መቼም ዘንድሮ ይህ ማኅበራዊ ሚዲያ ይሉት ጉዳይ አያሳየን የለም። ሰሞኑን ከአንዲት ወዳጄ ገጽ ደርሶ ያየሁት አንድ ወሬ በእጅጉ ሲያስደንቀኝ ከረመ። ነገሩ እንዲህ ነው። አንድ ከፍ ያለ ባለ ክሬም ኬክ ዙሪያው በቀለማት ደምቆ ከመሐሉ ጉልህ ቃል ሰፍሮበታል። መልዕክቱ የተጻፈው በእንግሊዝኛ ነው ‹‹ዲቮርስ›› ይላል። የጋብቻ ፍቺ እንደማለት።
ጉድ ፈላ። ‹‹ፍቺ›› ይሉት ቃል እኮ ትርጉሙ በጎ አይደለም። የትዳር፣ የጋብቻን መፍረስ የሚያረዳ ነው። ምን ያሻው ነው ጃል! እንዲህ አሽሞንሙኖ፣ አሳምሮ ‹‹እዩልኝ›› የሚለው? ነገሩ እያስደነቀኝ የሚያምረውን ትልቅ ኬክ በጥርጣሬ በዓይኔ ጫፍ ገረመምኩት። ልክ ነበርኩ። በጉልህ የተጻፈው ‹‹ዲቮርስ›› ይሉት ቃል መልሶ አፈጠጠብኝ።
አስገራሚው ጉዳይ ይህ ብቻ አይደለም። በኬኩ ዙሪያ በአማርኛ የተጻፈው መልዕክት በእጅጉ ያመራምራል። የጽሑፉን ሙሉ ሀሳብ በቀላሉ አምኖ ለመቀበል ይቸግራልና የአፍታ ጊዜን ልወስድ ግድ ነው። እንዲያም ሆኖ ጽሑፉን ከነትዝብቱ መቀበሌ አልቀረም። ‹‹ዲቮርስ›› ከሚለው ጽሑፍ በታች በአማርኛ የተጻፈውን ቃል አንድ በአንድ አነበብኩት። ‹‹እንኳንም ቀረብሽ፣ ቢቀር ዳቦ ድፊ፣ ጠላ ጥመቂ ነው›› ይላል።
ወዳጆቼ! እናንተም ይህን መሰል ጽሑፍ አይታችሁ፣ ታዝባችሁ ይሆናል። በእኔ በኩል ግን ግርምታው እስካሁን በውስጤ እንዳለ ነው። በአጭሩ የኬኩ ላይ መልዕክት የባልና ሚስቱ ፍቺ በመፅደቁ የሌሎች ሰዎችን የደስታ ስሜት ለማሳየት የተገለጸ ነው። ይህ መልዕክት ለብቻው ምንአልባት የሴቷን /የሚስቲቱን/ ባልንጀሮች ስሜት ያንጸበርቃል ባይ ነኝ።
መቼም አብዛኞቻችን ጊዜውን ማማረርና በጊዜው ማሳበብ ልምዳችን ሆኗል። ለዚህ አስገራሚ ጉዳይ ድንገት አስተያየት ብንጠየቅ ‹‹አይ! ጊዜ፣ ጊዜ አያሳየን፣ አያሰማን የለ›› እያልን ልናማርር እንችላለን። ለጊዜው በጊዜ ማሳበቡን እንተወውና ወዳነሳነው ሀሳብ እንመለስ።
እኔ አሁንም በሀሳብ በኬኩ ዙሪያ ነኝ። በዚህ ማኅበራዊ ገጽ ላይ የተለጠፈውን ጉደኛ ኬክ በዓይኔ ሕሊናዬ እየሳልኩ። የእናንተን አላውቅም እንጂ እኔ በኬኩ መቁረስ ጀርባ ይኖራሉ ያልኳቸውን እውነታዎች በምናብ እንዲህ እየገመትኩ ነው።
ፍቺ የፈጸመችው ወይዘሮ ይቅርታ፡- ወይዘሪት። ከፍርድ ቤት መልስ ለየት ባለ ልብስ ተውባ ከአናቷ ላይ የክብር አክሊል ደፍታ ትታየኛለች። በእርግጠኝነት እንደ እሷው ባለባበስ የደመቁ ሴቶች ዙሪያዋን ከበው ባለመደማመጥ ይንጫጫሉ። አብዛኞቹ የጥንዶቹን የቀደመ ታሪክ እያወሱ የሚሳሳቁ ናቸው። ጥቂቶቹ በባልንጀራቸው ትዳር መፍረስ አምነው ይሁንታው ላይ የሚያወጉ ይመስላል።
የኬኩ ዙሪያ ታዳሚዎች ፊት ላይ ጸጸት ይሉት አይነበብም። ሁሉም በተለየ ደስታና ፌሽታ እየቦረቁ የኬኩን መቆረስ ይናፍቃሉ። በእኔ ግምት በተጻፈው መልዕክት ላይ ተቃውሞ አቅራቢዎች እንደሌሉ ግልጽ ነው። በእያንዳንዱ ቃላት ላይ የስምምነት ሀሳባቸውን እንዳፀደቁ ይሰማኛል።
ምንአልባት የትዳሩ ‹‹እንኳን ቀረብሽ›› ኬክ የሚታጀበው በሻምፓኝና በሻማዎች ብቻ ላይሆን ይችላል። የፍቺው ደስታ ላሰባሰባቸው ታዳሚዎች የተዘጋጀ ምሳ፣ አልያም የራት ግብዣ አይጠፋም።
በእርግጠኝነት ይህ ዕቅድና ድርጊት በተለይ ከሴቷ ዘመድና ቤተሰቦች ይደገፍ አይመስለኝም። የትዳርን ክቡርነት የሚያውቁ፣ ልጃቸውን ለወግ ማዕረግ ያበቁ ወላጆች ለዚህ መሰሉ ዕቃ ዕቃ መሰል ጨዋታ እውቅናን አይሰጡም። እርግጥ ነው፣ በትዳር ዓለም ባልና ሚስት አይጋጩም፣ አይጣሉም ማለት አይደለም። ጠብ ጭቅጭቅና ምሬት በትክክል ይኖራል። ጎጆ ባለመስማማት ሲፈተን ግን ለመፍትሔው የራሱ ወግና ሥርዓት አለው።
ትዳር መሐል ንፋስ በገባ፣ ቅያሜ በመጣ ጊዜ ‹‹አንተም ተው፣ አንቺም ተይ›› ብሎ የሚዳኝ ሽማግሌ አይጠፋም። ባልና ሚስቱን በእኩል አስቀምጦ የሚዳኝ አስታራቂ ደግሞ ባብዛኛው በለስ ይቀናዋል። ትዳር እንዳይፈርስ፣ ጎጆ እንዳይፈታ፣ ልጆች እንዳይበተኑ የሚደረገው ማስማማት ተስፋ ባስቆረጠ ጉዳይ ላይ ፍሬ ይዞ ዓመታትን ሊቀጥል ይችላል።
በትዳር መሐል የሚፈጠሩ ችግሮች በዚህ መልኩ ሲፈቱ ‹‹እሰዬው›› ነው። ይህ አልሆን ብሎ የታሰበው ካልተሳካ ግን ትዳሩን በስምምነት አፍርሶ፣ ፍቺውን በፍርድ ቤት አፅድቆ በሠላም መለያየቱ አዲስ አይደለም።
አንዳንዴ በስምምነት የሚቋጩ ፍቺዎች ውሎ አድሮ ቤተሰባዊነት ይፈጥራሉ። እንዲህ ሲሆን ትናንት በ‹‹አንተ ትብስ፣ እኔ›› የተጋመደው አብሮነት ዛሬን በእህት ወንድምነት ተጣምሮ ትርጉም ያለው ሕይወት ይሰጣል።
ትዳር ከነችግሩም ቢሆን ሲፈርስ ቅር ያሰኛል። በእርግጥ እንከንና ችግር የዋጠው ሕይወት በይሉኝታ ብቻ ይቀጥል ላይባል ይችላል። መታወቅ ያለበት ግን ባብዛኛው መፍትሔ የሌለው ችግር አለመኖሩን ነው። ውሎ አድሮ ደግሞ ሁኔታዎች ሊለወጡ ይችላሉ። ዕድሜ ለመልካሞቹ ሽማግሌዎች ይሁንና ከባዱን አቅልለው፣ ቋጠሮውን የሚፈቱ ልበ ቀና አስታራቂዎች ሞልተዋል።
እኛ እስከዛሬ የምናውቀው፣ በሌሎችና በራስ ጥረት ጎጆ እንዲቆም ጥረት መኖሩን ነው። እኛ የምናውቀው ትዳር እንዳይፈርስ፣ ቤተሰብ እንዳይበተን ትግል መደረጉን ነው። ይህ አልሆን ብሎ ፍቺ ቢፈጸም ደግሞ የሌሎች ፈንጠዝያና ደስታ ታይቶ አይታወቅም። ‹‹እሰይ እነ እንቶኔ ተፋቱ፣ ተለያዩ›› ብሎ ጭፈራና ዕልልታ የለም። ለዛውም በገሀድ።
ዘንድሮ ግን ነገር ሁሉ ተቀይሯል። ለፈረሰ ትዳርና ጎጆ ከማዘን፣ ከማሰብ ይልቅ ለፍቺው ገሐዳዊ ዕውቅና ይሰጥ ይዟል። ዕውቅናው እኮ በተገቢው አካል ተችሮ ቢሆን አይደንቅም። በጥንዶቹ ልቦና ብቻ ቢቀርም እሰዬው ነው። ፍቺው ኬክ ተቆርሶለት፣ ሻምፓኝ ተከፍቶለት፣ በአጀብ ደምቆና በይሁንታ ፀድቆ ደስታን መፍጠሩ ግን እንደኔ በእጅጉ አሳዛኝ ያስብላል። ለዛውም ‹‹ትዳሩ እንኳንም ቀረብሽ፣አበጀሽ›› እየተባለ።
እስካሁን ከባሕላችን ውጭ የሆኑና ለእኛነታችን የሚጠቅሙ በርካታ ልማዶችን ከነጮቹ ወስደናል። እንዲህ ማድረጋችን እስከዛሬ ለኖርንበት ሕይወታችን ሲጠቅመን መኖሩን መካድ አይቻልም። አይበጁንም ባልናቸው መጤ ባሕሎች ላይ ግን ዓይን አንስተን፣ እጅ መሰብሰባችን ቢጠቅመን እንጂ አልጎዳንም። ይህ አይነቱን ማኅበራዊ እሴት የሚቃረን ጉዳይን ደግሞ ፈጽሞ ልንላመደው የማይገባ ተግባር ነው። ይህ ጅማሬ አጉል ልማድን ያጋባል። የትዳር ክቡርነትን ያቀልላል።
እኔ በግሌ ፍቺን አስመልክቶ በሚሰጠው የዕልልታ ዕውቅና ላይ መስማማትን አልሻም። ትዳር ሲፈታ፣ ጎጆ ሲበተን ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ‹‹እሰይ፣ጎሽ›› አያሰኝም። ለዛውም የሴትነት ወጉን አጣጥሎ፣ የነበረን ሙያ አንቋሾ ‹‹ቢቀር ዳቦ፣ቢረሳ ጠላው›› እየተባለ። እስቲ ልቦና ይስጠን። አበቃሁ።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም