የምንለው ደግሞ በጣም ፍትሃዊ በሆነ መንገድ የመጠቀም መብት እናግኝ የሚል ጽንሰ ሐሳብ ነው።

የታችኞቹ ሀገራት አካሔድ ዓለም ላይ ካለው ተሞክሮም በጣም በሚገርም ሁኔታ የሚፋለስ ነው። ለምሳሌ ሚኮንግ (Mekong River) ወንዝ የሚባል ኢሽያ ውስጥ አለ። በዚህ ወንዝ ተፋሰስ ያሉ “ሚኮንግ ወንዝ ኮሚሽን” እንዲቋቋም የሚፈልጉት የታችኞቹ ሀገራት ናቸው። ምክንያቱም ውሃ ከላይ ስለሚመጣ ማለት ነው። እኛ ዘንድ ደግሞ ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኖ ነው የታየው፤ ካለው ሕግም ጭምር የሚጻረር ሆኖ ነው የተገኘው።

በግብጽ በኩል ሰሞኑን ይፋ የተደረገውን ሃሳብ አስተውለናል። ኢትዮጵያ ያላት አቋም በማንኛውም ጊዜ ለመነጋገር በሯ ክፍት መሆኑ ነው። በተለይ ኢኒሼቲቩ ወደኮሚሽን ከመጣ በኋላ እነሱ ከእኛ ጋር ይቀጥላሉ፤ አንገፋቸውም። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ፍትሃዊነትን እየፈለገች ኢ-ፍትሃዊነትን ለማስፈን አትሔድም።

ስለዚህ ፍራቻ ካላቸው በቀጣይ በሚኖሩ መድረኮች ላይ በዚሁ አጋጣሚ የሱዳንም የግብጽም ወንድሞቻችን በተለይ ሁለቱ አቻዎቼ የውሃ ሚኒስትሮች ወደ መድረኩ መጥተው በሃሳብ መነጋገር ሌሎቹንም አፍሪካዊ ወንድሞቻቸውን ማቀፍ እንዲችሉ ጥሪዬን ማስተላለፍ እፈልጋለሁ።

የትብብር ማሕቀፉ ካሉት አንቀጾች መካከል በይደር ስለተቀመጠው አንቀጽ

በትብብር ማሕቀፉ አንቀጽ 14 ቢ ላይ ያለው በይደር የታለፈው የደህንነት ጉዳይ ነው። ወደ ኮሚሽኑ የሚመጣ አካል ሲመጣ አንዱ ሃሳብ የሚሆነው ይኸው ነው ማለት ነው። ይህ ማለት የውሃ ደህንነትን ለሁሉም ሀገሮች እንዴት አድርገን ነው ተጠቃሚ በሚያደርግ ደረጃ ላይ እያበሰልን የምንሔደው በሚል ታስቦ የገባ ነው። ስለዚህ የማንኛውም አባል ሀገር ጥያቄ ችላ የሚባል ሳይሆን በዚህ ውስጥ ተካትቶ የሚሄድ መሆኑንም ለማሳየት በሕግ ማኅቀፉ ላይም ስላስቀመጥን መብታቸው ነው ማለት ነው።

የተፋሰሱ ሀገራት ውሃን በጋራ ከመጠቀም አኳያ

በጋራ መጠቀምን በተመለከተ አስቀድሜ ያነሳኋቸው አንቀጾች ላይ በግልጽ ተቀምጧል። እያንዳንዱ አባል ሀገር ሲያቅድ ምን እንደሚሰራ በጋራ ስምምነት እንስማማበታለን ማለት ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ ላይ ለምሳሌ ለመስኖ ካቀድን ምን ያህል እንደምናወጣ ምን ያህል እንደምንጠቀም ስለሚታወቅ የታችኞቹ ደግሞ በዚያው ልክ ራሳችውን ያስማማሉ።

እንዲህ ስናደርግ የታችኞቹ አይጠቀሙ ማለት አይደለም። የእነርሱንም ታሳቢ አድርጎ ጠቅላላ በዓባይ ላይ ያለው የውሃ መጠን ስንት እንደሆነ ታይቶ እያንዳንዱ ሀገር ለዚያ እንዲሆነው በድርሻው ልክ መጠቀም በሚያስችል ደረጃ ላይ ቴክኒካል ማየትን ይጠይቃል ማለት ነው።

ለምሳሌ የሕዳሴ ግድብን ወስደን ብናይ በጣም በተሳካ ሁኔታ ጨርሰን ስንቀመጥ ባለፉት ዓመታት ሲራገቡ የነበሩ አሉባልታዎች እንደሚጎዳቸውና እንደማይጠቅማቸው እንዲያውም አደጋ እንደሚያመጣባቸው ተብሎ ሲነገር የሰነበተ ጉዳይ ነው። ዛሬ እነርሱ ከሚሉት በተገላቢጦሽ እኛ ባልነው ልክ ተፈጽሞ እናገኘዋለን። ሕዳሴ ሕዳሴ ሆኗል። እነርሱ የሚፈልጉት የውሃ መጠን ምንም ሳይቀንስባቸው ይልቁኑ እነርሱን ተጠቃሚ በሚያደርግ ደረጃ ጎርፍ ሆኖ በየዓመቱ እንደሚሰማ የሚታወቅ ነው። ካርቱም ላይ ችግር ነበር። በዚህ ዓመት ይህ ሁሉ ዝናብ ዘንቦ ካርቱም በጎርፍ አልተጎዳም። ለምን ቢባል የሕዳሴ ግድብ በቂ ውሃ በመያዙ ነው ማለት ነው። ስለዚህ ተጠቃሚ ናቸው።

በጋ ላይ ብናይ ከሕዳሴ በፊት የነበረው የውሃ መጠን የሚሄድላቸው አራት ወይም አምስት እጅ ነው። ከሕዳሴ በኋላ ተጠቃሚ ነው የሚያደርጋቸው። ስለሆነም ኢትዮጵያም ትጠቀማለች፤ እነርሱም ይጠቀማሉ። በዚህ መልኩ ልማቱም ጥቅሙም የጋራ ይሆናል ማለት ነው። ስለዚህ ቲዎሪ ብቻ ሳይሆን በተግባር መሬት ላይ ስላለን የትብብር ማኅቀፉ የሚደግፈው ይህን ነው። የሚያጠናክረውም ይህንኑ ነው፡።

ዓባይን ከኃይል ማመንጫነት ባሻገር

እንግዲህ በማንኛውም ፕሮጀክት ላይ የመጀመሪያው ትልቁ ሥራ የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ ይደረጋል። በትብብር ማሕቀፉ ላይም አንዱ አንቀጻችን ይህ ነው። ማንኛውም የሚሰራ ሥራ ኢትዮጵያ የምታለማው፤ ሱዳን የምታለማው፤ ዑጋንዳ የምታለማው በታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት ላይ ምንም ተጽዕኖ ማድረስ መቻል የለበትም። በዚህ ደረጃ መሰረት ፕሮጀክቶች እየተገመገሙ ያልፋሉ።

ይህ ትልቁ ነገር ሲሆን፣ እዚያ አካባቢ ምን ያህል መሬት ለመስኖ እንደሚለማ ማየት በጣም ያስፈልጋል። ሌላው ልማት የሚካሔደው ውሃ ስላለ ብቻ አይደለም፤ መሬቱ ለመስኖ የሚመች መሆኑን ማየት በጣም ያስፈልጋል። እዛ አካባቢ የምናለማቸው እና ለዚያ አካባቢ መሆን የሚችል የሰብል ዓይነቶች መኖራቸውም ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል። እኛ እስካሁን ባለን መረጃ በዓባይ ተፋሰስ ውስጥ በጣም ብዙ አቅሞች አሉ። በተለይ በታችኛው አካባቢ ብናይ ወደ ዳቡስ አካባቢ በጣም ትልቅ ሥራዎች አሉን። ወደ በለስ አካባቢም በጣም ሰፊ መሬት አለን። ይህንን ደግሞ ኢትዮጵያ የመጠቀም መብት አላት።

ነገር ግን ስንጠቀም ውሃውን አድርቀን ሳይሆን ቴክኖሎጂን በጣም መሰረት ባደረገ መልኩ እና ውሃ በሚቆጠብ መንገድ ነው። ስለሆነም ልማቶቻችን የታችኞቹን ታሳቢ አድርገን የምንሰራቸው ሥራዎች ይሆናሉ፤ በዚህ መልኩም ይቀጥላሉ ማለት ነው። ግብርና ከተባለ እርሻ ብቻ አይደለም። ዓሳ እርባታ ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡። ግድቦች ካሉ እኛ ዓሳ እዚያ አካባቢ እያመረትንና ትክክለኛ ሥራ እየተፈጠረ ለሌሎች ሀገሮችም በረከት ሆነን ኃይልም እያመነጨን መጠቀም እንችላለን።

ውሃ ማልማትን በተመለከተ

ውሃውን በተመለከተ ምንም የማያመነጩ ሀገራት አሉ፤ ነገር ግን ተጠቃሚ ናቸው። እኛ በዚያ ልክ ውሃ እንዲያመነጩ አናስገድድም። ምክንያቱም ጉዳዩ የተፈጥሮ ጉዳይ ነው፤ ዜጎች ናቸው፤ የእኛ ወንድሞች ናቸው። ከዓባይ/ ናይል የመጠቀም መብትም አላቸው ማለት ነው። ስለዚህ እዚህ ጋ እኛ በምናደርጋቸው ሥራዎቻችን ውሃንም እኛ እናጎለብታለን። እናለማለን፤ ለምሳሌ አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን የዛሬ አምስትና ስድስት ዓመት ትልቁ ያስጀመሩትና ውሃ ሀብት ላይ ሲሰራበት የቆየ ነው። ስለዚህ እነዚያን ያህል ችግኞችን በዓባይ ተፋሰስ በተከልን ቁጥር በጣም ከፍተኛ የሆነ የውሃ መጠን እንዲመነጭ እንደርጋለን። በጣም ከፍተኛ የሆነ የውሃ መጠን ሲመጣ ደግሞ በዚያ አካባቢ የሚመጣውን የአፈር መሸርሸር እንቀንሳለን። ስለዚህ ኩልል ያለ በጣም ንጹህ ውሃ ለወንድሞቻችን ይደርሳል። እኛ ስንባረክ ለእነሱም በረከት እንሆናለን። ይህ ደግሞ በማኅቀፉም ውስጥ ጭምር አለ። እና የዚህ ማኅቀፍ ስምምነት የምናወራውን እናደርጋለን ሳይሆን በጣም ብዙዎችን ተግብረን መሬት ላይ በመታየት ላይ ናቸው።

ማሕቀፉ የታችኞቹን ተፋሰስ ሀገራት አስገዳጅ ያደርጋል?

አስገዳጅ ነው ወይ ለተባለው አንዱ የዚህ ማኅቀፍ ይዘት መረጃ መቀያየር ነው፤ መረጃ ማለት የውሃ መጠን ብቻ ሳይሆን ፕሮጀክቶችን ነው፡። መሬት ላይ ምን አለ? የምንፈልገው ምንድን ነው? በቀጣይ የምናለማው ምንድን ነው? የሚሉ መረጃዎችን መለዋወጥ የግድ ይላል። እነርሱ (የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት) ወደ መድረኩ መምጣት የማይፈልጉት ለዚያ ነው። የሚፈርሙ ከሆነ ይመጣሉ። ደግሞ መረጃውን በሰጡ ቁጥር ተጠቃሚ ይሆናሉ። ምክንያቱም የሚሄድላቸው ውሃ መጠን ያላቸውን የውሃ ፍላጎት ታሳቢ ስለሚያደርግላቸው ማለት ነው። እሱ ከዚያ አኳያ የሚታይ ነው።

የኮሚሽኑ ተጠሪነት

ከአፍሪካ ኅብረት ጋር ያለው ግንኙነት እያንዳንዱ ሀገር የትብብር ማሕቀፉን በፓርላማው ካጸደቀ በኋላ ወደ አፍሪካ ኅብረት ያመጣል። ከመጣ በኋላ ከ60 ቀን በኋላ ወደ ሕግ እየገባ ይሄዳል። የጥቅምት 3ቱ ቀን ዋና ዓላማ ሱዳን ስድስተኛ ሀገር ናት፤ ሱዳን ካስገባች በኋላ ስድስት በመሙላቱ ባለን አንቀጽ መሰረት ሕግ ይሆናል ተብሎ ስለሚታሰብ ነው። ከዚያ በኋላ የሚኖረው ማንኛውም ዓይነት ቅሬታ ማንኛውም ዓይነት ጉዳይ ካለ ወደ አፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር መሄድን እንደ አማራጭ ማየት ይቻላል።

ትልቁ ነገር ግን በእያንዳንዱ ተፋሰስ ሀገራት መካከል ያሉ ጉዳዮች መፈታት ያለበት በኮሚሽን ደረጃ ነው። ማንም ሰው የራሱን ቅሬታና የራሱን ሃሳብ እንዲሁም የተለየ ነገር ሲያቀርብ የሚያቀርብበት ሁኔታ ሥርዓትና ሕግ አለው። ያንን ተከትሎ ወደዚያ መሄድ ይችላል።

ሀገራት ከገቡም በኋላ መውጣት ይችላሉ። በስምምነቱ ላይ ብናይ ማንኛውም ወደ ሥርዓቱ ገብቶ በሥራ ላይ ያለ ሰው ሥርዓቱን ተከትሎ ደግሞ አልፈልግም ካለ እና ካላዋጣው ያንን የማድረግ ነገሮች አሉት ማለት ነው። እዚህ ላይ ትልቁ ነገር ከመረጃ ልውውጥ ጋር ከታችኞቹም እየለማ ያለውና በቀጣይም የሚለማ ያለው የውሃ መጠን በቀጣይም ሊመጣ የሚችል የውሃ መጠንን በፕላትፎርሙ ደረጃ ይሰራል። ይህ ደግሞ ትልቁን ሥራ የሚወጣው ኮሚሽኑ ነው። በኮሚሽኑ ውስጥ ደግሞ የከፍተኛ ሥራ ባለቤቶች ሚኒስትሮች ናቸው። የአስራ አንዱ ሀገሮች የውሃ ሚኒስትሮች ካውንስል ናቸው። ስለዚህ ምክር ቤት አለው ማለት ነው። በዚያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስር ሴክተራል አድቫይዘር ኮሚቴ የሚባል አለ። ባለሙያዎች ከሁሉም ሀገር ይወጣጡና ቴክኒካሊ መታየት ያለባቸውን ጉዳይ እነርሱ ከጨረሱ በኋላ ለሚኒስትሮች ቀርቦ ለውሳኔ ይሆናል። አንዳንድ ጉዳዮች አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ወደ ሀገር መሪዎች እንዲሔዱ ሊደረጉ ይችላሉ። እሱ ግን ግዴታ ሳይሆን እንደ አስፈላጊነቱ የሚሔድ ነው።

ኮሚሽኑን ስናቋቋም የሚሆነው ዑጋንዳ ኢንቴቤ ላይ ነው። የዚህ ኮሚሽን ቅርንጫፎች የተለያየ ቦታ ይኖራሉ። ለምሳሌ አሁን ባለው ደረጃ ኢንትሮ የሚባል አለ። ኢንትሮ ማለት የምስራቅ አፍሪካ ቴክኒካል ሪጂናል ኦፊስ ማለት ነው። ስለዚህ የሱዳንም የደቡብ ሱዳንም የኢትዮጵያም የግብጽም ጨምሮ የእነሱ ባለሙያዎች የሚሳተፉበት በጋራ የምንመራው የራሱ የሆነ ቅርንጫፎች አሉት።

የቀሩት ሀገሮች ከዚህ በኋላ በርግጠኝነት ይፈርማሉ፤ ያጸድቁታልም። እኛ በዲፕሎማሲ የምንሰራው በምንገናኝበት ጊዜ ከውሃ ሚኒስትሮች ጋር እንነጋገርበታለን፤ በተለይ ከማንም በላይ የኬንያ ወገኖቻችን ተጠቃሚዎች ናቸው። ምክንያቱም የሚገኙት የላይኞቹ ላይ ነው። ስለዚህ እንደ ኢትዮጵያ ውሃ ሰጪ ናቸው እንጂ ተቀባይ አይደሉም። ወደ ዓባይ ወይም ወደ ናይል ለማጽደቅ ሲመጡ ተጠቃሚ ይሆናሉ፤ እንኳን ፊርማ ጀምረው ያላጸደቁ ቀርተው እኛ የምንጠብቀው የግብጽ ወገኖቻችንንና የሱዳን ወገኖቻችንንም ወደማሕቀፉ እንዲመጡ ነው። ምክንያቱም በቀጣናው አካባቢ በሁሉም አባል ሀገራት ላይ ያለው ሕዝብ ብዛት የምናስተዳድርበት ብቸኛው መንገድ የተፈጥሮ ሀብትን በመጠቀም ነው። ሰው ያለው አማራጭ የአየር ንብረት እየተዛባ በሄደ ቁጥር መስኖ ነው። መስኖ ለመጠቀም ሲኬድ ደግሞ የሚታየው ውሃ ነው።

ምስጋና

በመጨረሻም ኢትዮጵያውያን በተለይም በትብብር ማሕቀፉ ስምምነት ላይ አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ የነበሩ በሙሉ በናይል ወንዝ ተፋሰስ ውስጥ ያላችሁ ማኅበረሰብ እንኳን ደስ ያላችሁ። ምክንያቱም በናይል ወንዝ ተፋሰስ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በጣም ብዙ ሀገሮችን የሚያሳትፍ ሕግ፣ ሥርዓት፣ ማሕቀፍ መፈረም በመቻሉ ይህ ደስታ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የተፋሰሱ አባል ሀገራትም ጭምር ከፍተኛ ደስታ ነውና እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እወዳለሁ።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 7/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You