አዲስ አበባ፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የግብይትና የክፍያ ሥርዓቱ መዘመኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ያስሚን ወሀብረቢ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አካዳሚ በአምስተኛ ዙር በአራት ዘርፎች ያሠለጠናቸውን 85 ሠልጣኞች ከትናንት በስቲያ ሲያስመርቅ እንደተናገሩት፤ ተቋሙ የግብይት እና የክፍያ ሥርዓቱን በማዘመን ውጤታማ ሥራ እየሠራ ነው።
ተቋሙ እያከናወነ ከሚገኘው ሥራ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አካዳሚን በማቋቋም በዘርፉ እውቀት ያለው ኃይል እያፈራ መሆኑን ገልጸው፤ አካዳሚው የተጣለበትን ኃላፊነት በመወጣት ለ5ኛ ጊዜ እያስመረቀ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለጻ ተመራቂዎች የኢትዮጵያን የወጪ ንግድ ከማሳካት አንጻር ትልቅ ኃላፊነት ይጠብቃቸዋል።
ከገበያው ተጠቃሚ ለመሆን እና የተሻለ ገቢ ለማግኘት ጥራትን ማስጠበቅ የግድ መሆኑን ተናግረው፤ ተመራቂዎች ጥራትን በማስጠበቅ ሚናችሁ አይተኬ ነው ብለዋል።
አካዳሚው በጥራት ቁጥጥር እውቀት ያለው የሰው ኃይል ለማፍራት ታስቦ የተቋቋመ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይም በርካታ የጥራት ቁጥጥር ባለሙያዎችን እንደሚያፈራ አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኝ ነገራ በበኩላቸው እንደተናገሩት በኢትዮጵያ ምርት እና ምርታማነት እያደገ ስለመጣ በየጊዜው አዳዲስ ምርቶች የግብይት ሥርዓቱን ይቀላቀላሉ።
እንደ አገር በግብይት ሥርዓቱ ጥራት ላይ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ በአካዳሚው እየተሰጠ ያለው ሥልጠና ስለጥራት ያለውን ግንዛቤ የሚያሳድግ መሆኑን ገልጸዋል።
ስለጥራት በሚገባ የተረዱ ባለሙያዎችን ማፍራት ተወዳዳሪነትን እና ገቢን እንደሚያሳድግም ጠቁመው፤ ስለጥራት ማወቅ ገቢን እና ተወዳዳሪነትን እንደሚያሳድግ የሚያሳደግ ስለሆነ የተሰጠው ሥልጠና ስለ ጥራት ያለውን ፅንሰ ሀሳብ የሚያጎለበት መሆኑን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በ16 ዓመታት ያካበተውን ከፍተኛ ልምድ ሌሎች እንዲቀስሙት በማሰብ አካዳሚውን በ2015 ዓመተ ምሕረት ማቋቋሙን ተናግረው፤ ከሀገር ውስጥ በተጨማሪ በአንጎላም ሥልጠና መሠጠቱን አመላክተዋል።
ሠልጣኞቹ በቡና ጥራት ቁጥጥርና ቅምሻ፣ በጥራጥሬና ቅባት ጥራት ቁጥጥር፣ በኤሌክትሮኒክስ ግብይት እና በኤሌክትሮኒክስ የጨረታ ሥርዓት ከአንድ ሳምንት እስከ 3 ወራት ሥልጠና የተከታተሉ መሆናቸው ታውቋል። ሥልጠናው በቀን፣ በማታ እና በቅዳሜና እሁድ ፕሮግራሞች መሠጠቱም ተገልጿል።
መዓዛ ማሞ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 7/2017 ዓ.ም