አዲስ አበባ፡- በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሦስት ወራት የቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ምርት የወጪ ንግድ 522 ሚሊዮን ዶላር ያህል ገቢ መገኘቱን የቡናና ሻይ ባለሥልጣን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ ለኢፕድ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፤ በበጀት ዓመቱ ሦስት ወራት 115 ሺህ 851 ቶን በላይ የቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ምርት ወደ ውጭ በመላክ 522 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገቢ ተገኝቷል፡፡
አፈጻጸሙ ባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተላከው ጋር ሲነጻጸር በመጠን 69 በመቶ እና በገቢ የ46 በመቶ ጭማሪ መመዝገቡን አስታውቋል።
ከገቢው ከፍተኛ ድርሻ የሚይዘው ቡና ሲሆን፤ በበጀት ዓመቱ ሦስት ወራት 115 ሺህ 174 ነጥብ 75 ቶን ቡና በመላክ 519 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መገኘቱን ባለሥልጣኑ ገልጿል። አፈፃፀሙ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በመጠን 70 በመቶ እና በገቢ 47 በመቶ ጭማሪ መመዝገቡን አመላክቷል።
በ2017 በጀት ዓመት ሦስት ወራት የተላከው ቡና በመዳረሻ ሀገራት ሲታይ ጀርመን በመጠን 28 ሺህ 398 ነጥብ 68 ቶን የኢትዮጵያን ቡና በመቀበል አንደኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ተጠቁሟል።
ሳዑዲ ዓረቢያ 16 ሺህ 838 ቶን በላይ ቡና እንዲሁም ቤልጂዬም 12 ሺህ 503 ቶን በላይ የኢትዮጵያን ቡና በመቀበል ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃ የያዙ ሀገራት መሆናቸው ታውቋል።
ከአሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓን፣ ዩናይትድ ዓረብ ኤሜሬትስ፣ ጣሊያን፣ ጆርዳን እና ፈረንሳይ የኢትዮጵያን ቡና በመግዛት ከአራተኛ እስከ 10 ያለውን ደረጃ ይዘዋል።
ነፃነት ዓለሙ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 7/2017 ዓ.ም