የአደጋ ጊዜ ምላሽ የድጋፍ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፦ የዓለም አቀፍ የገጠር መልሶ ግንባታ ኢንስቲትዩት (IIRR) በአዲስ አበባ ከተማ፣ በሲዳማ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች ተግባራዊ የሚደረግ የአደጋ ጊዜ ምላሽ አገልግሎት የልማት ድጋፍ ፕሮጀክት ይፋ አደረገ።

ፕሮጀክቱ ትናንትና ይፋ ሲደረግ የኢንስቲትዩቱ ካንትሪ ዳይሬክተር ዘሪሁን ለማ እንደገለፁት፤ ከፖላንድ መንግሥት በተገኘ ድጋፍ ከፖላንድ ዓለም አቀፍ እርዳታ ማዕከል (PCPM) ጋር በመተባበር ለሁለት ዓመታት ተግባራዊ የሚደረገው ፕሮጀክት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ በሲዳማና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች ይተገበራል።

ለፕሮጀክቱ ተግባራዊነት አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ዶላር መበጀቱን አስታውቀው፤ በመዲናዋ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የእሳት አደጋ ተከላካዮችና የአምቡላንስ ባለሙያዎች ሥልጠና ለመስጠትና የአምቡላንስ ሠራተኞችን የቅድመ ሆስፒታል እንክብካቤ አቅም ለማሳደግ እንደሚሠራ አመላክተዋል።

በፕሮጀክቱ አማካኝነት ለእሳት አደጋ መከላከል የሚያገለግሉ መሣሪያዎች ድጋፍ እንደሚደረግ አንስተው፤ ፕሮጀክቱ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ የማኅበረሰብ አቀፍ የእንስሳት ጤና ባለሙያዎችን አቅም ለማሳደግ፣ ለአርብቶ አደር ማኅበረሰቦች የእንስሳት ጤና አጠባበቅ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

የፖላንድ ዓለም አቀፍ ርዳታ ማዕከል ሥራ አስኪያጅ ዎጅቴክ ዊልክ (ዶ/ር) በበኩላቸው። ማዕከሉ በኢትዮጵያ ያለውን የአደጋ ስጋት መከላከል አቅምን ለማጠናከር ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም የሰብዓዊ ርዳታ፣ የሕክምና ድጋፍና ለኢትዮጵያውያን ድንገተኛ የሕክምና ቡድን አባላት የአቅም ማጎልበቻ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ማዕከሉ በኢትዮጵያ በነበረው የ12 ዓመታት ቆይታ ከአራት ነጥብ አራት ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ በማድረግ በትምህርት፣ በጤናና በሌሎችም ዘርፎች 10 ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ወደትግበራ ማስገባት መቻሉን ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቱ ቀደም ሲል በኬንያ ተግባራዊ መደረጉን ያነሱት ሥራ አስኪያጁ፤ በኢትዮጵያ ለፕሮጀክቱ ተግባራዊነት ምቹ ሁኔታዎች አሉ ያሉት ዎጅቴክ (ዶ/ር)፤ በዚህም የአዲስ አበባ ከተማ እሳትና አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በቂ ሠራተኞችና የድንገተኛ እሳት አደጋን መከላከል የሚያስችሉ ማዕከላት መኖራቸውን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣናው ድንገተኛ አደጋዎችን ለመከላከል የሚያስችል ትልቅ ተቋም መገንባት መቻሏን በመግለጽ፤ ፕሮጀክቱ በዋነኝነት ለሙያተኞች የክህሎትና የቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑንም አመላክተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የድንገተኛ አደጋዎች ሕክምናና አምቡላንስ አገልግሎት ዳይሬክተር ዑመር አብዱራዛቅ በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ በወሳኝ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ የሪፎርም ሥራ በማከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል።

የሠራተኞችን አቅም በማሳደግና ዘመናዊ መሣሪያዎችን በመጠቀም ረገድ ይህ ፕሮጀክት ኮሚሽኑ እያከናወነ ከሚገኘው ሥራ ጋር ከፍተኛ ቁርጠኝት ያለው መሆኑንም ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ እንዲተገበር ላደረጉት አካላት ምስጋና ያቀረቡት አቶ ዑመር፤ ፕሮጀክቱ እስኪጠናቀቅ ኮሚሽኑ የበኩሉን አስተዋፅዖ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You