በማሠልጠኛው የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ሠራዊቱ ከመንግሥት በጀት ጥገኝነት እንዲላቀቅ የሚያደርጉ ናቸው

አዲስ አበባ፡የጦላይ ከፍተኛ ባለሌላ ማዕረግተኛ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት በግቢው የተጀመሩ የግብርና ልማትና የፈርኒቸር ሥራዎች ሠራዊቱ ከመንግሥት በጀት ጥገኝነት እንዲላቀቅና በምግብ እራሱን እንዲደግፍ ማስቻሉን አስታወቀ።

የጦላይ ከፍተኛ ባለሌላ ማዕረግተኛ ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ዋና አዛዥ ብርጋዴል ጄኔራል ጡምሲዶ ፊታሞ እንደገለጹት፤ በማሠልጠኛው የተጀመሩ የግብርና ልማትና የፈርኒቸር ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት አስገኝተዋል።

ትምህርት ቤቱ ዳር ድንበር ለመጠበቅ ደምና ላባቸውን ገብረው የሀገርን ሉዓላዊነትን የሚያስከብሩ ወታደሮች ከማሠልጠን ጎን ለጎን ከ87 ሄክታር በላይ የተለያዩ እርሻ ሥራዎች፣ የከብት እርባታ፣ የንብ ማነብ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የተለያዩ ቋሚ ተክሎችና የፈርኒቸር ውጤቶች እየለሙ ይገኛሉም ነው ያሉት።

እንደ ብርጋዴል ጄኔራል ጡምሲዶ ገለጻ፤ በ2016/17 በመኸር እርሻ በግቢው ከ85 ሄክታር በላይ በቆሎ ተዘርቶ ከ4 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል። በቦረና ድርቅ ጊዜ ዘር ለማቆየት ተብሎ የመጡ የቦረና ከብቶች በከፍተኛ እንክብካቤና ትጋት በተሠራው ሥራ ዘር ከማቆየት በተጨማሪ ሠልጣኙ የወተት ተዋፅዖ እንዲያገኝ አስችሏል።

በተጨማሪም የበቆሎ ምርቱ ወታደሩ ይበላው የነበረውን የሩዝ ምርት በበቆሎ ቅንጬ ለመተካት አስችሏል።

ብርጋዴል ጄኔራል ጡምሲዶ አክለውም፤ በመኸር እርሻ ከተመረተው በተጨማሪ በበጋ መስኖ የሽምብራ እርሻ ዝግጅት እየተደረገ ነው ያሉ ሲሆን በግቢው በፈርኒቸር ውጤት በተሠራ ሥራ ከአንድ ሚሊዮን 500 ሺህ ብር በላይ ወጪ ማዳን መቻሉን ጠቁመዋል።

ወታደር አምራች ሳይሆን የተመረተውን በመጠቀም ሀገርን የሚጠብቅ ብቻ እንደሆነ የሚታሰብ ቢሆንም ማሠልጠኛው ሀገራዊና ወገናዊ አስተሳሰብን መርሕ በማድረግ በተሠሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎች ከሠራዊቱ ተጠቃሚነት አልፎ ለአካባቢው ማኅበረሰብ እየጠቀመ መሆኑን ተናግረዋል።

ብርጋዴል ጄኔራል ጡምሲዶ፤ በግቢው ከሚሠሩ የልማት ሥራዎች በተጨማሪ የአካባቢውን ሥነ-ምሕዳር ከመጠበቅና በማሠልጠኛው ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ የዱር አራዊት እንዲጠበቁ መደረጉንም ጠቅሰዋል።

ከስድስት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የማረሻ ትራክተር እንዲሁም በአንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን አምስት የውሃ ፓምፖች በባለፈው ዓመት ከተመረተው ምርት መገዛቱን አስረድተዋል።

ማሠልጠኛው ከተጣለበት ሀገራዊ ኃላፊነት በተጨማሪ ያከናወናቸው በርካታ የልማት ሥራዎች ለሌላው ማሳያ የሚሆን ነው ያሉት ብርጋዴል ጄኔራል ጡምሲዶ፤ በዚህም በተለይ ለሠራዊቱ ተኪ ምግቦች ማቅረብ መቻሉን አብራርተዋል።

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You