ቢሾፍቱ:- የኢትዮጵያ አየር ኃይል በቴክኖሎጂ የተደራጀ አቅም ለአፍሪካ ሀገሮችም ምሳሌ እንደሚሆን ተጠቆመ። በአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ጉባኤ ኢትዮጵያ አፍሪካዊ አጀንዳን ማሳካት የምትችልበትን አቅም ማሳየቷ ተመልክቷል።
የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ጉባኤ ተሳታፊዎች በትላንትናው እለት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ አየር ኃይልንና የቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪን ጎብኝተዋል።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ በጉብኝት መርሐ ግብሩ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፣ ከጉባኤው አጀንዳዎች አንዱ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን በጋራ ማከናወን ላይ ያተኮረ ነው። ኢትዮጵያም እንደ ሀገር ረጅም እድሜ ያስቆጠሩ ተቋማት ያሏት ሲሆን፣ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፣ በተቋሙ ውስጥ ያለውን የተደራጀ አቅም ለሌሎችም ምሳሌ ሊሆን የሚችል ነው።
ኢትዮጵያ በተለይም ባለፉት ስድስት ዓመታት በፀጥታው ዘርፍ የተደረገውን ሪፎርም በአግባቡ የተጠቀመችበትና ያሳየችበት ነው። በፀጥታ ተቋማት ውስጥ የተደረጉ የሪፎርም ሥራዎች ተቋማቱ ከኢትዮጵያ አልፎ አፍሪካዊ ተቋም የመሆን አቅም እንዳላቸው ተናግረዋል። ከዚህ ውስም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ አየር ኃይል አንዱ ነው ብለዋል።
በአየር ኃይሉ ሌሎች አፍሪካውያን ሥልጠና ማግኘታቸውን አስታውሰው፣ ትብብሩና በየሀገሩ ያለውን አቅም መጠቀም ፋይዳው ጉልህ መሆኑን ያመላክታል ነው ያሉት። ተቋሙ እድሜ ብቻ ሳይሆን ትልቅ አቅም ያለውና በተለይም በአሁን ወቅት በቴክኖሎጂ የተደራጀና በበርካታ የልማት ሥራዎች ላይ የራሱን አስተዋፅዖ እያበረከት እንዳለ ገልጸዋል።
ይህ የተቋም ቁመና ኢትዮጵያ እንደለመደችው የሁሉንም ሀገራት አየር ኃይሎች አሊያም በዘርፉ መሠልጠን ለሚፈልግ ሁሉ ማሠልጠን እንደምትችልና ከዚህ ቀደም ያላት ፍላጎት ያልተቀየረ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ቅድሚያ ለአፍሪካ እንደምትሰጥ በመግለጽ፣ ተባብሮ መሥራት ከተቻለ አንድ አፍሪካዊ የተጠባባቂ ኃይል ሊኖር ይችላል ተብሎ የተቀመጠውን ግብ ማሳካት እንደሚቻል ጠቁመዋል። ጉብኝቱም ኢትዮጵያ ይህንን ሕልም ማሳካት እንደሚቻል ያሳየችበት እንደሆነም አመላክተዋል።
በመከላከያ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን የአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪውና የሎጂስቲክ አቅም ምን ያህል እያደገ እንደመጣና ይህንንም አቅም ለሚፈልጉ ሀገራት በጥገናም ሆነ በማዘመን ረገድ ኢትዮጵያ ማገዝ እንደምትችል ነው የገለጹት። በዚህም ማንኛውም ደረጃ ያለው አፍሪካዊ አጀንዳ መሳካት እንደሚቻል በተግባር የታየበት ነው ያሉት።
ከጉባኤው ጎንን ለጎንን አልጄሪያ፣ ሊቢያና ሱዳንን ጨምሮ ከተለያዩ ሀገራት ጋር አብሮ መሥራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ፍሬያማ የጎንዮሽ ውይይቶች መደረጋቸውንም ሚኒስትሯ ገልጸዋል። በዚህም ውጤታማ ወታደራዊ የዲፕሎማሲ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
የዩጋንዳ መከላከያ ሚኒስትር ጃኮብ ኦቦት፣ ኢትዮጵያ ያሰናዳቸው የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ጉባኤ እንዲሁም የአየር ኃይሉ ጉብኝት ታሪካዊ ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አጀንዳ በቁርጠኝነት እየሠራች መሆኗን ያየንበት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የደቡብ አፍሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ባንቱ ሆሎሚጋ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ጉባኤን ማዘጋጀቷ አሕጉራዊ እና ቀጣናዊ የሠላምና ፀጥታ ጉዳዮችን ለማጠናከር አይነተኛ ሚና ያለው ነው በማለት፣ ሀገሪቷ በወታደራዊ ዘርፍ ያላት ትልቅ አቅምም ለሌሎች አቻ ሀገራት ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል። ሁለቱ ሀገራት ትብብራቸውን የሚያጠናክሩበት መድረክ እንደነበረም አንስተዋል።
የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ጉባኤ “አፍሪካ በጠንካራ አንድነት፣ ለሁለንተናዊ ፀጥታና ሠላም” በሚል መሪ ሀሳብ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ከትላንት በስቲያ ጀምሮ እየተካሄደ ሲሆን፣ የጉባኤው ተሳታፊዎች በትላንትናው እለት ቢሾፍቱ በሚገኘው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ አየር ኃይል በመገኘት የሥልጠና እና የጥገና ማዕከላትን እንዲሁም የበረራ ትምህርት ቤትን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድን ጨምሮ ከአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ የመከላከያ ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና ወታደራዊ አታሼዎች ተሳትፈዋል።
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 7 ቀን 2017 ዓ.ም