ለሀገር ክብር በአንድነት የተሰለፉ ወንድማማቾች

ዜና ሐተታ

ሀገር ወዳድ ዜጎች በተልዕኮዋቸውና ሀገራቸውን በሚወዱት መጠን መስዋዕትነትን ይከፍላሉ። የሀገር ወዳድነት ፍቅር ሲታሰብ የሚከፈለው መስዋዕትነት ከሕሊና በላይ ሊሆን ይችላል። ወታደር በደምና በአጥንት የሕይወት መስዋዕትነት ለእናት ሀገሩ የመክፈል ዕድልን በተግባር የሚተረጉም ነው። ለዚህም ይመስላል ውትድርና የሀገር ወዳድነት ሚዛን ልኬቱ እንደሆነ ብዙኃኑ የሚናገሩት።

ወታደር ልክ እንደ ኃይለኛ ጅረት ነው ይባላል። ጅረት ኃይሉ ተዳክሞ እስኪረጋ ድረስ ተምዘግዛጊ ሆኖ እንደሚወርድ ሁሉ ወታደርም በነፍሱ ተወራርዶ የሕይወቱ ምዕራፍ እስኪከደን ገድሉን ከመፈጸም ወደ ኋላ አይልም። ይህ ገድል በሀገር ፍቅር ስሜት ሲታጀብ ደግሞ ሌሎችን ለማነሳሳትም የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅም ጠቃሚ ይሆናል።

የሀገር ፍቅር ስሜት ይነስ ይብዛ እንጂ በበርካታ ዜጎች ውስጥ የሚናወጥ የስሜት ማዕበል ነው። ይህን የሀገር ፍቅር ስሜት ደግሞ በደም ጭምር ለመክፈል የሚታደሉ በርካቶች ናቸው። በተለይ ከአንድ ማህፀን ወጥተው ለአንድ ዓላማ የሚሰለፉ ወጣቶች። ለዚህ ክብር የበቁ ጥቂቶች አክሊሉ አበራ እና ቴዎድሮስ አበራ ወንድማማቾች፤ ታላቅና ታናሽ የአንድ ማህፀን ተጋሪዎችም ናቸው።

ትውልድና እድገታቸው ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ዞን ነው። ተነጣጥለው አያውቁም ውሎና አዳራቸውም አንድ ላይ ነው። ከቤተሰቦቻቸው የሚሰጣቸው ሥራ በጋራ ሲከውኑ፤ ሲተጋገዙ ቤተሰብ ሲረዱ እየተመረቁ አድገዋል።

እናት አባታቸውን በጋራ ከማገልገል የሀገርን ዳር ድንበር እስከመጠበቅ የዘለቀ ጥብቅ ቁርኝት አላቸው። እቅዳቸውና ተልዕኳቸው ሳይዛነፍ ብዙ የሕይወት ምዕራፎች ተራምደዋል።

“እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ” እንዲሉ ሀገርን በደምና በላብ የማገልገል ውጥናቸውም በጋራ ያሰቡት ነው። ይህም ውጥን ከግብ ለማድረስ ጦላይ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ገብተው እያንዳንዷን ሥልጠና በአግባቡ ተከታትለዋል።

ወንድማማቾቹ አክሊሉና አበራ የጦላይ ከፍተኛ ባለሌላ ማዕረግተኛ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት በመሠረታዊ ውትድርና በቅርቡ ካስመረቃቸው ምሩቃን መካከል ናቸው።

አሁን ደግሞ ለልዩ ተልዕኮና የሀገራቸውን ዳር ድንበር በመጠበቅ ለሉዓላዊነቷን ለማጽናት ተዘጋጅተዋል። አክሊሉና አበራ እንደማንኛውም ሰው የሃሳብ ልዩነቶች አሏቸው፤ ነገር ግን ሁሌም በሃሳብ የበላይነት የሚያምኑና ለጋራ ዓላማቸው ቅድሚያ የሚሰጡ በመሆናቸው ከዓላማቸው ጽናት ፈቀቅ ማለትን አይወዱም።

ወንድማማቾቹ እስከ መጨረሻዋ እስትንፋሳቸው እናት ሀገራቸው ለማገልገል ዛሬም እንደ ትናንቱ በአንድ ልብ በመምከር ቁርጠኛ መሆናቸው ይናገራሉ።

አክሊሉ አበራ ታላቅ ወንድም ሲሆን ከታናሽ ወንድሙ ቴዎድሮስ ጋር ከተወያየ በኋላ በውትድርና ሙያ ኢትዮጵያ ለማገልገል ወደ ውትድርና ሥልጠና መግባታቸውን ያስታውሳል።

ከልጅነቴ ጀምሮ መከላከያ ሠራዊት የመቀላቀል ከፍተኛ ፍላጎት ነበረኝ የሚለው መሠረታዊ ወታደር አክሊሉ፤ ከየትኛውም ዓይነት ወገንና ፓርቲ ድጋፍም ሆነ ተቃርኖም ሳይኖራቸው ሀገራቸው ብቻ ለማገልገል ወስነው ከቤት መውጣታቸውን ያብራራል።

በዚህም መሠረት ለራሳቸው በገቡት ቃልና በሥልጠናው ባገኙት ሀገራዊ እሳቤ በፍትሐዊነትና በታማኝነት ሀገራቸውን ያለ ልዩነት ለማገልገል ቁርጠኛ እንደሆኑም ያክላል።

ሥልጠናውም በሚገባ ተከታትለን መሠረታዊ ወታደር መሆን ችለናል፤ የሚሰጠንን ሀገራዊ ግዳጅ በአግባቡ ለመወጣት ዝግጁ ነው ሲል ሃሳቡን ይገልጻል።

ሀገሪቷን ከውጭ ወራሪና ከውስጥ ፀረ-ሠላም ኃይል ለመጠበቅ እንዲሁም ዘላቂ ልማት እንዲረጋገጥና የኢኮኖሚ አውታሮቿ ሠላማዊ እንቅስቃሴ እንዲኖራቸው ለማድረግ ወንድማማቾቹ ዝግጁ ናቸው።

መሠረታዊ ወታደር ቴዎድሮስ አበራ በበኩሉ፤ ከታላቅ ወንድሙ ጋር ሠልጥኖ ወታደር ለመሆን በመብቃቱ ደስተኛ መሆኑን ይናገራል።

በበፊት ሕይወታችንም ተነጣጥለን አናውቅም፤ በሥራ አጋጣሚ የትም ስንሄድ አብረን ነው የምንሄደው የሚለው መሠረታዊ ወታደር ቴዎድሮስ፤ አሁንም በሥልጠና ባገኘነው እውቀትና ብሔራዊ እሳቤ በጋራ ለመሥራት ዕድሉን አግኝተናል ይላል።

መሠረታዊ ወታደር ቴዎድሮስ፤ በማዕከሉ በርካታ የተግባርና የንድፈ ሃሳብ ሥልጠናዎች ማግኘታቸውን ጠቅሶ፤ በውትድርና ሙያ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መስዋዕት ለመክፈል ዝግጁ ነኝ፤ ማንም ሀገሬን ላይ ጉዳት እንዳያደርስ እኔ ቀድሞ እደርስላታለሁ ሲል ለውትድርና ሙያ ያለውን ክብርና ለሀገሩ ያለውን ፍቅር ይገልጻል።

ወንድማማቾቹ ከቤተሰብ ጀምሮ ያላቸውን ጥብቅ ቁርኝት በማስፋት በሠራዊቱ ውስጥ ለአንድ ዓላማ የመሰለፍን ሙያዊ ግዴታ በመላበስ ሀገርን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ወኔ በተሞላበት ስሜት አስረድተዋል።

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You