ሲፌኔ ተክሉ ትባላለች፡፡ በ2016 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና በተፈጥሮ ሳይንስ 575 ያመጣች ናት፡፡ ይህም የሀገሪቱ ከፍተኛ ውጤት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ተማሪ ሲፌኔ በኦግዚሊየም ካቶሊክ ትምህርት ቤት ተማሪ የነበረች ሲሆን ጊዜን መሠረት ያደረገ እቅድ በማውጣት ረዘም ላለ ጊዜ ማንበቤ ለዚህ ውጤት አብቅቶኛል ስትል ትናገራለች፡፡
ሲፌን፤ ብዙውን ጊዜ ትምህርት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መቆየት፣ በቡድን ማጥናት በተለይም ደግሞ ፈተና ላይ የሚቀርቡ ሁሉም የትምህርት ዓይነቶችና ምዕራፎች ብዛት በመለየትና ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ለዚህ ውጤት መምጣት ምክንያት ሆኗል ትላለች ፡፡ ያመጣሁት ውጤት ከግል ጥረቴ በተጨማሪ የቤተሰብና መምህራኖች ድጋፍ ትልቅ አስተዋፅዖ ነበረው ብላለች፡፡
በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ አፕላይድ ኒውትሬሽን በማጥናት የሥርዓተ ምግብ ባለሙያ መሆን እንደምትፈልግ ገልጻ፤ አሁን ላይ በዩቲዩብና በተለያዩ ሌሎች ፕሮጀክቶች ተማሪዎችን ለማገዝ በማስተማር ላይ እንዳለች ታስረዳለች።
ፈተና የሚወጣበት ምዕራፍ ስለማይታወቅ በተቻለ መጠን ሁሉንም ምዕራፎች ለመሸፈን ተማሪዎች ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል የምትለው ተማሪ ሲፌኔ፤ ለዚህም ቀጣይ ተፈታኞች ጊዜያቸውን በማጣጣም በእቅድ ማጥናት ጥሩ ውጤት እንዲያመጡ ይረዳቸዋል ስትል መክራለች፡፡
ተማሪ ፍሪና ሠላምም የኢትዮ ፓረንት ትምህርት ቤት ተማሪ ስትሆን ያመጣችው ውጤት 538 ነው ይህም በማኅበራዊ ሳይንስ ከፍተኛ ውጤት ያስገኘች አስብሏታል።
ያገኘሁት ከፍተኛ ውጤት የጥረቴ ፍሬ ነው የምትለው ተማሪዋ እስከ መጨረሻው የፈተና ሰዓት ድረስ ከእኔ የሚጠበቀውን አድርጌአለሁ ስትል ያለፈውን ጊዜ ታስታውሳለች፡፡
በመምህራን በኩል የነበረው ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑ ይህን ውጤት እንዳመጣ ረድቶኛል፡፡ በተለይም መምህራን ዓመቱን ሙሉ ለሀገር አቀፍ ፈተናው እንድንዘጋጅ የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል ብላለች፡፡
በቀጣይ በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ ምን መማር እንዳሰበች ያልወሰነችው ተማሪዋ ሕዝብን የሚጠቅም ሀገርን የሚያኮራ እንዲሁም እራሴን የሚያስደስት ቦታ ላይ እንደምሠራ ቃል እገባለሁ ስትልም ተናግራለች፡፡
የቀጣይ ተፈታኞች ጥናቱ እንዲሁም ፈተናው ቀላል እንደማይሆን አሳስባ ከእነሱ የሚጠበቀውን ሁሉ ማድረግ እንዳለባቸውም ምክረ ሃሳቧን አስቀምጣለች፡፡
ትምህርትን በአግባቡ ከማጥናት ባሻገርም በፈተና ሰዓትም ምንም አይነት ፍራቻም ሆነ መወዛገብ ሳይኖር በተረጋጋ መንፈስ ወደ ፈተና ቢገቡ እንደኔ ጥሩ ውጤት ማምጣት ይችላሉ ብላለች፡፡
ተማሪዎቻቸውን ሙሉ በሙሉ ካሳለፉ የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቤቶች አንዱ የሆነው የየኔታ አካዳሚ ጄኔራል ማናጀር ወይዘሮ ጥሩወርቅ አየለ፤ ትምህርት ቤቱ በ2015 እንዲሁም በ2016 የትምህርት ዘመን 12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ተማሪዎችን ሙሉ በሙሉ ማሳለፍ ችሏል ይላሉ፡፡
የኔታ አካዳሚ ተማሪዎች ላይ ከስር የሚሠራ በመሆኑ ይህ ውጤት ሊገኝ ችሏል ያሉት ወይዘሮ ጥሩወርቅ ትምህርት ቤቱ ከጥሩ ትምህርት ከመስጠት ባለፈ ሥነምግባር ላይ በትኩረት ይሠራል ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
በተለይም ሀገር አቀፍ ፈተናው ላይ በቂ ዝግጅት መደረጉንና ተማሪዎች ብዙ ያለፉ ዓመት ፈተናዎች እንዲሠሩ መደረጉን ገልጸው፤ የመጣው ውጤት የምንጠብቀው ነው ይላሉ፡፡
ሌሎች ትምህርት ቤቶች ከኔታ አካዳሚ በተለይም ተማሪዎች ላይ ከስር ጀምሮ መሥራትና ከትምህርቱ በተጨማሪ ሥነምግባር ላይ መሥራት እንደሚገባ ተሞክሮ መውሰድ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡
በ2016 የትምህርት ዘመን ለሀገር አቀፍ ፈተና ከተቀመጡ 674 ሺህ 823 ተማሪዎች ውስጥ 36 ሺህ 409 ወይም 5 ነጥብ 4 በመቶ የማለፊያ ውጤት ማግኘታቸው ትምህርት ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
በአዲስ አበባ በ2016 ዓ.ም 21 ነጥብ 4 በመቶ ተማሪዎች የማለፊያ ውጤት ማምጣታቸውንና ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ5 በመቶ እድገት መመዝገቡን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡
ከሰሞኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2016 የትምህርት ዘመን በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ በሀገር አቀፍ ፈተና 500 እና ከዚያ በላይ የሆነ ውጤት ላስመዘገቡ 484 የከተማዋ ተማሪዎች እንዲሁም ተማሪዎቻቸውን ሙሉ በሙሉ ላሳለፉ የከተማዋ ትምህርት ቤቶች እውቅናና ሽልማት አበርክቷል፡፡ ተማሪ ሲፌኔ ተክሉና ተማሪ ፍሪና ሠላም ሽልማቱ ከተበረከተላቸው ተማሪዎች ውስጥ ግንባር ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡
በዚሁ ዓመት ፈተናውን ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል ከ600 በተፈጥሮ ሳይንስ ከአዲስ አበባ ኦግዚሊየም ካቴድራል 575 በሴት ተማሪ በማኅበራዊ ሳይንስ ከኢትዮፓረንትስ 538 ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡ ተገልጿል፡፡
ዳግማዊት አበበ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 7/2017 ዓ.ም