ሀገራዊ ምክክሩ – ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት

ሀገራዊ ምክክሩ የአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ በተለያዩ ክልሎች እየተካሄደ ይገኛል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአፋር ክልል በቅርቡ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍን ማጠናቀቁ ይታወሳል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ በሶማሌ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍን እየተከናወነ ይገኛል።

ምክክሩ አንድነቷ የተጠበቀ ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚያስችል ሂደት መሆኑን በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚገልጹት ጉዳይ ነው። በሂደቱ የተሳተፉ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ሀገራዊ ምክክሩ አንድነቷ የተጠበቀ ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት ያስችላል የሚል እምነት እንዳላቸው ለኢፕድ ተናግረዋል።

የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ምክትል ሊቀመንበር መሐመድ አወል፤ እንደ ፓርቲ የሀገራዊ ምክክሩን አስፈላጊነትን ለረጅም ጊዜ ስናነሳው የነበረ ጉዳይ ነው። የረጅም ጊዜ ጥያቄያችን በለውጡ መንግሥት ምላሽ በማግኘቱ የራሳችንን ዝግጅት በማድረግ የምክክር ሂደቱ የሚጀመርበትን ጊዜ በጉጉት ስንጠብቅ ቆይተናል ይላል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ሆኖ ጠንካራ ኢትዮጵያን መመሥረት እንዲችል ትርክቶቻችን ሊመሳሰሉ ይገባል በሚል ውይይቱን መጠበቃቸውን የሚጠቁሙት ምክትል ሊቀመንበሩ፤ የምክክር መድረኩ ሲከፈት ፓርቲያቸው በራሱ በኩል በጉባዔ ደረጃ ተነጋግሮበት ዝግጅት አድርጎ የለያቸውን አጀንዳዎች ይዞ መቅረቡን ያስረዳሉ።

አቶ መሐመድ እንደሚያስረዱት፤ ሀገራዊ ምክክር ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት አንድነታችንን ጠብቀን ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት ነው። ምክክሩ ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች የወጡ አካላት ተገናኝተው በሠለጠነ መንገድ ተነጋግረው ለሀገርና ለወገን የሚበጅ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ያደርጋል።

ፓርቲያቸው ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመመሥረት እንደሚሠራ ያመላከቱት ምክትል ሊቀመንበሩ፤ በዚህ ውይይት አናምንም ብለው የቀሩ ፓርቲዎች ጥርጣሬያቸውን ወደጎን በማራቅ ችግሮች የሚፈቱት ተቀራርቦ በመነጋገር ስለሆነ ወደ ምክክሩ ሊመጡ ይገባል ይላሉ።

የአፋር ነፃ አውጪ ግንባር የፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል አሕመድ ሐሰን በበኩላቸው፤ ሀገራዊ ምክክሩ እንደ ክልል ለአፋር ሕዝብ እንደ ሀገር ደግሞ ለመላው ኢትዮጵያውያን ጠቃሚ መሆኑ ነው የተናገሩት።

በተለይም በአሁኑ ሰዓት ያሉትን ችግሮች በማስወገድ ሀገራችንን ከመበታተን አደጋ ታድጎ ሕዝባችን ተፈቃቅሮ በአንድ እንዲኖር ያደርጋል ሲሉ ያስረዳሉ።

ሠላም መምጣት የሚችለው በሰከነ መንገድ ዴሞክራሲያዊ ውይይት አድርጎ መግባባት ሲቻል ነው። ምክክሩ የሀገራችን ችግር የት ላይ ነው የሚለውን ለይቶ ቁስሏን እንዴት ማከም እንደሚቻል የሚያመላክትና ያለፉ ሥርዓቶች የፈጠሯቸው ጠባሳዎች ዳግም እንዳይከሰቱ ትክክለኛ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ ይሆናል ብለን እንጠብቃለን ይላሉ።

በአፋር ክልል የተደረገውን የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ሂደት ፓርቲያቸው አሳታፊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዳገኘው የጠቆሙት አሕመድ፤ እኛ የሀገራችንን የሕመም ምክንያት ነው የምንለውን ለይተንና መክረን አጀንዳችንን አስተላልፈናል ሲሉ ይናገራሉ። ይህም ከሌሎች ክልሎች ከሚሰበሰቡ አጀንዳዎች ጋር ተደምሮ ሀገራዊ ምክክር ተደርጎበት ሀገራችንን የሥልጣኔ ማማ ላይ ለማስቀምጥ የሚያስችል ጉዞ እንድናደርግ ያግዘናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል።

የአርጎባ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ፓርቲ አመራሩ ጀማል ሐሰን በበኩላቸው፤ ሀገራችንን ለማሳደግ እና ሠላም እንዲሰፍን ለማድረግ በሀገር ደረጃ ብቻ ሳይሆን ከወረዳ ጀምሮ ባሉት የአስተዳደር አወቃቀሮች የሚወከሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች እና ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት ምክክር ማካሄድ ያስፈልጋል ባይ ናቸው። አሁን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እያካሄደ የሚገኘው ይህን በጎ ተግባር በመሆኑ መደገፍ እንደሚገባ ይገልጻሉ።

ሀገራዊ ምክክሩ አሁን ያለውን ግጭት ምድራችን ሠላም እንዲሰፍን ያደርጋል ብለው እንደሚያምኑ የሚገልጹት የፓርቲ አመራሩ፤ በተያያዘው መንገድ ከተመካከርንና ከተወያየን ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሰን ችግሮቻችንን እንፈታለን ሲሉ ይጠቁማሉ።

በአጠቃላይ የተጀመረው የምክክር ሂደት ጠንካራ ሀገር እንዲኖረንና ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ የምንልበትን ዕድል ይሰጣል የሚል ዕምነት እንዳላቸው ይናገራሉ።

ክልላችን በሀገራዊ ምክክሩ የሚያደርገው ተሳትፎ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎችና ባለድርሻ አካላት ያካተተ እንዲሆን በቂ ዝግጅት ተደርጎበት የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረኩ በጥሩ መንገድ ተከናውኗል ይላሉ።

በክልላችን የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ብልፅግና ፓርቲም የራሳቸውን አጀንዳ አቅርበው ውይይትና ምክክር ተደርጎባቸዋል የሚሉት ደግሞ የአፋር ክልል ዞን አንድ ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊው ናስር መሐመድ ናቸው።

ሀገራዊ ምክክሩ ከዚህ ቀደም ያልነበረ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘ ዕድል መሆኑን የሚያወሱት የፓርቲው ጽሕፈት ቤት ኃላፊው፤ ቀደም ሲል ዜጎች ሀሳባቸውን በነፃነት የሚያስተናግዱበት መንገድ ሳይኖራቸው በመቅረቱ የተለያዩ ምርጫዎች ውስጥ የገቡበት ሁኔታ መኖሩን ያስታውሳሉ።

ምክክሩ ይዞ የመጣው የትኛውንም ሀሳብ በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት የሚቻልበትን አማራጭ ነው። ምክክሩ ገና የጅማሬ ሂደት ላይ የሚገኝ ቢሆንም እስካሁን እየታየ ያለው ሂደት የሚበረታታ ነው ይላሉ።

አያይዘውም፤ ሀገራዊ ምክክሩ ሕገመንግሥቱን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በተናጠልና በወል የሚነሱ ጥያቄዎች ላይ በስፋት ምክክር ተካሂዶባቸው በውይይት ሂደትና በሕዝብ ድምፅ መልስ የሚያገኙበት መሆኑን ይጠቁማሉ። ከምክክሩ በኋላ እንደ ሀገር ይዘን የምንጓዘው የጋራ ገዢ ሀሳብ እና ትርክት ይኖረናል የሚል እምነት አለን። በውጤቱም ሀገራችን እየተጓዘች በምትገኝበት የእድገት ጎዳና ላይ በፍጥነት እንድትገሰግስ በር ይከፈታል ሲሉ ሀሳባቸውን ቋጭተዋል።

ተስፋ ፈሩ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2017 ዓ.ም

Recommended For You