- 11 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል
- 337 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል
አዲስ አበባ፡- በ2016/17 የምርት ዘመን ለመኸር እርሻ ስምንት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ኩንታል የኬሚካል የአፈር ማዳበሪያ ማቅረቡን የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ። በዘር ከተሸፈነው 11 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሔክታር መሬት 337 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅም ተገልጿል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ ትላንት በሰጡት መግለጫ እንዳመላከቱት፤ በ2016/17 የምርት ዘመን ለመኸር እርሻ ስምንት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ኩንታል የኬሚካል አፈር ማዳበሪያ ማቅረብ ተችሏል።
እንደ አቶ ጌቱ ገለጻ፤ በተለያዩ ሰብሎች ከተሸፈነው 11 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት 337 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል።
በዘር ከተሸፈነው መሬት ውስጥ ስምንት ሚሊዮን 651 ሺህ ሄክታር በኩታ ገጠም ማልማት ተችሏል ያሉት ኃላፊው፤ በአጠቃላይ በዘር ከተሸፈነው መሬት 78 በመቶውን በክላስተር የለማ መሆኑን አስታውቀዋል።
በምርት ዘመኑ የኬሚካል ማዳበሪያን፣ መደበኛና ቨርሚ ኮምፖስትን ለአርሶ አደሩ ማቅረብ መቻሉን ጠቅሰው፤ ለአርሶ አደሩ ከቀረበው ስምንት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ኩንታል የኬሚካል አፈር ማዳበሪያ ውስጥ ከስምንት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን በላይ ኩንታል ጥቅም ላይ መዋሉን ገልጸዋል።
በክልሉ የሜካናይዜሽን፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና የባለሙያዎች ምክር እያደገ መምጣቱን አንስተው፣ አራት ሚሊዮን ሔክታር መሬት በሜካናይዜሽን ታግዞ መልማቱን ተናግረዋል።
በበቆሎ ሰብል ልማት ሁለት ሚሊዮን ሔክታር መሬት በዘር መሸፈኑን የገለጹት አቶ ጌቱ፤ አንድ ሚሊዮን 40 ሺህ ሔክታር መሬት በማሽላ ሰብል ዘር እንደተሸፈነ ጠቁመዋል።
በመኸር እርሻ ሦስት ሚሊዮን 165 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ ሰብል መሸፈኑን ጠቅሰው፤ ከውጪ የሚገባውን የቢራ ገብስ ለማስቀረት 528 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ገልጸዋል።
የሩዝ ምርትን ለማሳደግ አንድ ሚሊዮን 918 ሺህ ሔክታር መሬት መልማቱን አስረድተው፤ 603 ሺህ ሄክታር በአኩሪ አተር ፣ 518 ሺህ ሄክታር በለውዝ፣ 180 ሺህ ሄክታር መሬት ደግሞ በሱፍ ዘር መሸፈኑን አስረድተዋል።
ለውጪ ገበያ እንዲቀርቡ ከሚሠራባቸው ሰብሎች መካከል የቦሎቄ ምርት አንድ ሚሊዮን 81 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን በመግለጽ፤ ሰሊጥ 500 ሺህ ሔክታርና ማሾ 300 ሺህ 112 ሄክታር መሬት ላይ መልማታቸውን ተናግረዋል።
በእንስሳት ልማት በሰው ሠራሽ ዘዴ አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ላሞችና ጊደሮችን ማዳቀል ተችሏል ያሉት ኃላፊው፤ 53 ሚሊዮን የአንድ ቀን የዶሮ ጫጩቶችን ለአርሶና ከፊል አርብቶአደሩ የማከፋፈል መቻሉን አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል አንድ ሚሊዮን 31 ሺህ ዘመናዊ የንብ ቀፎዎችን ማከፋፈል መቻሉን ጠቁመዋል።
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2017 ዓ.ም