ኢትዮጵያ በምግብ እራሷን ለመቻል ግብርናው ላይ ትኩረት አድርጋ እየሠራች ነው

አዲስ አበባ፡ኢትዮጵያ በምግብ እራሷን ለመቻል ግብርናው ላይ ትኩረት አድርጋ እየሠራች ነው ሲሉ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አስፋው (ዶ/ር) ገለጹ።

በምግብ ሥርዓትና በአግሮኢኮሎጂ ላይ ያተኮረው የመጀመሪያው የአፍሪካ ወጣቶች ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አስፋው (ዶ/ር) በጉባዔው መክፈቻ ላይ እንዳሉት፤ አፍሪካ በምግብ እራሷን አለመቻሏ ለበርካታ ችግር አጋልጧታል።ከእነዚህም መካከል ተደራራቢ ግጭቶችና ሠላም ማጣት ዋነኞቹ ናቸው።እነዚህንና ሌሎች ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትም በምግብ እራስን መቻል የቅድሚያ ተሰጥቶት መሥራት ያለበት ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ላለፉት ዓመታት ለግብርናው የሚገባውን ያህል ትኩረት ሳይሰጥ ቆይቷል ያሉት ሚኒስትሯ፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ሀገሪቱ በምግብ እራሷን ለመቻል በግብርናው ላይ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በግብርናው ዘርፍ ኢንቨስትመንትን በማበረታታት፣ ሜካናይዜሽንን በማበራከት፣ ኩታ ገጠም እርሻን በማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን አመልክተው፤ የግብዓት አቅርቦትን የማሳደግና በወቅቱ ተደራሽ የማድረግ ተግባር መከናወኑን ጠቅሰዋል።ለአብነትም የማዳበሪያ አጠቃቀም ከነበረበት 13 ሚሊዮን ኩንታል በ2016 የምርት ዘመን ወደ 20 ሚሊዮን ኩንታል ከፍ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ዘንድሮ 24 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለመግዛት መታቀዱን ገልጸው፤ በኢትዮጵያ ያለው የማዳበሪያ አጠቃቀም በአምስት ዓመት ውስጥ በእጥፍ አድጓል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የሜካናይዜሽን ሥራውን አጠናክሮ   በመቀጠል ከትራክተር ጀምሮ እስከ ወተት ማለቢያ ያሉ ማሽነሪዎችን ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ በማድረግ ሀገሪቱ በምግብ እራሷን ለማስቻል ቅድሚያ ተሰጥቶት የሚሠራ መሆኑ ማሳያ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ጉባኤው በዋናነት የምግብ ሥርዓቱን ለማስተካከል ግብርና ላይ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ ላይ መሥራት አለበት በሚሉ ጉዳዮች ላይ ለመምከር የተዘጋጀ መሆኑን ያነሱት ፍጹም (ዶ/ር)፤ የአፍሪካ የምግብ ሥርዓትና ሉዓላዊነት በአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ተፅዕኖ እየደረሰበት በመሆኑ የአሕጉሪቱን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ግብርናው ላይ እንዴት መሥራት ይቻላል? የሚለው ላይ መፍትሔ ለማምጣት የሚመክር መሆኑን ገልጸዋል።

ጉባኤው በመዲናዋ አዲስ አበባ መካሄዱ ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናዋን ለማረጋገጥ የስንዴ እና የሌማት ትሩፋት ንቅናቄዎችን እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስ እየተሠራ ያለው አረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ እንዲሁም በቱሪዝም ዘርፉ ያላትን ልምድ ለማካፈል ይረዳል ብለዋል፡፡

ጉባኤውን ያዘጋጀው አላይንስ ፎር ሶቨርኒቲ ኢን አፍሪካ (AFSA) ዋና አስተባባሪ ሚሊዮን በላይ (ዶ/ር)፤ ጉባዔው ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ከ45 የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ከ250 በላይ ወጣቶች በአካል እንዲሁም ከሁለት ሺህ በላይ ወጣቶች በኦንላይን እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ጉባዔው የአፍሪካን ግብርና ሥነ ምሕዳርና ብዝኃ ሕይወት የመጠበቅን እንደ ዋና ጉዳይ አድርጎ የሚካሄድ መሆኑን ተናግረው፤ አፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነቷን ለማረጋጥ ሁሉም የእሴት ሰንሰለት በራስ አቅም ላይ የተመሰረተ መሆን ይኖርበታል ብለዋል ፡፡

ጉባዔው በቀጣይ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በየሁለት ዓመቱ እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡

ዳግማዊት አበበ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You