ሰንደቅ ዓላማችን – ለሁለንተናዊ ክብራችን

‹‹ሰንደቅ ዓላማ›› የሚለው ስያሜ ከሁለት ቃላቶች አካል የተመሠረተ ትርጓሜን ይዟል።ቃላቶች በተናጠል ሲተረጎሙ ሰንደቅ-ማለት ‹‹ምርኩዝ፣ ምሰሶ፣ በትር እንዲሁም የነፃነትና የሉዓላዊነት ምልክት እንደማለት ነው። ዓላማ ማለት ደግሞ ‹‹ምልክት፣ አቋም፣ ስብ ስብ፣›› የሚለውን ሀሳብ እንደሚያመለክት ለቃሉ የተሰጠው ትርጉሜ ይጠቁማል።

ሁለቱ የቃላት ጥምረቶች ‹‹ሰንደቅ ዓላማ›› በሚል ኅብር በአንድ ይጋመዳሉ። ይህ ማለት ደግሞ የሀገር መታወቂያ፣ የሕዝብ አንድነት መጠበቂያና የክብር መለያ ምልክት እንደማለት ነው። ይህ ታላቅ ስያሜ በሌላ መልኩ ሲቃኝ ሰንደቅ ዓላማ የአንድ ሀገር ሕዝብና መንግሥት ሉዓላዊ ነፃነትና ልዩ ተምሳሌት ሆኖ ይመዘገባል፡፡

ኢትዮጵያ በሰንደቅ ዓላማ ክብር ስማቸውን አድምቀው ጽፈዋል ከሚባሉ ሀገራት ተርታ ትሰለፋለች። ይህ እውነታ ደግሞ ዘመናትን ወደኋላ መለስ ብለን ታሪክን እንድንቃኝ ምክንያት ይሆናል። በሀገራችን ከ1890ዎቹ አጋማሽ ድረስ የነበረው የሰንደቅ ዓላማ ኅብር ወጥነት እንዳልነበረው ይነገራል። ይህ እውነታም ሰማያዊ ነጭና ጥቁር ቀለማት ለዓመታት የባንዲራችን ቋሚ መለያዎች እንደነበሩ የሚጠቁም ነው፡፡

እነዚህ ቀለማት በሰንደቅ ዓላማነት ከመውለ ብለባቸው አስቀድሞም በሀገራችን ጥቅም ላይ የዋሉት ቀለማት መልከ ብዙና ቋሚ ያልነበሩ ናቸው። በዘመኑ ሰንደቅ ዓላማ ማለት ለመንግሥት ግዛት ለሠራዊትና ለሃይማኖት መለያነት ከማገልገል ያለፈ ትርጉም እንዳልነበረው ታሪክ ይጠቁማል።

የዘውዳዊ አገዛዝ ሥርዓት እስኪያበቃ ድረስ የነበሩት ሰንደቅ ዓላማዎች የገዢ መደቦቹን ዓላማ በወከለ መልኩ ምስላቸውን የሚያንፀባርቁ ነበሩ። ይህ መሆኑ ደግሞ ወጥነት ባላቸው ቀለማት ሀገርን የሚወክል ሰንደቅ ዓላማ ዕውን እንዳይሆን ምክንያት ሆኖ ቆይቷል፡፡

በ1898 ዓ.ም አካባቢ በሀገራችን ለመጀመሪያ በሚባል መልኩ የሰንደቅ ዓላማ ቀለማት የተለየ ትኩረት አገኘ።ይህ እውነታም አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ቀለማት በኢትዮጵያዊ ማንነት ውስጥ እንዲሰርጹ ልዩ ኃይልን ፈጠረ። አረንጓዴ የልምላሜ፣ ቢጫ የተስፋና ብርሃን፣ ቀይ ደግሞ የመስዋዕትነት ትርጓሜ እንዲኖራቸው ሆኖ ተቀረጸ፡፡

አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ባንዲራ ከፍ ብሎ መውለ ብለቡ ለሁሉም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ የማንነቱ መሠረት፣ ሊሆን አልዘገየም። ትውልዱ በነዚህ ኅብረ ቀለማት ውስጥ ማንነቱን አጽንቶ ሀገሩንና ዜግነቱን ሊወድ፣ ስለባንዲራው ክብር እስከሕይወት መስዋዕትነት የደረሰ ተጋድሎ ሊያደርግ አቋሙን አጸና። በቀለማቱ ኅብር በትርጓሜው ኃይል ልባቸው በፍቅር የነደደው ወገኖች ባንዲራው ዓላማና ሕይወታቸው ሆነ። ሰንደቅ ዓላማ ማለት ለኢትዮጵያውያን ስምና መለያቸው እስኪሆን ድረስ በክብር ተንበረከኩለት፡፡

በየዘመናቱ በነበሩ አገዛዞች እንደ ሥርዓቱ አይነትና ፍላጎት በሰንደቅ ዓላማው ላይ ከፊል ለውጥ ሲደረግ ቆይቷል። እንዲያም ሆኖ ኢትዮጵያዊነትና የሰንደቅ ዓላማ ፍቅር ከከፍታው ዝቅ ብሎ አያውቅም።ሁሌም ለአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ ያለው ክብር የቀዘቀዘ አይደለም። ከቀድሞ ታሪኮች እውነታዎች ሲመዘዙ ደግሞ ጽናትና ጥንካሬ ልቆ ይታያል።

ከዘመን ድርሳን ወጎችን ስንሰማ ደግሞ ከአንድ አይረሴ እውነታ ያደርሰናል።የዛኔ የባንዲራው ስም በተነሳበት ዓውድ ሁሉ በንቀት ልቆና ረግጦ የሚያልፍ አንዳች ኃይል አልነበረም። በባንዲራው የሚምል፣ የሚማለድ፣ የሚወስን ትውልድ ዕልፍ ነበር። ይህ ትውልድ ሁሌም ሰንደቁን የማሸነፊያ ኃይል አድርጎ ይረታበታል። ‹‹ወድቆ በተነሳው ባንዲራ›› ይሉት ቃል ከአንደበት ከወጣ ንቅንቅ ይሉት የለም።ባንዲራ ታሪክ፣ ባንዲራ ሕይወት፣ ባንዲራ ሀገር ማለት ነውና፡፡

ኢትዮጵያዊነትና የሰንደቅ ዓላማ ፍቅር ትስስራቸው ይለያል። ይህ የማንነት መለያ በጦርነት አውድማ የድል ብስራት ነው። ጀግኖች በተሰለፉበት ግንባር ሕይወታቸውን አሳልፈው ይሰጡለታል። ሰንደቅ ዓላማ በሠላም መንደር የሁሉም መኖርና ሕልውና ሆኖ ዘልቋል። በባንዲራው መውለብለብ የማንነት መልክ ይረጋገጣል፣ የዜግነት መብት በግልጽ ይታያል፡፡

በትምህርት ዓለም ተማሪዎች ሰንደቃቸውን እያዩ በክብር ይዘምራሉ። እያንዳንዱ የመዝሙር ስንኝ ትርጉሙ የሚጎላው በከፍታ ልቆ ከሚታየው ባንዲራ ጋር በእኩል ሲውለበለብ ነው። ይህ የትውልድ አደራ የታተመበት፣ የታሪክ ድርሳን ደምቆ የተከተበበት ሰንደቅ ዓላማ የበዛ መስዋዕነት ተከፍሎበታል። ጀግኖች አርበኞች የጠላት ወራሪን የመከቱበት ኃይላቸው ነው። በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ማንነታቸውን የሚገልጹበት ውበታቸው ነው፡፡

ጀግኖች አትሌቶቻችን በዓለም አደባባይ ድል ሲጎናጸፉ የአሸናፊነት ዓርማቸው ሰንደቅ ዓላማቸው እንደሆነ ዘልቋል። ይህ መላው ዓለም በአድናቆት እጁን በአፉ የሚጭንበት፣ ደማቅ ድልን የሚያይበት ዓርማችን ለበርካታ አፍሪካ ሀገራት ጭምር መሠረት ነው። ያለምንም ቅኝ ግዛት በክብር የኖረችው ኢትዮጵያ ቀድማ ያውለበለበችውን አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀይ ባንዲራ ከነፃነት እስራታቸው መፈታት ማግስት እንደ ልዩ ገድ የቆጠሩት ሀገራት ቋሚ መለያቸው እንዳደረጉት ዘልቀዋል፡፡

ሰንደቅ ዓላማ ለኢትዮጵያውያን የጋራ ሀብትና በእኩል የመግባቢያ ሰነድ ነው። በማንነቱ ጉልበት ሺዎችን አንበርክኳል።በውበቱ ድምቀት እልፎችን ማርኳል። በውስጡ ያለው የዕንባና ሳቅ ታሪክም የደም መስዋዕትነት የተከፈለበት ነው። ጀግኖች ለባንዲራቸው ፍቅር ሕይወታቸውን ሲሰጡ ቅር ብሏቸው አያውቅም።

ከአፍሪካ አሕጉር አብዛኞቹ የቅኝ ተገዢ ሀገራት በአንድም ይሁን በሌላ የሀገራችንን የሰንደቅ ቀለም ተውሰው እኛን ሊመስሉን ሞክረዋል።በነፃነታቸው ማግስት ድልን የተመኙት አፍሪካውያን ወንድሞቻችን የኢትዮጵያን ባንዲራ ውለታ መቼውንም ቢሆን የሚዘ ነጉት አይሆንም። ይህ ለማንነታችን ዓርማና መለያ የሆነው ባንዲራችን ዘመናትን ከእኛው ጋር ዘልቋል ወደፊትም እንዲሁ ይቀጥላል፡፡

ኢትዮጵያዊነትና የሰንደቅ ዓላማ ታሪክ ፈጽሞ ተነጣጥለው አያውቁም። የብሔር ብሔረሰቦች ማንነት የተሳሰረው በዚሁ የቀለማት ኅብር ሆኗል። ሰንደቅ ዓላማችን ትውልድ በማንነቱ የራሱን ዐሻራ እንዲያኖር መሠረቱ ነው። ትናንትን ከዛሬና ከነገ ጋር ለማጠንከር የታሪክ መነሻ ሆኗልና።

በሀገራችን ስለባንዲራ ክብር ሲባል በየዓመቱ ቀኑ በትኩረት ተዘክሮ ያልፋል።በራሱ መርሕና መልዕክት የሚከበረው ይህ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በየጊዜው ሲታወስ ታላቅነቱን በሚዘክርና በሚያስታውስ ዝግጅት ነው። ዘንድሮም ለ17ኛ ጊዜ በመላው ኢትዮጵያ የባንዲራ ቀን ተከብሮ ውሏል።

ጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ተከብሮ የዋለው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በትምህርት ቤቶች፣ በተለያዩ ተቋማትና መሰል ስፍራዎች ሁሉ ዕለቱን በክብር አስታውሷል። በዚህ ቀን አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀይ ባንዲራችን በኢትዮጵያ ሰማይ ስር በድምቀት ተውለብልቧል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር ጎልቶ ተሰምቷል፡፡

‹‹ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ›› በሚል መሪ ቃል ተከብሮ ውሏል። ዕለቱም በኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ አባት አርበኞችና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት በድምቀት ተከብሮ አልፏል፡፡

ዘንድሮም ብሔራዊ አንድነታችን፣ ኢትዮጵያዊ ማንነታችን፣ እንደ ብረት ጠንክሮ ይዘልቅ ዘንድ የሰንደቅ ዓላማችን ሁለንተናዊ ክብር በከፍታ መታየቱ ይቀጥላል፡፡

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You