ኢትዮጵያውያን ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው ሰርተፍኬት በሚያስገኘው የ“ኮደሮች” ሥልጠና ሊሳተፉ ይገባል

ከ242 ሺህ በላይ ሠልጣኞች የኮደሮች ሥልጠናን እየተከታተሉ ነው

አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያውያን ዓለም አቀፍ እውቅናና ተቀባይነት ያለው ሰርተፍኬት በሚያስገኘው የ”ኮደሮች” ሥልጠና ሊሳተፉ እንደሚገባ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡ የአምስት ሚሊዮን “ኮደሮች” ይፋ ከተደረገ ጀምሮ ላለፉት ሶስት ወራት ከ242 ሺህ በላይ ሠልጣኞች ተመዝግበው ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ እንደገለጹት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያስጀመሩት የአምስት ሚሊዮን “ኮደሮች” ሥልጠና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና እና ተቀባይነት ያለው ሰርተፍኬት የሚሰጥበት ነው፡፡

በመሆኑም ታዳጊዎች፣ ወጣቶች፣ የመንግሥት ሠራተኞች እና በተለያየ የሥራ መስክ ውስጥ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች የእድሉ ተጠቃሚ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል፡፡

የአምስት ሚሊዮን “ኮደሮች” ሥልጠናን በተመለከተ የተለያዩ አካላት ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑን ገልጸው፤ ሥልጠናው ምንም ዓይነት ክፍያ የማይጠየቅበት ነው፡፡ የመመዝገቢያ ሊንኩም በመንግሥት ኮሙኒኬሽን ይፋዊ ገጽ ላይ በተለያየ ጊዜ እያሳወቅን ነው ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

ሠልጣኞች በኦንላይን በነጻ ተመዝግበው ሥልጠናውን በማንኛውም ቦታ ሆነው በስልካቸው መከታተል ከመቻላቸውም በተጨማሪ ለሥልጠና በተዘጋጁ የትምህርት ተቋማት መከታተል እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

ሥልጠናው የኢትዮጵያ ወጣቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊ የሆኑ የዲጂታል ክህሎት እንዲኖራቸው ለማድረግ የተቀረጸ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአምስት ሚሊዮን “ኮደሮች” ይፋ ከተደረገ ጀምሮ ላለፉት ሶስት ወራት ከ242 ሺህ በላይ ሠልጣኞች ተመዝግበው ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ያሉና ያጠናቀቁ ሠልጣኞች መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡

ለሥልጠናው በአጠቃላይ ከተመዘገቡት ሠልጣኞች ውስጥ ከ81 ሺህ በላይ የሚሆኑት መሠረታዊ የፕሮግራሚንግ ሥልጠና፣ ከ78 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ መሠረታዊ የዳታ አናላይስስ ሥልጠና እየተከታተሉ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

ከ82 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ መሠረታዊ የአንዲሮይድ አፕሊኬሽን ላይ እየተሰጠ ያለውን ሥልጠና እየወሰዱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You