አዲስ አበባ:- በአፍሪካ ያጋጠሙ የፀጥታን ችግሮችንና የተለያዩ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ሌሎችን ከመመልከት ይልቅ በአሕጉሪቷ ያሉ አካላት በአንድነት መቆም ይገባቸዋል ሲሉ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ጥሪ አቀረቡ።
የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ጉባኤ “አፍሪካ በጠንካራ አንድነት፣ ለሁለንተናዊ ፀጥታና ሠላም” በሚል መሪ ሀሳብ ትናንትና በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም መካሄድ ጀምሯል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ መድረኩን ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር፤ በአፍሪካ በአሁኑ ወቅት የፀጥታ ጉዳዮች፣ የውስጥ ግጭቶች፣ ድንበር ዘለል ግጭቶች፣ የሽብርተኝነትና የአክራሪዎች ስጋቶች እየጨመሩ መምጣታቸውን አንስተዋል።
ተግዳሮቶቹን ለመፍታት ወደ ሌሎች አካባቢዎች ማማተር ሳይሆን ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ በሚለው መርሕ መሠረት በጋራ መቆም እንደሚገባ አመላክተዋል።
አፍሪካውያን ለደኅንነታቸውና ለመፃኢ ዕድላቸው ኃላፊነት የሚወስዱበት ጊዜ ላይ መሆናቸውን የተናገሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በአሕጉሪቱ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን አስከፊነት በመገንዘብ ከመወያየት በዘለለ በንቃት ዘላቂ መፍትሔ ወደመፈለግ መሸጋገር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ የሚለው መርሕ መፈክር ከመሆን አልፎ በተግባር የሚገለጥ መሆኑንም አንስተዋል። በሰብዓዊ ርዳታና በሰብዓዊ መብት ተሟጋችነት ሽፋን የሚደረጉ የውጭ ጣልቃ ገብነት ችግሮችንም በጋራ መጋፈጥ እንደሚገባ ተናግረዋል። ለዚህ ደግሞ ቀጣናዊ ትብብር እና አብሮነት ላይ ትኩረት አድርጐ መሥራት ይገባል ብለዋል።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ በበኩላቸው፤ በፀጥታው ዘርፍ ትብብርን በማጠናከርና ሽብርተኝነትን በመዋጋት የበለጠ አስተማማኝና ሠላም የሰፈነባት አፍሪካን መገንባት እንደሚገባ አስታውቀዋል።
ጉባኤው የአፍሪካ ሀገራት በትብብር በአሕጉራቸው በአስተማማኝ ፀጥታ ላይ ለመሥራት፣ ከሀገር አቀፍ ድንበሮች በላይ የሆኑ ጉዳዮች ላይ በቅርበት ለመሥራት እንዲሁም በመፃኢው የአፍሪካ ብልፅግና ላይ ያላቸውን ቁርጠኝነት ለማጉላት የሚረዳ መሆኑን ገልጸዋል።
በአፍሪካ ኅብረት የፖለቲካ ጉዳዮችና የፀረ-ሽብር ማዕከል ተወካይ ባባቱንዴ አባዮሚ በበኩላቸው፤ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች፣ የፀጥታ ችግሮች፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የጂኦ ፖለቲካ ፉክክርና ሌሎች ከፀጥታ ጋር የተገናኙ ችግሮች አሕጉሪቱን እየፈተኑ ይገኛሉ ሲሉ ተናግረዋል።
ለአፍሪካ የፀጥታ ችግሮች የአፍሪካ አባል ሀገራት በተጠናከረ የጋራ ትብብር ሊሠሩ እንደሚገባ አመላክተው፤ ጉባኤውም ለዚህ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ጠቁመዋል። የአፍሪካ ኅብረትም ለመሰል የትብብር ሥራዎች ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በጉባኤው ላይ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የተለያዩ ሚኒስትሮችና አምባሳደሮች እንዲሁም ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በነገው ዕለት በሚጠናቀቀው ጉባኤ በአሕጉሪቱ ለሚከሰቱ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የጋራ አቅጣጫዎች፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር ያሉ ዕድሎች ላይ የልምድ ልውውጥና ሌሎች አጀንዳዎች ላይ ጥልቅ ውይይት እንደሚደረግ ተገልጿል።
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 6 ቀን 2017 ዓ.ም