አዲስ አበባ፦ በመካከለኛው፣ በምሥራቅ እና በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ከሚጠናከሩት የአየር ሁኔታ ክስተቶች ላይ በመነሳት ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ከአማራ ክልል በሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ ዋግኸምራ፤ ሰሜን ሸዋ እና የኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞኖች፤ ከትግራይ ክልል የደቡብና የደቡብ ምሥራቅ ዞኖች፤ ከአፋር ክልል ፋንቲ፣ ማሂ፣ ሃሪ እና ጋቢ ዞኖች፤ ከኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ፣ ምዕራብ፣ ደቡብ ምዕራብ እና ሰሜን ሸዋ (ሰላሌ)፤ አዲስ አበባ፤ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ለኢፕድ በላከው የትንበያ መረጃ አመላክቷል።
በሚቀጥሉት አሥር ቀናት በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የሀገሪቱ ክፍሎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙም ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል። ዝናብ ሰጭ የአየር ሁኔታ ክስተቶች በደቡብ፣ ምሥራቅ ፣ደቡብ ምዕራብ ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የተሻለ ገጽታ እንደሚኖራቸውም ተገልጿል።
በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት ከኦሮሚያ ክልል ባሌ እና ምሥራቅ ባሌ፣ ጉጂ፣ ምዕራብ ጉጂ፣ ቦረና እና ምሥራቅ ቦረና ዞኖች፤ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ፣ ጎፋ፣ ጌዴኦ፣ ወላይታ፣ ኮንሶ፣ አማሮ፣ ባስኬቶ፣ ቡርጂ እና ደቡብ ኦሞ ዞኖች፤ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ቤንች ሸኮ፣ ዳውሮ፣ ኮንታ እና ምዕራብ ኦሞ ዞኖች፤ ሁሉም የሲዳማ ክልል ዞኖች፤ ከሶማሌ ክልል ፋፋን፣ ኤረር፣ ጀረር፣ ኖጎብ፣ ሊበን፣ ቆራሂ ዶሎ፣ ዳዋ፣ ሊበን፣ አፍዴር እና ሸበል ዞኖች፤ እንዲሁም ሐረሪ እና ድሬዳዋ ላይ በብዙ ቦታዎቻቸው ላይ ቀላልና መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ተጠቁሟል።
የክረምት ወቅት ዝናብ እያገኙ በነበሩት በምዕራብ፣ በደቡብ ምዕራብ እንዲሁም በምሥራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ዝናቡ ቀጣይነት እንደሚኖረው ተመላክቷል። እንዲሁም በፀሐይ ኃይል ታግዞ ከሚጠናከሩ የደመና ክምችቶች ጋር ተያይዞ በምዕራብና ቄለም ወለጋ፣ ኢሉባቦር፣ ቡኖ በደሌ፣ ጅማ፤ ከፋ፣ ሸካና ማጂ አካባቢዎች ላይ በጥቂት ስፍራዎች ላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ።
ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ፣ ሆሮጉዱሩ ወለጋ፣ አርሲ እና ምዕራብ አርሲ፤ ምሥራቅ እና ምዕራብ ሐረርጌ፣ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል፣ አሶሳ፣ ካማሺ እና የማኦኮሞ ልዩ ዞን፤ ከጋምቤላ ክልል የኢታንግ ልዩ ዞን፣ ኑዌር፣ አኝዋ እና ማጃንግ ዞኖች በብዙ ቦታዎቻቸው ላይም ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ተጠቅሷል።
ከአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር፣ ምስራቅ፣ ምዕራብ እና ሰሜን ጎጃም፣ የሰሜን፣ የደቡብ እና የማዕከላዊ ጎንደር፣ አዊ ዞኖች እና ባሕርዳር ዙሪያ፤ ከትግራይ ክልል የሰሜን ምዕራብ እና የምዕራብ ዞኖች ላይ ቀላል መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ትንበያው ጠቁሟል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ጥቅምት 5 ቀን 2017 ዓ.ም