አዲስ አበባ፡– የናይል ተፋሰስ የትብብር ማሕቀፍ ስምምነት ወደ ተግባር መግባቱ በዓባይ ውሃ ኢትዮጵያ ላይ የሚቀርቡ ምክንያት አልባ ክሶችን የሚያስቀር መሆኑን በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ሀብት ምሕንድስና ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር መኮንን አያና አስታወቁ፡፡
ፕሮፌሰር መኮንን አያና ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የናይል ተፋሰስ የትብብር ማሕቀፍ ስምምነት ወደ አስገዳጅ ተግባር መግባቱ የዓባይ ውሃን ለብቻቸው የሚጠቀሙ ሀገራትን የበላይነት የሚያስቀር ነው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ የተፋሰሱ ሀገራትን የጋራ ተጠቃሚነትን ያረጋግጣል። ተፋሰሱን በጋራ የመጠበቅና የማልማት ሥራዎችን ሕጋዊ ማሕቀፍ እንዲኖራቸው የሚያደርግ ጭምር ነው፡፡
የማሕቀፍ ስምምነቱ ወደ ተግባር መግባቱ ኢትዮጵያ ወንዙን በመጠቀም ለመልማት የምታደርገውን ጥረት ሕጋዊ ከማድረጉ በላይ በየጊዜው የሚቀርቡባትን ክሶች ውድቅ የሚያደርግና የሚያስቀር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
እንደ ተመራማሪው ማብራሪያ፤ የናይል ተፋሰስ የትብብር ማሕቀፍ ስምምነት የተጀመረው እ.ኤ.አ ከ1997 ጀምሮ ነው፡፡ የናይል ቤዚን ኢኒሼቲቪ ለአስር ዓመታት ስምምነትና ውይይት ተደርጎበታል፡፡ ይህም በአባል ሀገራት መካከል መተማመን እንዲፈጠርና መወያየት እንዲችሉ አስችሏል፡፡ በመጨረሻም የናይል ተፋሰስ የትብብር ማሕቀፍ ስምምነት ወደ አስገዳጅ ተግባር መግባቱ የቅኝ ግዛት ውሎችን ውድቅ በማድረግ የጋራ ተጠቃሚነትን እንደሚያረጋግጥ ነው፡፡
የናይል የትብብር ስምምነት ተፈጻሚ መሆን የኢትዮጵያን የመልማት መብት ሌሎችን በማይጎዳ መልክ መሆኑን ያረጋግጣል ያሉት ተመራማሪው፤ ኢትዮጵያ ሁሌም ዓለም አቀፍ መርሆችን አጥብቃ ታከብራለች፡፡ የስምምነት ማሕቀፉ ተቋማዊ ሰውነት የሚኖረው በመሆኑ ለኢትዮጵያ ያለው ትርጉም ትልቅ ነው ብለዋል፡፡
የትብብር ማሕቀፍ ስምምነቱ ወደ አስገዳጅ ተግባር መግባቱ አግባብነት የሌላቸው ውንጀላዎችን ተቀባይነት ያሳጣል ያሉት ምሑሩ፤ በበላይነት እንጠቀም ከሚሉት ሀገራት ውጭ ለሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት ጉልህ ጠቀሜታ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡
በዓለም ላይ ሁለትና ከሁለት ሀገራት በላይ የሚያቋርጡ 276 ያህል ወንዞች መኖራቸውን የሚገልጹት ፕሮፌሰሩ መኮንን፤ ብዙዎች ግጭት የለባቸውም፡፡ ግጭት የሚስተዋልባቸው ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ኮሚሽን መሥርተው በጋራ ማስተዳደር በመቻላቸው ችግሮችን ቀርፈዋል፤ የጋራ ተጠቃሚነታቸውንም አረጋግጠዋል፡፡ የኢትዮጵያ ፍላጎትም ይሄው መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
የናይል ተፋሰስ የትብብር ማሕቀፍ በይፋ ወደ ተግባር መግባቱ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ የጥረት ውጤት መሆኑን አመልክተዋል፡፡
እንደ ፕሮፌሰር አያኖ ገለጻ፤ ግብጽና ሱዳን የትብብር ማሕቀፉን አንቀበልም እያሉ ነው፡፡ የዓባይን ወንዝ ለብቻቸው የሚጠቀሙበት በመሆኑ የጋራ ተጠቃሚነትን አልፈልጉትም፡፡ በቅኝ ግዛት ወቅት የወጡ ስምምነቶችን በማስጠበቅ የኢ- ፍትሐዊ ተጠቃሚነታቸውን የማስቀጠል ፍላጎት አላቸው፡፡
ነገር ግን ኮሚሽኑ ወደ ሥራ ሲገባና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አጠቃቀም ላይ ዕቅድ አውጥቶ መሥራት ሲጀምር እንደሚጠቅማቸው በመገንዘብ ተገደውና ወደው ሊፈርሙና ሊያፀድቁ ይችላሉ ብለዋል፡፡
ወንዙን በትብብር የመጠበቅና የመጠቀም ጉዳይ ለሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት አዋጭ ነው የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ ግብፅና ሱዳን አምነውና ተገደው ወደ ኮሚሽኑ ይገባሉ። ኬንያ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ሱዳን ፈርመው ያላፀደቁ ሀገራት በመሆናቸው ኢትዮጵያ የማግባባት ሥራ መሥራትና ኮሚሽኑንን ማጠናከር እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
ግብፅን ከማሳመን ፈርመው ያላፀደቁ ሀገራት እንዲያፀድቁ ማድረግ ጥሩ አማራጭ መሆኑን አመልክተው፤ ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ሥራዋን በማጠናከር የፈረሙ ሀገራት እንዲያፀድቁ በማግባባት ውኃውን በብቸኝነት መጠቀም የሚፈልጉ ሀገራት ጉልበትን ማመናመን ይኖርባታል ነው ያሉት፡፡
የናይል ተፋሰስ የትብብር ማሕቀፍ በይፋ ወደ ተግባር በመግባቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነት እንደሚኖረው ገልጸው፤ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቷን ውጤታማ መሆኑን አንዱ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሞገስ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 7 ቀን 2017 ዓ.ም