አዲስ አበባ፡- ማንኛውም የሕንጻ ግንባታዎች ሲከናወኑ የመሬት መንቀጥቀጥን የሚቋቋሙ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ በሰመራ ዩኒቨርሲቲ የፊዚክስ መምህሩ ፍሬወለጋ ገለታ ገለጹ፡፡
መምህሩ ፍሬወለጋ ገለታ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የሕንጻዎች ግንባታዎች ጂኦሎጂካል መረጃን መሠረት ያደረጉና የመሬት መንቀጥቀጥ ቢከሰት መቋቋም የሚችሉ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይገባል።
ሰሞኑን በአዋሽ ፈንታሌ አካባቢ ያጋጠመው የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረት አዲስ አበባ ድረስ መሰማቱን አስታውሰው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የመሬት መንቀጥቀጥ ድጋሚ ሊከሰት ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አመላክተዋል።
ትላልቅ ሕንጻዎች በሚገነቡበት ወቅት ጂኦሎጂካል መረጃን መሠረት በማድረግ እንዲሁም የመሬት መንቀጥቀጥን መከላከል የሚያስችል አሠራርን ሊከተሉ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
አስፈላጊው የአፈር ምርመራና ጥናት በማካሄድ የመሬት መንቀጥቀጥ ቢከሰት እንኳን ሊሰነጠቅ የማይችል ጠንካራ ሕንፃ መገንባት የሁልጊዜም ሥራ ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመው፤ ከአካባቢው ሁኔታ ጋር የተዛመደና በጥናት ላይ የተመሠረተ ግንባታን በማካሄድ አደጋዎችን መቀነስ እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።
የመሬት መንቀጥቀጥ በአለቶች ግጭትና መላቀቅ፣ በእሳተ-ገሞራ ሂደት፣ በኬሚካልና ኒውክሌር ፍንዳታ እንዲሁም በሰው ሠራሽ መንገድ ሊከሰት እንደሚችል አስረድተዋል።
ከሰሞኑ የደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ በቀጣይም ሊከሰት ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል። እንደ ፍሬወለጋ ገለጻ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ በዚህ ጊዜ ይከሰታል ብሎ መገመት ባይቻልም ጥንቃቄ ማድረጉ ተገቢ ነው፡፡
በሰመራ ዩኒቨርሲቲ የተዋቀረ የጥናት ቡድን የመሬት መንቀጥቀጥ በተከሰተበት አካባቢ በመሄድ ምልከታ ማድረጋቸውን እና በቀጣይም ጥናትና ምርምር በማድረግ ለሚመለከተው ባለድርሻ አካላት ለማድረስ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡
የአፋር ማኅበረሰብ ከቦታ ቦታ እየሄደ የሚኖር ማኅበረሰብ በመሆኑ ጉዳት እንዳይደርስባቸው የማስገንዘብ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል፡፡
የመሬት መንቀጥቀጥ በሚከሰትበት ወቅት ኅብረተሰቡ ፎቅ ላይ ካሉ ወደ ኮለን መጠጋት መሬት ላይ ከሆኑ ደግሞ ከኤሌክትሪክ ማማዎች በመራቅ እና ገላጣ አካባቢዎች በመሆን እራሳቸውን ሊጠብቁ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
በአዋሽ ፈንታሌ አካባቢ መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል አራት ነጥብ ዘጠኝ ሲሆን ጥቅምት 3 ቀን 2017 የተከሰተው ደግሞ በሬክተር ስኬል አራት ነጥብ ስድስት ሆኖ መመዝገቡን አስታውሰዋል፡፡
የተከሰተው አደጋ የጉዳት መጠንም ዝቀተኛ ነው ያሉት ፍሬ ወለጋ፤ በቀጣይ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ ምርምሮችን ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የስምጥ ሸለቆ መገኛ እንደመሆኗ የከፋ ጉዳት ባያደርስም በተለያዩ ጊዜያት የመሬት መንቀጥቀጥ አጋጥሟታል፡፡
በ1900 ዓ.ም ስድስት ነጥብ ሰባት፣ በ1909 ዓ.ም ስድስት ነጥብ ስምንት እንዲሁም በ1961 ዓ.ም ስድስት ነጥብ አምስት በሬክተር ስኬል የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን የጂኦሎጂ መረጃዎች ያሳያሉ።
ሄለን ወንድምነው
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥቅምት 6 ቀን 2017 ዓ.ም