ዜና ሐተታ
ኢትዮጵያን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት አልሚ ባለሀብቶች ተመራጭ ማድረግ ያስቻሉ የአዋጅ፣ የአሠራርና ሌሎችም በርካታ ማሻሻያዎች እንዲሁም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታዎች ተከናውነዋል። በዚህም በየጊዜው የኢንቨስትመንት ፍሰቱ እያደገ በመምጣቱ ኢትዮጵያ ከምሥራቅ አፍሪካ ዋናዋ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እየሆነች ነው።
እንደ ሀገር ለዘርፉ የተሰጠውን ልዩ ትኩረት ከሚመሰክሩ ሥራዎች አንዱ በኦሮሚያ ክልል ዱከም ከተማ የሚገኘው እ.አ.አ በ2007 የተቋቋመው የኢስተርን ኢንዱስትሪ ፓርክ ነው። ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሥራ ኃላፊዎችና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች የኢንዱስትሪ ፓርኩን የሥራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
ጉብኝቱ በፓርኩ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ከተሠማሩት ከ153 በላይ የውጭ አልሚ ባለሀብቶች ይገኛሉ። በፓርኩ የሚገኙ ኩባንያዎች የምርት እንቅስቃሴና የሚደረግላቸው ድጋፍ ምን እንደሚመስል ለኢፕድ ሃሳባቸውን አጋርተዋል።
ሊንዳ ኢትዮጵያ ጋርመንት በኢስተርን ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ከተሰማሩ የቻይና ኩባንያዎች መካከል አንዱ ነው። የኩባንያው ጀነራል ማናጀር ሚስተር ጄ ይፋን እንደሚገልጹት፤ በኢትዮጵያ ኢንቨስት በማድረጋቸው እጅግ ደስተኛ ናቸው። ሊንዳ ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2013 የተቋቋመ ሲሆን ለ10 ዓመታት ያህል የተለያዩ የአልባሳት ውጤቶችን በማምረት ለገበያ ሲያቀርብ ቆይቷል።
ኩባንያው በስሩ ከአንድ ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል የሚሉት ሚስተር ጄ፤ ከዚህ ቀደም ብዛት ያላቸውን የተለያዩ አልባሳት በማምረት ወደአሜሪካና አውሮፓ ሀገራት ያቀርብ እንደነበር ነው የተናገሩት።
የተለያዩ የጨርቅ ግብዓቶች ከውጭ በማስገባት ተኪ ምርቶችን ለማምረት በተጀመረው እንቅስቃሴ ኩባንያው ምርቶቹን ለኢትዮጵያ ገበያ እያቀረበ ሲሆን መንግሥትም ተገቢውን ድጋፍ እያደረገልን ነው ይላሉ።
ሌላኛው በኢስተርን ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የተሠማራው የቻይና ኩባንያ እ.አ.አ በ2016 በ181 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመው ሁአጂያን አሉሚንየም ነው።
ከ170 በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች በቋሚነት የሥራ ዕድል ፈጥሯል። በተለያየ ዲዛይንና ቀለም ለበር፣ ለመስኮትና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉ 16 አይነት የአሉሚንየም ፕሮፋይሎችን በማምረት ለሀገር ውስጥ ገበያ እንደሚያቀርብ የኩባንያው ጀነራል ማናጀር ሚስተር ዴቪድ ዞሁ ይናገራሉ።
እንደ ጀነራል ማናጀሩ ገለጻ፤ ካምፓኒው በግብዓትነት የሚጠቀመው የአገልግሎት ጊዜያቸው ያበቁና የወዳደቁ አሉሚንየሞችን ሲሆን፣ እጥረት ሲኖርም ከውጭ ያስገባል።
ድርጅቱ በቀን ከ10 እስከ 15 ቶን በማምረት ለሀገር ውስጥ ገበያ እያቀረበ ቢሆንም ያለውን ፍላጎት ማሟላት ባለመቻሉ እና በቂ ግብዓት ባለማግኘቱ ለውጭ ገበያ ማቅረብ አዳጋች ሆኖበታል። ከውጭ ምንዛሪ እጥረትና ከግብዓት ጋር የተያያዙ ችግሮችም አሉበት ይላሉ።
የኢስተርን ኢንዱስትሪ ፓርክ ማኔጅመንት ኮሚቴ ሺያ ዞሁ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያና ቻይና በርካታ ዓመታትን በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አሳልፈዋል።
በዚህም ከፓርኩ ምሥረታ ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግሥት ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል። ምቹ የሥራ ከባቢ በመፍጠሩ በፓርኩ የሚገኙ ኩባንያዎች በአግባቡ የምርት ሂደት በማከናወን ላይ ይገኛሉ ሲሉ ያስረዳሉ።
ፓርኩ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ጨምሮ ከክልል፣ ከፌደራልና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሁሉ በቅርበት እየሠራ ነው። በዚህም ምቹ የመሥሪያ ከባቢ መፍጠር ተችሏል። በፓርኩ የሚገኙ ካምፓኒዎች ቁጥርም እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰዋል።
የቻይናና የኢትዮጵያ ግንኙነት ከጊዜ ወደጊዜ በሁሉም ዘርፎች እያደገ መጥቷል፤ ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት የብሪክስ አባል መሆኗ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በይበልጥ ለማሳደግ ምቹ አጋጣሚን ተፈጥሯል ይላሉ።
ሚስተር ሺያ ዞሁ እንዳመላከቱት፤ በቅርቡ ተግባራዊ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የተለያዩ ግብዓቶችን
ከውጭ በማስገባት በፓርኩ የሚገኙ ካምፓኒዎችን የማምረት አቅም ለማሳደግ ያግዛል። በዚህም በርካታ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር የአካባቢውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማጠናከር ያግዛል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) እንደሚገልፁት፤ ለውጡን ተከትሎ ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢን በመፍጠር ኢትዮጵያን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት አልሚ ባለሀብቶች ተመራጭ ለማድረግ በተሠሩ የሕግ፣ የኢኮኖሚና ሌሎችም በርካታ ማሻሻያዎች በየጊዜው ወደኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ የሚመጡ ባለሀብቶች ቁጥር ጨምሯል።
እንደ ዘለቀ (ዶ/ር) ገለጻ፤ አሁን ላይ በኢስተርን ኢንዱስትሪ ፓርክ መዋለ ንዋያቸውን ፈሰስ በማድረግ ላይ ከሚገኙ 153 የውጭ ባለሀብቶች መካከል 95 ከመቶ የቻይና ቀሪዎቹ ደግሞ የሕንድና የእንግሊዝ ባለሀብቶች ናቸው።
በኢትዮጵያ አጠቃላይ ከ3 ሺህ 300 በላይ የሚሆኑ የቻይና ኩባንያዎች ከ8 ነጥብ 5 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ መዋለ ንዋይ ፈሰስ በማድረግ በሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ አይነተኛ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ ያስረዳሉ።
የቻይና ኩባንያዎቹ በተኪ ምርት፣ በክህሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም በንግድ ትስስር እያበረከቱት ከሚገኘው አስተዋፅዖ ባሻገር ከ325 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠር መቻላቸውን ይጠቁማሉ።
የሀገር ውስጥና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ኮሚሽኑ የድጋፍና ክትትል ሥራ እየሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህም በኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን የሚገኙ ባለሃብቶች በሚደረግላቸው የቅርብ ድጋፍ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት የድርሻቸውን እየተወጡ ይገኛሉ ይላሉ።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውም በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች የሚቀርቡ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ጥያቄዎችን ምላሽ በመስጠት ገንቢ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ነው ያስገነዘቡት።
ቃልኪዳን አሳዬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 6 ቀን 2017 ዓ.ም